በታሪካዊው የለጋ ኦዳ የዋሻ ላይ የሚገኙ ኪነጥበብ ጌጦቹ ለረጅም ዘመናት ብዙም ሳይታወቁ ተደብቀው ኖረዋል፤ አልተዘመረላቸውም። የጥበብ ሥራዎቹ ፋይዳ እንደሌላቸው ተቆጥረው ተዘንግተውና ተረስተው ቆይተዋል። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለይም ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ግን ታሪክና ታሪካዊ ቦታዎች እውነተኛ ማንነታቸውን ለመተንፈስ አንደበት አውጥተዋል።
የ25 ዓመቱ አቶ አህመድ ኢብራሒም በለጋ ኦዳ ዋሻ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ፣ ጥንታዊ የጥበብ ሥራዎች እውነታው ስላልተነገረላቸው እንጂ ለአካባቢው ማህበረሰብ፣ ለሀገር መልካም ገጽታ ግንባታ እና በአጠቃላይ ለሰው ልጅ እጅግ የላቀ ፋይዳ ያበረክቱ ነበር። ድሬዳዋ ከተማም ዙሪያዋን በእንደእነዚህ ዓይነት ታሪካዊ ዋሻዎች መቀነት የታጠቀች ናት ሲሉ ገልጸዋል።
ማህበረሰቡ ስለ ቦታው ጠቀሜታ ያለው ግንዛቤ እምብዛም በመሆኑ ተንከባክቦ ሊይዘውና ሊጠብቀው አልቻለም። በዚህ የተነሳ የአካባቢው ሕፃናት በአካባቢው ከብቶች ሲያግዱ መጫዎቻቸው ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ አላበረከተም። በመሆኑም በሌላ መንገድ መያዝና መጠበቅ ይገባ ነበር ይላሉ።
አሁን ላይ በተገቢው በመጠበቅና በማስተዳደር ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆን በማድረግ ለብዙ ሰዎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መፍጠር የሚችል መሆኑን አቶ ኢብራሂም አብራርተዋል።
በሐምሌ ወር መጀመሪያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን ከአዲስ አበባ 548 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው የምሥራቋ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከሏ ድሬዳዋ እግር ጥሎት ሳይሆን አስቦበት ተገኝቶ ነበር።
በዚህ ወቅትም በከተማዋ ዙሪያ ጥምጥም የሚገኙ የገጠር አካባቢዎች በውል የሚታወቁትን የቀደምት ታሪካዊ የዋሻ ውስጥ ጥበቦች መመልከት ችሏል። ከእነዚህ በጥበብ የተንቆጠቆጡ ዋሻዎች መካከል ለጋ ኦዳ፣ፓርክ ኢፒክ እና ጎዳ አጅዋ ታሪካዊ ቦታዎችን ለሚያደንቅም ሆነ ለተመራማሪ በእጅጉ ጠቃሚነታቸው የላቀ ነው።
የለጋ ኦዳ ዋሻ ከከተማዋ ደቡብ ምዕራባዊ አቅጣጫ ከሚገኙ ዋሻዎች መካከል አንዱ ሲሆን በ38 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ይህ ዋሻ በ1933 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለተመራማሪዎች እንዲተዋወቅ የተደረገ ሲሆን ቅድመ አዝያስ እና ኦንሲዩ ዲ-ቻምፓርደን የተሰኙት ተምራማሪዎች የማስተዋወቁ ፈር ቀዳጆች እንደሆኑ ተጠቅሷል። (ዳኛቸው ለታ 2018)
በላይኛውና በታችኛው የዋሻው ንጣፎች ላይም ከ600 በላይ በቅብ/ስዕሎች የተንቀጠቆጡ ምልክቶችና ጽሑፎች ሰፍረው ይገኛሉ። የዋሻው ግድግዳ ተጨማሪ ሌሎች ስዕሎች እንዳሉት ምልከታዎቻችንና የሰነድ መረጃዎች ያሳያሉ።
የከተማው ባህልና ቱሪዝም የቱሪስት ኦፊሰር አቶ ደረጀ ታደሰ እንደገለጸልን አቶ አህመድ የዋሻ ውስጥ ጥበቦችን በመንከባከብ፣ በመጠበቅና በማስተዋወቅ እውቅና የተሰጣቸው ናቸው። ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ሀገርና ባህል ወዳድ ናቸውም ሲል አቶ አህመድን በተግባራቸው ያወድሳል።
አቶ አህመድ ኢብራሂም የ«በ» ፊደል በሚመስል በዋሻው የተለያዩ ክፍሎች የሚስተዋሉትን የምልክት ፊደሎች ላፍታም እንኳን ሳይዘነጋ መስመር በመስመር ሲያስታውስ እና ሲገልጽ በሙያው የተካነ አካልም አይስተካከለውም።
ሌላው ቀርቶ አንድ የሙያው ምሩቅ አስጎብኚ ሊያውቃቸው ከሚገባው መሠረታዊ እውቀቶች በላቀ ደረጃ የተካነ ነው። በእጅ አለመንካትን ጨምሮ አንድ ጎብኚ ሊከተላቸው የሚገቡ መመሪያዎችን ጠንቅቆ ከማወቁም በላይ በዋሻው ውስጥ በቅብ ያሽቆጠቆጡትን ጥበቦቹን በመጠበቅ ካለው ቅርበት የተነሳ ለይቶ ያውቃቸዋል። ከከተማው አስተዳደር አጅቦን የሄደው አስጎብኚ ገለጻውን ከሰዓት አኳያ ገታ እያደረገው እንጂ ስለ ዋሻው ውስጥ ጥበቦች ሲገልጽ ቢውል የሚጠገብ አይደለም።
ታሪካዊ ዋሻው ከሰባት ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ መሆኑን አጥኚዎቹ ያመላክታሉ። በመጥፋት ላይ ከሚገኙ ብርቅዬ ታሪካዊ ሀብቶችም አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል። የለጋ ኦዳ ዋሻ ጥንታዊ ጥበቦች የሰው ልጅ ከረጅም ጊዜ በፊት ለተግባቦት አገልግሎት ይጠቀምባቸው የነበሩ ምልክቶችን የእድገት ደረጃ በማሳየት ለዘርፉ ተመራማሪዎች ፍንጭ የሚሰጥ ነው።
የሚስተዋሉት የእንስሳት ሥዕሎችም ምናልባትም በዚያን ዘመን ይኖሩ የነበሩትን የእንስሳት ዓይነቶች የሚያመላክት ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የሥዕሎቹ ጥበቦቹ በዚያን ዘመን ይኖሩ የነበሩትን ሕዝቦች የአስተሳሰብ የእድገት አድማስ የሚመላክቱ ናቸው። አብዛኛውን የሥዕል ጥበቦቻቸውን አሽቆጥቁጠው የቀቡትም በቀይና በጥቁር ቀለም ነበር።
በዋሻው ከተሳሉት ስዕሎች መካከል ዝሆን፣ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ሰው፣ ምግብ እየተጎራረሱ የሚመገቡ ሰዎች፣ጊንጥ፣ የእጅ መሣሪያዎች እና ሌሎች ይገኙበታል። እነዚህ ጥበቦችም የሰው ልጅ በዚያን ዘመን ሲገለገልባቸው የነበሩ የእጅ መሣሪያዎችንና በአካባቢው የነበሩ እንስሳትና የሰዎች የሕይወት ዘይቤም ምን እንደነበር ጭምር ፍንጭ የሚሰጡ ናቸው።
በታሪካዊና ጥንታዊ ቦታዎቻችን ዙሪያ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥናትና ምርምር ቢካሄድ፣ የጥበብ ሥራዎቹና አካባቢው በተገቢው ቢጠበቅ፣ ያልተደረሰባቸውና ያልተሰሙ በርካታ እውነታዎች የሰው ልጅ እንደሚያገኝ ጥርጥር የለውም።
እውነታው የሚያሳየው በአሁኑ ዘመናዊ ትውልድ እና በቀደሙት ትውልዶች መካከል የተዘነጉ በርካታ ተጨባጭ እውነታዎች መኖራቸውን ነው። ልክ እንደ ለጋ ኦዳ ያሉ የጥንት ታሪካዊ አካባቢዎች ደግሞ የሰውን ልጅ ሊያያቸው የሚገቡ የተሸሸጉ የተለያዩ ታሪካዊ ምስጢሮችና እውነታዎች ስለመኖራቸው በር የሚከፍቱ ማሳያዎች ናቸው።
የዘርፉ ምሁራን ከፍተኛ ጥረት አካሂደው ድምዳሜ ላይ ያልደረሱባቸውና ማረጋገጫ ያላገኙባቸው በርካታ ታሪካዊ የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ደረጃዎች፣ የእምነት ደረጃዎች ወይም የመተጋገዝ መጠኖች ስለመኖራቸው ይነሳሉ። (Gabora, L. (2007). In Handbook of Theories and Methods in Archaeology.)
ቀደምት የሰው ልጅ ዝርያ ነው ተብሎ የሚታሰበው ሆሞኒድ (ቅድመ ሰብ፣ ዘረሰብ) የአስተሳሰብ ደረጃው ውስን እንደሆነ ይነሳል። የተቀናጀ የድርጊትና የተግባቦት ምላሽ ለመስጠት እንደሚሞክር ይነገርለታል። ሌሎች ተጽዕኖዎች ቢኖሩበትም። በተመሳሳይ ከዚያ በፊት የነበሩት ዝርያዎች ይሄን ማድረግ አለመቻላቸውም በታሪክ ሰፍሮ ይገኛል።
የዘርፉ ምሁራን እንደገለጹት ራሳቸው የሰሯቸው ባይሆኑም መጠለያዎችን ይጠቀሙ ነበር። ተፈጥሯዊ የሆኑ እንደ ከባድ ዝናብና የአየር ንብረት ዓይነት ተግዳሮቶችም ተግባቦቶቻቸውን ያውኳቸው እንደነበር ተጠቁሟል።
ማቲን (1996) የተሰኘ የዘርፉ ተመራማሪ እንዳመላከተው ከ60 ሺ እስከ 30ሺ ዓመታት መካከል ባለው በቀደምቱ የድንጋይ ዘመን የሰው ልጅ የግንዛቤ ደረጃ የተወሰነ ነበር። በሰው ልጅ ባህል መካከል ትልቅ መምታታትም ተስተውሏል።
ተመራማሪው እንዳሉት የሰው ልጅ አዝጋሚ የለውጥ እንቅስቃሴ ከስድስት ሚሊዮን ዓመታት በፊት ሲከሰት ከተስተዋለው በላይ በርካታ የምርምር ውጤቶች ተመዝግበው በሚገኙበት በዚህ ወቅት የሰው ልጅ ባህል ከዚያ ወቅት በበለጠ ደረጃ በእጅጉ መመታታቶች የሚስተዋሉበት ነው ብሏል።
በአውሮፓ ጥበብ ብቅ ብቅ እንዳለ ተፈጥሯዊ በሆኑ ዋሻዎች የእንስሳት ቅብ ያርፍባቸው እንደነበር ያስታውሳል። የሀገራችን ታሪካዊ ጥበብ የታተመበት የለጋ ኦዳ ዋሻ ጥበቦች ስላልተነገረላቸውና በሰፊው ባለመተዋወቃቸው እንጂ ስለ ዘመናዊ የሰው ዘር አመጣጥ ከሰባት ሺ ዓመታት በፊት ያምኑበት ከነበረው ምንጭ በተሻለና በላቀ ደረጃ አስረጂዎች ናቸው።
አደጋ የተጋረጠባቸውና በመጥፋት ላይ በመሆናቸው መታደግ ካልተቻለ የሚገኙት መረጃዎች አንድ በአንድ እየተንጠባጠቡና እየሾለኩ የሚባክኑ ከሆነ ጥሩውና እውነተኛው ታሪክ እየተደበቀ የሚሄድ መሆኑ አይቀርም። የተወሰነው የዋሻው ክፍል የመደርመስ ሁኔታዎች ይስተዋላል። ይሄን ማዳን ካልቻልን የታሪክ ተወቃሾች ወይም ባለዕዳዎች መሆናችን ግልጽ ነው።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከባህልና ቅርስ ጥበቃና ምርምር ባለሥልጣን ጋር በቅንጅት ጣራውን ለመጠገን ሙከራ አድርገዋል። የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የተጋረጡባት ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ አካባቢው ከመጥፋቱ በፊት ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግላት እንደሚገባ መሆኑ ተጠቁሟል።
አካባቢው የሁሉም ዓይነት የአየር ጸባይ ያለበት ሲሆን ማህበረሰቡ አርሶአደርና አርብቶአደር ነው። በመሆኑም በዋናነት ቡና እና ጫት አምራች ከመሆኑም በላይ መጠናቸው አነስተኛ በሆኑ የመስኖ ሥራዎች ፍራፍሬም ጭምር ያመርታል። የክረምቱን ዝናብ በመጠቀም ደግሞ ማሽላ ይመረታል።
የጎብኚዎችን ቀልብ የሚያማልል አቀማመጥ የታደለችው የበረሃዋ ንግስት በርካታ ሊተዋወቁና ሊወራላቸው የሚገቡ ቅርሶች ባለቤት በመሆኗ በሰፊው መሰራት ይኖርበታል። ይህ ሲሆን ታሪካዊ ቦታዎችና ታሪካዊው ሕዝብ ከግርዶሹ ብቅ ብሎ የሀገሪቱ ብሎም የዓለም ቅርስና ታሪክ አካል ይሆናል። የቱሪዝም ልማቱም እየፋፋ የኢኮኖሚው አጋዥ ሆኖ ታሪክ ለሀገሪቱ ውለታ ይከፍላል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2011
መሃመድ ሁሴን