በመዲናዋ አላግባብ ቆሻሻን ያስወገዱ አካላት ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ተቀጡ

አዲስ አበባ፡- በከተማዋ ቁጥጥር በሚደረግባቸው ሥፍራዎች አላግባብ ቆሻሻን ባስወገዱ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ 75 ሚሊዮን 715 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ ሥራ አስፈጻሚ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሠራቸውን ሥራዎች በተመለከተ በ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና በ2018 ዕቅድ ዙሪያ ውይይት ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጠብቆ ለማቆየት የደንብ ማስከበር ባለስልጣን በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የቁጥጥር ሥራን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በከተማዋ ቁጥጥር በሚደረግባቸው ሥፍራዎች አላግባብ ቆሻሻን ባስወገዱ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ 75 ሚሊዮን 715 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል ብለዋል፡፡

በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ስኬታማነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መሥራት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ሻለቃ ዘሪሁን፤ የመንገድ ደኅንነትን ማስጠበቅ፣ የከተማን ውበት መጠበቅ፣ የወንዝ ዳርቻዎች ፅዳትን ማስጠበቅ፣ አዋኪ ድርጊቶችን መከላከል፣ የመሬት ወረራን እና በግንባታ ፍቃድ ቁጥጥር ላይ የሚስተዋሉ የደንብ መተላለፎችን መልክ ማስያዝ የተቋሙ ኃላፊነት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን ሕገወጥ ድርጊቶች ለመቆጣጠርም ከተቋማት ጋር በቅንጅት የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የስታንዳርዳይዜሽንና ክትትልና ቁጥር ዳይሬክቶሬት አቶ ዳንኤል ቀፀላ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በተለያየ መንገድ በቅንጅት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መፍጠር ተችሏል፤ የሕገ-ወጥና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድን ለመከላከል በሚሠሩ ሥራዎች ለ338 ሺህ 411 የኅብረተሰብ ክፍሎችም ተመሳሳይ ግንዛቤ ተሰጥቷል፡፡

በተደረገው የቁጥጥር ሥራ ከኢንዱስትሪዎች ከሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚመነጭ ዝቃጭ፣ ተረፈ ምርት እና ቆሻሻ በአግባቡ ባላስወገዱ 329 ድርጅቶችና 539 ግለሰቦች ላይ 75 ሚሊዮን 715 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ርምጃ መወሰዱን በሪፖርቱ ተገልጸዋል፡፡

የመሬት ወረራን በመከላከል እና በመቆጣጠር በተወሰዱ ርምጃዎች በከተማዋ በመሬት ባንክ ያልተካተቱ 11 ሚሊዮን 652 ሺህ 379 ካሬ ሜትር ቦታን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በመረከብ እየተቆጣጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከል እና በመቆጣጠር በተወሰዱ ርምጃዎች በትምህርት ቤቶች ዙሪያ ደንብ በተላለፉ 5 ሺህ 220 ደንብ ተላላፊዎች ላይ ከተቋማቱ 500 ሜትር እንዲርቁ በማድረግ ለትምህርት ቤቶች ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ ከሠራቸው የሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር አንጻር 12 ሺህ 140 ሕገ-ወጥ ንግድን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ርምጃ መውሰዱን የገለጹ ሲሆን፤ የንግድ ፈቃድ ኖሯቸው ነገር ግን ከተፈቀደላቸው ቦታ ውጪ የበረንዳ ንግድ በሚፈጽሙ 7ሺህ 394 ደንብ ተላላፊዎች ላይ ርምጃ መወሰዱም ተገልጿል፡፡

የኢ-መደበኛ ንግድን ለመከላከልም ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በመሆን ቦታ ተሰጥቷቸው እንዲነግዱ እና ንግዱ በተማከለ እና ሕግን በጠበቀ መልኩ እንዲሄድ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ተብራርቷል፡፡

ባለሥልጣኑ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ግንባታ እና ፍቃድ ቁጥጥር ባለሥልጣን ተቋማት ጋር በሠራው የቅንጅት ሥራ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአዲስ ሕንጻ ግንባታ የግንባታ ማሻሻያ እና የእድሳት ፈቃድ እንደተሰጣቸው ጠቁመው፤ ነገር ግን አጠራጣሪ በሆኑ እና ክትትል በተደረገባቸው 3 ሺህ 854 ግንባታዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

በሪፖርቱ እንደተመላከተው የከተማዋን ውበት ለመጠበቅ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገባቸው ከሚገኙ ፍቃድ የሌላቸው ሕገ-ወጥ ማስታወቂያዎችን መቆጣጠር እንደሆነ ጠቅሰው፤ የማስታወቂያ ፍቃድ ሲሰጥ በግልባጭ ባለሥልጣኑ እንዲያውቅ እንደሚደረግ ገልጸው፤ ይህን ሂደት ባልጠበቁ 122ሺህ 826 ሕገ-ወጥ ማስታወቂያዎች ላይ ርምጃ መውሰዱንም ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በከተማዋ የሚስተዋለው የደንብ መተላለፍ በተጠናቀቀው የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት 69 ነጥብ 8 በመቶ መቀነሱም ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ኃላፊ ሻለቃ ዘሪሁን፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የፍትሕ እና የመልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ በጥምረት የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት ተቋማት ተገኝተዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በቅንጅት ከሚሠራባቸው ተቋማት ጋር የጋራ ውይይት ያደረገ ሲሆን በቀጣይ በጀት ዓመት ለሚሠሩ ሥራዎች ዕቅድ አስቀምጧል፤ በቅንጅት ለሚሠሩ ተቋማትም ዕውቅናን ሰጥቷል፡፡

በሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You