በአዲስ አበባ በ2017 በጀት ዓመት፡-

– መዲናዋን ተመራጭ የሚያደርጉ ሥራዎች ተሠርተዋል

– ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

– ከ360 ሺህ በላይ ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ከተማዋን ለነዋሪዎች ተስማሚ፣ በጎብኚዎች ተመራጭ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡ በበጀት ዓመቱ ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንና ከ360 ሺህ በላይ ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩንም አመልክተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ጉባኤው ላይ የአስተዳደሩን የበጀት ዓመቱን የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ትናንት ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ ለመኖር ምቹ ካልሆነ ጎስቋላ አካባቢዎች ለተነሱ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤቶችን፣ በቂ የመሥሪያ ሼዶችን፣ አረንጓዴና መጫወቻ ቦታዎችን፣ የጤናና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም የንግድ ሱቆች ተገንብተው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል፡፡ በተከናወኑ የልማት ሥራዎችም ከተማዋን ለነዋሪዎች ተስማሚ፣ በጎብኚዎች ተመራጭ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

በሁለተኛው የኮሪዶር ልማት 135 ኪሎ ሜትር የተሽከርካሪ መንገድ፣ 246 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 141 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ፣ 43 ኪሎ ሜትር የመሮጫ ትራክ፣ 53 የተሽከርካሪ እና እግረኛ መሻገሪያ ድልድዮች፣ 190 ኪሎ ሜትር የጎርፍ ማስወገጃ ሥርዓት ዝርጋታና፣ 83 ኪሎ ሜትር የድጋፍ ግንብ ሥራ ተሠርቷል ያሉት ከንቲባዋ፤ ሁለት ሺህ 830 የመብራት ምሰሶዎች፣ 179 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፤ ተከናውኗል፡፡ በርካታ የአረንጓዴ ልማት፣ የሕዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች፣ ዘመናዊ የመንገድ ዳር የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች መገንባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አመልክተው፤ የገቢ አሰባሰብ ንቅናቄ በመፍጠርና ጠንካራ የክትትል ሥርዓት መዘርጋት መቻሉ ለውጤቱ መገኘት አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡ አፈፃፀሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በገንዘብ ከ83 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ እድገት ለማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

በተገኘው ገቢም የመዲናዋን የልማት ፍላጎት ወጪ መሸፈንና ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ነዋሪ መደጎም መቻሉን ጠቅሰው፤ የከተማዋን የውሃ አቅርቦት እና የፍሳሽ አገልግሎት ለማሻሻል ከመንግሥት እና ከብድር በተመደበ 18 ቢሊዮን ብር በጀት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለሥራ ፈላጊ ዜጎች ዘላቂ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር እና የምግብ ዋስትና እጦት ተጋላጭነትን በመከላከል ድህነትን ለመቀነስ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ 300 ሺህ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ366 ሺህ044 ሥራ ፈላጊዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በከተማ ግብርና ዘርፍ 40 ሺህ 230፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ 91 ሺህ 737 እና በአገልግሎት ዘርፍ 234 ሺህ77 የተፈጠረ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የትምህርት ተሳትፎና ፍትሐዊነትን በማሳደግ በዕውቀትና በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድን ማፍራት በትኩረት ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል መሆኑን ጠቅሰው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቅበላ አቅምን አንድ ሚሊዮን 253 ሺህ 737 ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከ840 ሺህ 585 በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ መቻሉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከተማዋን ከጎበኙ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች፣ ከተካሄዱ ከ150 በላይ ኮንፍረንሶች፣ ኤግዚቢሽኖችና ኤክስፖዎች ከ143 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶችም ከ56 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ መዲናዋ ኢኮኖሚ ፈሰስ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You