ባለፈው ሳምንት አንድ ዘጋቢ /ዶክመንታሪ/ ፊልም አይቼ ነበር። ልመናን በማጥፋት ወይም በመቀነስ ዙሪያ ያጠነጠነ ነው። የራሴን ግምት ወስጄ ልመናን ለማጥፋት ቢያንስ 20 ዓመት ይፈጃል የሚል ሃሳብ ይዤ ነበር። በማግስቱ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መግለጫ ወጣ፡፡ መግለጫው አይቼውና ሰምቼው ከማውቀው ነገር በላይ ሰቅጣጭ ሆነብኝ። ወጣቱ በሽብርተኝነት ሰበብ የግፍ ግፍ ተሠርቶበታል፡፡ ሠርቶ መብላት በማይችልበት ሁኔታ መላ አካሉ ተሽመድምዷል። አካለ ጉዶሎ ሆኖአል። ወጣቱን ከልመና ለማውጣት ይውል የነበረ የሀገር ሀብት ተመዝብሯል፤ ተዘርፏል፡፡ በማንአለብኝነት የገባበት እስከማይታወቅ ድረስ ደብዛው ጠፍቷል፡፡ እንዴት ተደርጐ ከልመና ይወጣል? ምን አማራጭ አለ? ግራ የገባ ነገር ነው፡፡
እንዲህ ከሆነማ ልመና በ20 ዓመት ቀርቶ በ50 ዓመትም መጥፋቱ ያጠራጥራል። ያውም ብዙ ከልመና መውጫ አማራጮችን ይዞ ወንጀል፣ ዘረፋ፣ ሌብነትና ማጅራት መቺነት ነግሶ የሕግ የበላይነት ጠፍቶ የሚከተል መዘዝ ይዞ ነው። «ይሞታል ወይ ታዲያ» የሚለው ዘፈን የትውልድ መመሪያ ይሆናል። « ማን በልቶ ማን ጦም እንደሚያድር እንተያያለን»። የሚል መሪ ቃል ይፈጠራል። ይህ ሁሉ «ሁሉን ለእኔ በሚሉ ስግብግብ የቀን ጅቦች ክፋትና ንፍገት የሚመጣ ነው።
ኸሊል ጅብራን የተባለው ዝነኛ የሊባኖስ ፀሐፊ «The criminal» የሚል አስተማሪ ጽሑፍ አለው። «ወንጀለኛው» ብዬ ተርጉሜዋለሁ እነሆ፡-
በቤይሩት ከተማ የሚኖር አንድ ወጣት ነበረ። ፈርጣማ ነው፤ ጉልበት አለው። የመጣው ሥራ ሠርቶ ለመኖር ነበር። ሥራ ፈለገ አጣ። ለተራ ሥራ ከፍተኛ ተያዥ አምጣ አሉት። አይተውት ስለማያውቁም ፀጉር ልውጥ ሆነባቸው። ሥራ ለማግኘት ድፍን ቤይሩትን ቢዞርም ማግኘት ግን አልቻለም። ስለዚህ ወደ ልመና ገባና በየቤተ እምነቱ እየዞረ ለመለመን አልሆነለትም። ምዕመናኑ « ይሄ ምን ያስለምነዋል? ወጣት ነው ጠንካራ ነው ሠርቶ አይበላም? ሰነፍ ሆኖ ነው እንጂ ቢሠራ ይሻለው ነበር» እያሉ ምጽዋታቸውን ነፈጉት፡፡
እርሱም ጦም ውሎ ጦም ማደሩ በዛበት፣ በኋላ አንድ ቀን ፀሐይ ስታዘቀዝቅ ከቤሩይት ፈቀቅ ብላ ወደ ምትገኝ ኮረብታ ወጣ አንዱ ዛፍ ሥር ተቀምጦ ፈጣሪውን ማማረር ያዘ፡፡ ምነው አምላኬ በረሃብና በበረንዳ አዳር ይሄን ያህል የምታሰቃየኝ በየትኛው ኃጢአቴ ነው? ሠርቼ ልብላ ስል የምጠይቀው ተያዥ ነው። እኔ ዘመድ ቀርቶ የማውቀው ሰውም የለኝም። በየእምነት ቤቱ ሄጄ ለመንኩ ምዕመናኑ ጨከኑብኝ። ኧረ ተው ፈጣሪ ኧረ ተው ምህረትህን አውርድልኝ እያለ በእንባ ጭምር የታጀበ እግዚኦታውን ለፈጣሪው አሰማና ሲደክመው እዚያው ዛፉ ሥር በጀርባው ተንጋልሎ ሰማይ ሰማዩን ሲያይ ድንገት ዓይኑ አንድ ቅርንጫፍ ላይ አረፈ። ከሃሳቡ ባንኖ ተነስቶ ያን ቅርንጫፍ ቆረጠ። እንጨቱ ጠንካራ ነውና ለዱላም ለከዘራም ይሆናል። ጅንፎ አበጀለት። አሁን የልቡን ሊያደርስ እንደሆነ ነብሱ ነገረችው። ከዚያ ያን እህል ውሃ የማያሰኝ ሽመል ወደ ከተማይቱ ቀስሮ ጮኸ፡፡ «እናንት የቤይሩት ሰዎች ሆይ! ጨካኞች ናችሁ እኔ ብቻ በልቼ ልሙት ባዮች፣ ስግብግቦች፣ ለደሀ የማታዝኑ ከጅብ የከፋችሁ አውሬዎች ናችሁ። እነሆ አሁን ጊዜው ደረሰ። ማን በልቶ ማን ጦም እንደሚያድር እንተያያለን» አለና ጨለምለም ሲል ያን ሽመል ይዞ ወደ ከተማው ገባ። ከዚያ በኋላ ማታ ጠግቦ ወደ ቤቱ የሚሄደውን አንድ ሰው ሲወላገድ አየው። በያዘው የወይራ ሽመል ማጅራቱን ሲለው ሰውየው ወደቀ። በፍጥነት ኪሱን በረበረ። ደህና ገንዘብ አገኘ። በዚያም ገንዘብ ራሱን አሳመረ።
እንዲህ ከሆነማ ብሎ ማጅራት መምታቱን አጠናክሮ ቀጠለ። ገንዘብ በገንዘብ ሆነ፤ ቤት ተከራይቶ መዝረፍ መስረቅ የየዕለት ምሽት ሥራው ሆነ። ቀጥሎም ዘረፋውን በቡድን አደራጀ። በዋና ዋና የከተማይቱ መዝናኛዎች ሁሉም ዘርፎ ለእሱ ያስረክባል። ከዚያም ለቡድኖቹ የየራሳቸውን ድርሻ ይሰጣቸውና ይበተናሉ። እንዲህ ከሆነማ ተባለለት። ማን በልቶ ማን ጦም ያድራል በሚል ብሂልም ዘረፋና ሌብነት ከፖሊስ አቅም በላይ እስኪሆን ድረስ በዛ፤ ሕዝቡም ኡኡ ማለት ጀመረ። ያ መጀመሪያ በዚህ ወጣት ላይ የተሠራው ንፍገትና ጭካኔ ወጣቱን ወንጀለኛ አድርጐ አረፈው።
የእኛም ሁኔታ ወደዚያው እየሄደ ነው። በመቶ ሺህ ለሚቆጠር ወጣት የሥራ ዕድል ሊፈጥር የሚችል ገንዘብ ያውም ከሕዝብ ግብርና ታክስ የሚሰበሰብ ገንዘብ በጥቂት ስግብግቦች አማካይነት ተዘርፏል። ስለዚህ ወጣቱ ሳይወድ በግድ ወንጀለኛ ይሆናል። በአዲስ ፖሊስ ፕሮግራም የምንሰማውና የምናየው ነው። ቀን በጠራራ ፀሐይ ኪስ አውላቂው በዝቷል። ሞባይልና ቦርሳ ነጥቀው የሚሄዱበት ሁኔታም በሰፊው እየተስተዋለ ነው። በ12 ሰዓት ቤተክርስቲያን የሚሄዱ እናቶች የለበሱትን ጋቢ የሚነጠቁበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በተለይ ማታ ከ1-4 ሰዓት ያለው ጊዜ አደገኛ ሆኗል። ሕዝቡ የቡድን ሌቦችንና ዘራፊዎችን ለመከላከል የራሱን አደረጃጀት ፈጥሮና ከማኅበረሰብ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ተራ ገብቶ እየተዘዋወረ ሲጠብቅ ነው የሚያድረው፤ ይህ ሁሉ የሚሆነው ወጣቱ ሥራ ስለአጣ ነው። ሥራው ከየት ይምጣ? ገንዘቡ የት ሄደ? ቢባል የሜቴክ ጅብ ቅርጥፍ አድርጎ በልቶታል።
ሜቴክ ስንል ስለ አንድ ብሔር (ዘር) እያወራን አይደለም ስለ አንድ የመንግሥት ኩባንያ እንጂ። ሌቦች ሆን ብለው ዘረፋውን ከዘር ጋር ሊያገናኙት ይሞክራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ይህን ጉዳይ አስረግጠው አስረድተዋል። የብሔር ሌባ እና የዘር ሌባ የለም። ዘረፋና ሌብነቱ የተፈጸመው በአልጠግብ ባይ ስግብግብ ሁሉን ለእኔ ባይ አዕምሮ ቢስ ግለሰቦች ነው። በራሳቸው በወንድማቸው በእህታቸው በባለቤታቸውና በልጆቻቸው ስም ጥቅም ለማካበት የመንግሥትና የሕዝብን ሀብት የዘረፉት ግለሰቦችና በቡድን የተደራጁ ሌቦች ናቸው። የተዘረፉት እኮ የትግራይ እናቶችና አባቶች ጭምር ናቸው። ግብር ከፋዮችና አንድ ጀሪካን ውሃ ለማግኘት ሙሉ ሌሊት ወረፋ ይዘው ብርድ ላይ የሚያድሩ ምስኪኖች ከዘራፊዎች ያገኙት ሰባራ ሳንቲም የለም። ዘራፊዎች እኩይ ተግባራቸው ሲጋለጥ ግን በዘራቸው የተጠቁ ለማስመሰል አንድ ቀን እንኳ ዞር ብለው ያላዩትን ሕዝብ መሸሸጊያ ሊያደርጉት ይፍጨረ ጨራሉ። ይህ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው። ያጋለጣቸው ሥራቸው ነውና አሁንም ሥራቸው ያውጣቸው። የዘር ማንነታቸው ከሕግ በላይ አያደርጋቸውምና በሕግና በሕግ አግባብ ብቻ የእጃቸውን ያገኛሉ።
የሙስናን/ሌብነት ደረጃ በየሀገሩ እየለየ መግለጫ የሚያወጣ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም አለ። በዚህ ድርጅት መግለጫ መሠረት ሙስና የመንግሥትን ሥልጣን ለግል ጥቅም ባለማዋል ዴንማርክ፣ ኒውዚላንድ፣ ፊንላንድና ስዊድን ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ የእኛ አገር በ2014 ከዓለም ዘጠናኛ (90) ደረጃ ላይ ነበረች። የአሁኑ የ2018 መግለጫ /Index/ ከአምናና ካቻምናው ብዙም መሻሻል አልታየበትም፡፡
ለምሳሌ አሜሪካ በሙስና 16ኛ ነች። ፓኪስታን ከ180 አገሮች 117ኛ ስትሆን፤ ህንድ ደግሞ ከ175 አገሮች 81ኛ ናት። እኛም ከ180 አገሮች 90ኛ ከነበርንበት ደረጃ አሁን ላይ የባሰ ቁልቁል መውረዳችን ጥርጥር የለውም። ያውም የሰሞኑን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሰነድ ማስረጃ ሳይጨምር! የአሁኑንማ ቢሰሙ ምን ሊሉ እንደሚችሉና ከዓለም ስንተኛ ደረጃ ላይ እንደሚያስቀምጡን መገመት አይከብድም።
በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ብያኔ (definition) መሠረት ሙስና (ሌብነት) የሚለው ቃል ትርጉም «የመንግሥትን ሥልጣን ለግል ጥቅም ማዋል ነው። (Corruption is touse public power for personal Interest) በዚህ ትርጉም መሠረት የእኛዎቹ ዘራፊዎች የመዘበሩትን፣ የዘረፉትንና የሠረቁትን የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት እውነተኛ ባለቤቱ ለሆነው ሕዝብ መመለስ አለባቸው። በእርግጥ ገንዘቡ በየውጭ አገሩ በተቀማጭና በቢዝነስ ሽርክና ሄዶ እዚህ ላይኖር ይችላል። ቢሆንም መንግሥታችን ከየአገራቱ ጋር ተመካክሮ ማስመለስ ይጠበቅበታል።
ምግብ አጥቶ ከቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ያገኘውን በልቶ የሚያድር ዜጋ በሞላበት አገር ወጣቱ ሥራ አጥቶ ወደ ስርቆትና ሌብነት እየገባ ባለበት ሁኔታ ጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናት የሀገሪቱን ሀብት እንደፈለጉ ሲጫወቱበት ማየት ያሳዝናል፤ ያሳፍራል። ለከት ሊኖረውና ልጓም ሊበጅለትም ያስፈልጋል። ጊዜ የለንም ያለን ጊዜ አሁን ነው። የጀመርነውን ለውጥ በማይቀለበስበት ደረጃ ወደፊት ለማስቀጠል የሚቻለው ዛሬ ስንሠራ ነው፡፡ ሙስናን (ሌብነትን) ለመከላከል፣ ለማጋለጥና ሕግ ፊት ለማቅረብ ሁላችንም ለአገራችን ያለብንን የዜግነት ድርሻ እንወጣ!!!
ሙስና (ሌብነት) እና ልመና ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው። ሙስና፣ ሥራ አጥነት፣ የወጣቶች ሥርቆት፣ ማጅራት መቺነትና ኪስ አውላቂነት በጣም ጥብቅ ቁርኝት አላቸው፤ አይነጣጠሉም፤ አይለያዩም። አንዱ ባለበት ሌላውም አለ። በመንግሥት ሀብት ሙስና አለ ማለት ሥራ አጥነት፣ ወጣት ወንጀለኝነትና የቡድን ዘረፋ አለ ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል የሙስና ደረጃችን እ.አ.አ. በ2014 የነበረው ከ180 አገሮች 90ኛ ላይ የነበረው የአገራችን የሙስና ደረጃ አሁን ላይ ከ175 አገሮች 107ኛ ሆኗል። ከ2000-2017 ድረስ ባሉት 18 ዓመታት አማካይ የሙስና ዕድገታችን 109.6 ነበር።
የሙስና ደረጃችን ከፍ ባለ ቁጥር የድህነታችን መጠንም በዚያው ልክ ያድጋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ልመና በስንት እጥፍ ጨምሯል። ቤት ሰብሮ ስርቆትና የቡድን ዘረፋስ? ኪስ አውላቂነትስ? ሙስና በጨመረ ቁጥር ልመናና የወጣት ወንጀለኝነት አብሮ ይጨምራል። በዚያው መጠን የሕዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት ስጋትና ሰቆቃ ይሆናል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ክፍቱን ውሎ ክፍቱን ቢያድር ዞር ብሎ የሚያየው የሌለው ቤት ዛሬ ወጣ ብሎ ለመመለስ ቆልፎ እንኳን ማመን አልተቻለም።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ሙስና በተሰኘውና የመንግሥትን ሥልጣን ለግል ጥቅም በሚያውለው አሠራር የተነሳ ነው። አሁንም ቢሆን በየቦታው ትናንሽ ሜቴኮች ሞልተዋል። ስለሆነም መለቀምና ለሕግ መቅረብ አለባቸው። ለዚህም በዋናነት ተጠያቂው መንግሥት ቢሆንም ሕዝቡ እንደዜጋ የራሱ ሀብት ሲዘረፍ እጁን አጣጥፎ ሊቀመጥ አይገባም። ስለሆነም የየድርሻችንን እንወጣ።
ግ.ለ