
አዲስ አበባ፡– የውጭ ሀገር ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት የዜጎችን የመሬት ይዞታ የማግኘት መብት እንደማያጣብበው የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ አስታወቁ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው እለት የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ አስተላልፏል፡፡
አዋጁን አስመልክቶ ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ፤ የውጭ ዜጎች የመሬት ባለቤትነት የዜጎችን መሬት የማግኘት መብት እንደማያጣብብ ገልጸዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ በማብራሪያቸው፤ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ የከተሞች እና የውጭ ኢንቨስትመንት እንደተስፋፋ፣ ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት እንደጨመረ፣ የሕዝብ ቁጥር እንዳደገ፣ የዜጎች የአኗኗር ዘይቤ እንደተለወጠ እና መንግሥት ለመሠረተ ልማት ግንባታና ለከተሞች እድገት የሰጠው ልዩ ትኩረት ተደማምሮ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎትና እድገት እንደተከሰተ ጠቅሰዋል።
በሀገራችን የሪል ስቴት ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህ ዘርፍ ጤነኛ ውህደትን ተከትሎ እንዲያድግ እና እየሰፋ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦት ሚዛን ማስተካከል እንዲቻል ዘመናዊነታቸውን የጠበቁ፤ የውሃ ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገድ ፣ የጤና እና የትምህርት መሠረተ ልማት የተሟላላቸው የቤት ልማቶችን ማስፋፋት ያስፈልጋል። በመሆኑም የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ይዞታ መሆን የሚችሉበትን እድል መፍጠር አስፈላጊና ተገቢ አማራጭ ነው ብለዋል።
የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት ወይም ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል መሬት የሚያገኙበትን ሕጋዊ አሠራር መዘርጋት፣ የውጭ ዜጎች እና ባለሀብቶች እምነት ኖሯቸው የውጭ ካፒታል በኢትዮጵያ ሥራ ላይ እንዲውል ያስችላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የአዋጁ መጽደቅ አዎንታዊ ሀገራዊ ኢንቨስትመንት ምልከታ እንዲኖር ለማድረግ እና የኢንቨስትመት ፍሰትን ለማሳለጥ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል።
ረቂቅ አዋጁ አራት ክፍሎችና 20 አንቀጾች እንዳሉት ተናግረው፤ በውጭ ዜጋ ስለሚያዝ የማይንቀሳቀስ ንብረት፣ ቅድመ ሁኔታዎችና ገደቦች፤ የባለቤትነት ወይም የይዞታ ቀሪ መሆን፣ ስለማመልከቻ፣ ፈቃድና የባለቤትነት ወይም የይዞታ ማረጋገጫ ሂደት፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባራትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን አካቷል ብለዋል።
ረቂቅ አዋጁን የሚደግፉና ጥንቃቄ የሚሹ ሃሳቦችም ከምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል።ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፤ የአዋጁ መጽደቅ የሀገር ውስጥ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ ያደርጋል፤ የመሬት በውጭ ዜጎች መያዝ እንደደቡብ አፍሪካ ኮሎናይዜሽን ሊያመጣ ይችላል፤ ሀገር ውስጥ የተገኘ ካፒታልን ወደ ሌላ ሀገር ለማሸሽ በር ይከፍታል፤ የታክስ ስወራንና የሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ሊያባብስ ይችላል፤ ብሔራዊ ደህንነትን ስጋት ላይ ይጥላል፤ መሬት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ንብረት በመሆኑ አይሸጥም አይለወጥም ከሚለው ከሕገ- መንግሥቱ አንቀጽ 40 ድንጋጌ ጋር ይጋጫል፤ የዜጎች የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ይህን አዋጅ ማጽደቅ ተገቢ አይሆንም የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተዋል፡
በተቃራኒው በአዋጁ መጽደቅ አስፈላጊነት ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል፤ የአዋጁ መጽደቅ ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት ጋር በትብብር በመሥራት ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ያፋጥናል፤ ኢትዮጵያውያን በሌሎች ሀገራት የመሬት ባለቤት እንደሆኑ ሁሉ፤ የሌሎች ሀገራት ዜጎችም በኢትዮጵያ የቤት ባለቤት መሆናቸው ፍትሐዊ ነው፤ ኮሎናይዜሽን በሌሎች ሀገራት ዜጎች ላይ የጭቆና ቀንበር በማስቀመጥ ተጠቃሚ መሆንን የሚመለከት ሲሆን፤ መሬትን ለውጭ ዜጎች መሸጥ ግን የውጭ ምንዛሪን በማግኘት ጥቅምን ማረጋገጥ ስለሆነ ተመሳስሎ የለውም፤ አዋጁ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ያሳድጋል፤ የመኖሪያ ቤት ችግርን ይፈታል፤ የሥራ እድልን ይፈጥራል፤ የኢትዮጵያን ተፈላጊነት ያሳድጋል፤ የሚሉ ሃሳቦች በአዎንታዊነት ከተነሱት መካከል ናቸው።
በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ በደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 53 -4 እና በሕግ አወጣጡ መመሪያ ቁጥር 11/2000 አንቀጽ 17-1ሀ መሠረት፤ ለዝርዝር እይታ ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ እንዲቀርብበት ተደርጓል።
በእለቱ ምክር ቤቱ ሌሎች ሁለት ጉዳዮችንም ተመልክቷል። በእዚህም በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ የ29ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። በሌላ በኩል የከተማ መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከተማ መሬት ይዞታና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ እንዲደነገግ ለምክር ቤቱ ያቀረበው ረቂቅ አዋጅ ሲሆን፤ ይህም አዋጅ ቁጥር 1381/2017 ሆኖ በሦስት ተቃውሞ እና በሁለት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም