
-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም
አዲስ አበባ፡- ክንደ ብርቱው የመከላከያ ሠራዊት መሥዋዕትነት በመክፈል የጠላትን ሴራ በማክሸፍ ኢትዮጵያን እያጸና እንደሚገኝ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የምዕራብ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በነቀምቴ ስታዲየም ትናንት ሲከበር በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የመከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ እና የማጽናት ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል።
በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ልማት እንዳይረጋገጥ ለማድረግ የሚጥሩ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ሰላም እያሰፈነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ክንደ ብርቱ ሠራዊቱ መሥዋዕትነት በመክፈል የጠላትን ሴራ በማክሸፍ ኢትዮጵያን እያጸና እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የምዕራብ ዕዝ መንግሥት እና መከላከያ ሠራዊት የሚኮሩበት ጀግና ዕዝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዕዙ የኢትዮጵያ ጋሻ በመሆን ሀገሩን እየጠበቀ ይገኛል ብለዋል። ባለድል በመሆን የተቋማችን ኩሩ ዕዝ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፤ ምዕራብ ዕዝ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሊጠናቀቅ ባለበት በአሁኑ ወቅት የምሥረታ በዓሉን ማክበሩ ቀኑን ልዩ እንደሚያደርገው አብራርተዋል፡፡
ዕዙ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚቃጡ ማንኛውንም ጥቃት በመመከት ሀገርን እያኮራ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ሠራዊቱ በአሸባሪው እና በጽንፈኛው ላይ ርምጃ በመውሰድ ሰላምን እያረጋገጠ እንደሚገኝም ጨምረው ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ አሁንም ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ምዕራብ ዕዝ በየትኛውም ቦታ በመንግሥት የተሰጡትን ግዳጆች በጀግንነት እየተወጣ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሠለ መሠረት፤ ዕዙ በጽናት ሀገሩን እየጠበቀና የተሰጡትን ግዳጆች በጀግንነት እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሀገሪቱን ዳር ድንበር በመጠበቅና ሰላም በማረጋገጥ ላይ እንደሚገኝም ተናግረው፤ የኢትዮጵያ ጋሻ የሆነው ምዕራብ ዕዝ በየትኛውም ቦታ ሕዝባዊ ባህሪን በመላበስ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ ለአብነትም የታላቁ የህዳሴ ግድብን በመጠበቅ እና ለግድቡም ቦንድ በመግዛት ሕዝባዊነቱን ያረጋገጠ ዕዝ ነው ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ሰላም እያረጋገጠ የሚገኝ ጀግና የሕዝብ ልጅ ነው ያሉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ፤ በክልሉ ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥና የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መሥዋዕትነት በመክፈል ሰላምን እያረጋገጠ የሚገኝ ጀግና የሕዝብ ልጅ መሆኑን ገልጸው፤ እያበረከተ ላለው ተግባርም በክልሉ መንግሥት ስም ምስጋና አቅርበዋል። የምዕራብ ዕዝም የወገን መከታ በመሆን በከፍተኛ ጀግንነት ሀገሩን እያገለገለ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመርሃ ግብሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሠረት፣ ከፍተኛ ጄነራል መኮንኖችና ሌሎች አመራር አባላት ተሳትፈዋል።
እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንዲሁም የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የምዕራብ ዕዝ 47ኛ ዓመት ምሥረታ በዓሉን ለሶስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበሩ ታውቋል። የምዕራብ ዕዝ የተመሠረተበት 47ኛ ዓመት በዓል ‘የጽናት ተምሳሌት፤ የኢትዮጵያ ጋሻ’ በሚል መሪ ሃሳብ በኦሮሚያ ክልል በነቀምቴ ከተማ ወለጋ ስታዲየም ትናንት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም