
የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞችን ወደ ሊቢያ ለመላክ የያዘው ዕቅድ፤ የግለሰቦቹ በሕግ ሂደት ውስጥ የማለፍ መብት እንዲከበር የተላለፈውን የቀደመ ውሳኔ “በግልጽ የሚጥስ ነው” በማለት አንድ ዳኛ በጊዜያዊነት እንዲታገድ ወሰኑ። ይህ ውሳኔ የተሰማው የአሜሪካ መንግሥት ስደተኞች ላይ እየወሰደ ካለው ርምጃ ጋር በተያያዘ ሁለት ባለሥልጣናት አገሪቱ በቅርቡ ስደተኞችን ወደ ሊቢያ ማባረር ልትጀምር እንደምትችል ከተናገሩ በኋላ ነው።
ባለሥልጣናቱ ስደተኞችን ወደ ሊቢያ ማባረርን በተመለከተ ለሰጡት አስተያየት የሊቢያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ሃሚድ ደቤይቤህ በኤክስ ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ አገራቸው “በየትኛውም ሁኔታ የስደተኞች መዳረሻ አትሆንም” በማለት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ባለሥልጣናት እንዳሉት የአሜሪካ ጦር ሠራዊት በዚህ ሳምንት ውስጥ ስደተኞችን ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር በአውሮፕላን ሊያጓጉዝ ይችላል።ሊቢያ ከአስር ዓመት በላይ በግጭት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በአገሪቱ ውስጥ በሚፈጸም ወንጀል፣ ሽብርተኝነት እና ተቃውሞ ምክንያት ዜጎቹ ወደዚያ እንዳይሄዱ የሚመክር ሆኖ ሳለ፤ ስደተኞችን ወደ ሊቢያ ለመላክ የተላለፈው ውሳኔ ውዝግብ ማስነሳቱ አይቀርም ተብሏል።
የኢሚግሬሽን ጠበቆች የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ለማስቆም ረቡዕ ዕለት በማሳቹሴትስ ግዛት ለሚገኙ ዳኛ አቤት በማለት “በአስቸኳይ” በጊዜያዊነት እንዲታገድ ጠይቀዋል። ጠበቆቹ “ከተዓማኒ ምንጮች የሚወጡ በርካታ ዘገባዎች ስደተኞችን በአስቸኳይ ከአሜሪካ ወደ ሊቢያ ለመውሰድ በረራዎች እየተዘጋጁ” መሆኑን እንደሚያመለክቱ በመግለጽ፤ በፍርድ ቤት እግድ እንዲጣልላቸው ጠይቀዋል።
ይህንንም ተከትሎ ዳኛ ብራያን መርፊ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ የአሜሪካ መንግሥት ስደተኞችን በአስቸኳይ ለማስወጣት የሚያስችለው ዕቅድ፣ ከዚህ ቀደም ስደተኞች ከአገር የማባረር ውሳኔ ሳይተላለፍባቸው ከሀገር እንዳይወጡ በሚል በፍርድ ቤቶች ያስተላለፉትን ውሳኔ የሚቃረን በመሆኑ ዕግድ አስተላልፈዋል። ቀደም ሲል የወጣው የፍርድ ቤት ውሳኔ ባለሥልጣናት ስደተኞችን ከአገር ከማባረራቸው በፊት በሚገባቸው ቋንቋ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ እና ላለመባረር ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለፍርድ ቤት ጥያቄ የሚያቀርቡበት ዕድል መመቻቸት እንዳለበት ያሳስባል።
ስደተኞችን ወደ ሊቢያ ለማባረር የተያዘውን ዕቅድ ያውቁ እንደሆነ የተጠየቁት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በሰጡት ምላሽ፣ “የማውቀው ነገር የለም። የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤትን መጠየቅ አለባችሁ” ሲሉ መልሰዋል። የትራምፕ አስተዳደር ሕገወጥ ያላቸውን ስደተኞች እንዲቀበሉት ከጠየቃቸው በርካታ አገራት መካከል አንዷ ሊቢያ ሳትሆን እንደማትቀር ይታሰባል ።
ሩዋንዳ በዚህ ሳምንት ከአሜሪካ ጋር በሚደረግ ንግግር “የመጀመሪያ ደረጃ ላይ” መሆኗን ስትገልጽ፤ ቤኒን፣ አንጎላ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኢስዋቲኒ እና ሞልዶቫም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ውስጥ ተጠቅሰዋል። እስካሁን አሜሪካ ምን ያህል ስደተኞችን ወደ ሊቢያ ለማባረር እንዳቀደች ወይም ስደተኞቹ ወደየትኛው የሊቢያ ክፍል እንደሚወሰዱ የታወቀ ነገር የለም።
በአውሮፓውያኑ 2011 የሙአመር ጋዳፊ አስተዳደር ከሊቢያ ከተወገደ በኋላ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት አገሪቱ ሁለት አስተዳደር አላት። ምዕራባዊው ክፍል በተባበሩት መንግሥታት በሚደገፈው መንግሥት ሲተዳደር፣ ምሥራቃዊው ክፍል ደግሞ በጄኔራል ኻሊፋ ሃፍታር ቁጥጥር ስር ይገኛል። ባለፈው ሰኞ የጄነራሉ ልጅ ዋሽንግተን ውስጥ ከአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የተገናኘ ሲሆን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እና የሊቢያ ቃል አቀባይ ግን ንግግሩ ስደተኞችን በማባረር ላይ እንዳልሆነ አስተባብለዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው ጥር ወደ ከሥልጣን ከተመለሱ በኋላ አወዛጋቢውን የጦርነት ጊዜ ሕግን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ስደተኞችን ከአሜሪካ የማባረር ዘመቻ ጀምረዋል።በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ደግሞ በፈቃዳቸው አሜሪካንን ለቀው ለሚወጡ ሕገወጥ ስደተኞች መንግሥት አንድ ሺህ ዶላር እንደሚሰጣቸው አሳውቋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም