
በዲግሪ ከተመረቅሁ እንደቀልድ አንድ መንፈቅ ሆነኝ። ሥራ ፍለጋ ማስረጃዎቼን በአንዲት የላስቲክ ቦርሳ ውስጥ ከትቼ ማለዳ፣ አራት ኪሎ ፣ ፒያሳ፣ ለገሐር፣ ደግሞ ሜክሲኮ ስኳትን እውልና ማታ እግሬ ቀጥኖ እመለሳለሁ። እግር እንደ እርሳስ የሚያልቅ ቢሆን ኖሮ የእኔ ይቀድም ነበረ። ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ፣ ጫማዬ አቻየው ነው። አባቴ ነው ያወረሰኝ። እኔም ዕድሜ ይስጠኝ እንጂ የወደፊት ልጄ የኮቴ ነገር አያሳስበውም። ለመጀመሪያ ጊዜም፣ “እንደ እውነቱ ከሆነ በአሁኑ ሰአት በአዲስ አበባ ሥራ ከመፈለግ ይልቅ አልማዝ መፈለግ ይቀላል” ስል ተፈላሰፍኩ፡፡
ዘወትር ብትት ብዬ ቤቴ ስገባም፣ የእናቴ የዘወትር ጥያቄ፣
“ዛሬስ እንዴት ነው ምን አዲስ ነገር አለ?” መልስ አልመልስላትም ይልቁኑ ከቀኝ እጄ ከወጣ ላቦት የወረዛች ዶክመንት መያዢያዬን ወዲያ አሽቀንጥሬ እጥልና ከበርጩማው ላይ ዘፍ ብዬ እቀመጣለሁ እንጂ። ብዙ ጊዜ ዶክመንቱ ብትንትኑ ይወጣል፡፡
እናቴ የተበታተነውን እያስተካከለች፣ “አትበሳጭ ማን ያውቃል አዛኝቷ፣ የጭንቅ አማላጅቷ ነገ የምታደርገውን” ትላለች። በትልቅ ትሪ ላይ ኮትቻ አፈር የመሰለ እንጀራ አንጥፋ፣ ፊፍቲ ሴንትን የሚመስል ሽሮ ቁጭ ታደርግበትናም፣
“በል አሁን እራትህን ብላ” እያለች አይን አይኔን እያየች ቡና ታፈላልኛለች። እየተሳቀቅሁ እበላለሁ። ቡናዋንም መርዝ የምጠጣ ያህል በግድ እውጠዋለሁ፡፡
“እዚያ ማንትስ መስሪያ ቤት ደግሞ ምን አሉህ?” ከ ሀ እስከ ፐ እነግራታለሁ፡፡
ማንትስ መሥሪያ ቤት ዶክመንቴን ባስገባሁ በምናምን ቀኑ የእናቴ ስልክ ላይ ደውለው፣ ለጽሁፍ ፈተና ጠሩኝ። ሄድኩ። አመልካቹ እንደ ዓባይ መንገድ ተጠማዟል። ፈተናው ቀረበ፤ ጥያቄዎቹ እንደሚከተሉት ናቸው
ሥራ ለምን ይጠቅማል?
ሥራን ማን ፈጠረ?
ሥራ ባይኖር ምን ትሠራለህ?
ሥራ ከሥር ጋር ያለውን አንድነትና ልዩነት ግለጽ?
ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው ያሉት ሰውዬ ማናቸው፣ ሥራቸውስ ምን ነበር?
5.1 ለምን አሉ?
5.2 መቼ አሉ?
5.3 ለማን አሉ?
5.4 በምን ምክንያት አሉ?
ለሁሉም ጥያቄ ግልጽና የማያሻማ መልስ ስጥ። እኔም የሚከተለውን መልስ ሰጠሁ፡፡
ሥራ ለምን ይጠቅማል?
ሥራ ሥራ ሥራ ለምን ነበረ የሚጠቅመው? . . . እንጃ አላውቀውም። ለምን ይሆን እናንተዬ?
- ሥራን ማን ፈጠረ?
ሥራን የፈጠረው አቶ ሥራህ ብዙ የተባለ ግለሰብ ነው
- ሥራ ባይኖር ምን ትሠራለህ/ትሰሪያለሽ?
ሥራ ባይኖር እሠረሥራለሁ፡፡
- ሥራ ከሥር ጋር ያላቸው አንድነትና ልዩነት ግለጽ/ጭ
ሥራና ሥር በድሮ ጊዜ ወንድምና እህት ነበሩ አሉ። እንዲያውም ሥራሥር የሚለው ኃ.የተ. የግል ኩባያ የነርሱ ነበር አሉ፡፡
- ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው ያሉት ማናቸው?
እትዬ ሳራ ናቸው፡፡
5.1 ለምን አሉ?
ሥር በጣሽ ባላቸው በነገር እሾህ እየተተናኮሱ ሥራ አላሰራ ስላሏቸው
5.2 መቼ አሉ?
ግቢያቸውን በእሾህ እያሳጠሩ ሳለ
5.3 ለማን አሉ?
ለባላቸው፤ ሥርህ ይበጠስ ሲሉም መርቀዋቸው ነበር አሉ በጊዜው፡፡
5.4 በምን ምክንያት አሉ?
ከሠራተኛቸውጋ ጠርጥረዋቸው
እናቴ በመልሴ ደስ አላት
በል እንግዲህ ለቃለ መጠይቁ ደግሞ በርትተህ አጥና። ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ምንድነው የማጠናው? . . . ለነገሩ እናቴ ልክ ናት። እዚህ አገር ሁሉም ነገር በጥናት ነው። በደጅ ጥናት፡፡
እሺ፡፡
ተኛሁ። ቃለመጠይቁን እየናፈቅሁ፡፡
ምንጭ:- ከዳዊት ወርቁ አጫጭር ልቦለዶች የተወሰደ
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም