የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ማሳያ መስታወቶች

በአንድ ሀገር የሚገለጥ የሥልጣኔ፣ የኢኮኖሚ፣ የነጻነት፣ የእድገንና ዲፕሎማሲን የመሳሰሉ መስኮች ታሪክ በትውልዶች ቅብብሎሽ ውስጥ እየተሠራ እና እያደገ የሚሄድ ነው። የቀደሙት እየጀመሩ የሚከተሉት ያሳድጉታል። አንድ ቦታ ተጀምሮ አያልቅም። በአንድ ጊዜ ተሠርቶም የሚጠናቀቅ አይሆንም። ለዚህ ደግሞ፣ እንደ ሀገር የሥልጣኔ መንገዳችንን፤ የኢኮኖሚም ከፍታና ዝቅታችንን፤ የሀገር ግንባታ ጉዟችንን መመልከቱ ጥሩ ማሳያ ነው።

ይሄ እውነት ደግሞ ላለፉት ስድስት ዓመታት በተጓዝንበት መንገድ በእጅጉ እየተገለጠ የመጣ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ዓመታት፤ በአንድ በኩል ነባር እሴቶችን የማሳደግ ሥራ ተሠርቶባቸዋል። ችግሮችን እያረሙና መልካም መሰረቶችን አልቆ እያደሱ የተሄደባቸውም ናቸው። በዚህ በኩል ታሪክ፣ ባሕል፣ ቅርስና ማንነት ተጣምረው የተገለጡባቸው አያሌ ቅርሶች ከተሰወሩበት አቧራና ቆሻሻቸው እየተራገፈ ደምቀውና ገዝፈው እንዲገለጡ ተደርጓል። የአዲስ አበባ መልክ ደግሞ የዚህ አብነት ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ አዳዲስ ሥራዎችን ከፍ ባለ ደረጃ ጀምሮ የመጨረስ ጉዞውም ተጠቃሽ ነው። ይሄም አዲስ አበባን ጨምሮ አያሌ ሥፍራዎች ላይ እየተተገበረ ያለ፤ እንደ ሀገር ከፍ ላለ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሥነ ልቡናዊ ከፍታዎች ዋጋ ያላቸው ተግባራት የተከናወኑበት ነው። ለዚህ ደግሞ በግብርናው፣ በአረንጓዴ ዐሻራው፣ በሌማት ቱሩፋቱ፣ በማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው መሰረተ ልማት ግንባታዎች፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፤… መስኮች የተከናወኑ ታላላቅ ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በማሕበራዊ ገጻቸው “ይህ ዓመት የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ነው ባልነው መሰረት እየመጣ ያለው ለውጥ ይበል የሚያስብል ነው።” ሲሉ የገለጹበት መንገድም፤ እንደ ሀገር የተጀመሩ የላቁ ተግባራት የኢትዮጵያን ከፍታ፤ የኢትዮጵያውያንም ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን የመሆን አይቀሬነት ከማስገንዘብ ባለፈ መግለጥ ያስቻሉ ሥራዎች መሠራታቸውን የሚያረጋግጥ ነው።

በዚህ በኩል፣ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን አመላካች ከሆኑ አያሌ ተግባራት መካከል፤ ጥቂቶቹን ለመጠቃቀስ ልሞክር። የመጀመሪያው የኢኮኖሚው መስክ ውጤት ነው። ከሰሞኑ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በያዝነው ዓመት አጠቃላይ ኢኮኖሚው በታቀደው መሠረት በ8ነጥብ4 በመቶ የሚያድግ መሆኑ ታይቷል። ይሄ እድገት በዘርፉ ደረጃ ሲታይም፣ ግብርና በ6 ነጥብ1 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ በ12 ነጥብ8 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ በ12 በመቶ፣ ኮንስትራክሽን በ12 ነጥብ3 በመቶ፣ እንዲሁም አገልግሎት በ7 ነትብ1 በመቶ የሚያድጉ ስለመሆኑ አመላክቷል።

እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲው መስክ ስኬቶችም የዓመቱ መገለጫዎች ናቸው። ከዲፕሎማሲው አኳያ፣ ኢትዮጵያ በባለ ብዙም ሆነ በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ጥቅሞቿን የምታስጠብቅበትን ልዕልና ተጎናጽፋለች። ለምሳሌ፣ ከሶማሊያ ጋር የነበረውን ጉዳይ በውይይት መፍታት፤ የባሕር በር ጥያቄውንም ዓለምአቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ ችላለች።

በተሠሩ የፖለቲካና የጸጥታ ተቋማት ሪፎርሞችም ኢትዮጵያ የነበረባትን የሕልውና አደጋ ቀልብሳ ወደ አስተማማኝ ሕልውና እየተሻገረች ነው። ዛሬ ላይ መንግሥት የፈጠረው አቅም፣ የፀረ ለውጥ ኃይሉ መዳከም እና ዓለም አቀፍ ለውጡ የኢትዮጵያን ሪፎርም ለማሳካት የተሻለ ዕድል የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን፤ መንግሥትን በኃይል የመጣል ቅዠት ውስጥ ያሉ ኃይሎች ሁነቱን ተገንዝበው በብዛት ወደ ሰላም እንዲመለሱ እያደረገ ይገኛል።

ሌላው በውጤት የምንጠቅሰው አብነት ደግሞ፣ በማሕበራዊ ዘርፍ ተግባራት የተገኘው ሲሆን፤ በዚህ ረገድ “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ቃል ከ82 ቢልዮን ብር በላይ ድጋፍ በመሰብሰብ በአጠቃላይ 6815 ትምህርት ቤቶች በመላ ሀገሪቱ መገምባት የተቻለበትን ሥራ መጥቀስ ይቻላል። ይሄ ሥራም የነባር ትምህርት ቤቶችን አቅም ለማሻሻል እና በግጭት የተጎዱትን ለመጠገን የተደረጉ ጥረቶችንም የሚያካትት ሲሆን፤ ተግባሩም በትውልድ ላይ ለሚሠራው ሥራ መሠረት የሚጥል መሆኑ እሙን ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ፣ የመንግሥትን የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን ከማሳለጥ እና ዜጎች በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ላይ ያላቸውን ቅሬታ በመቀነስ ርካታን የማሳደግ ግብን ይዘው እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትም ሌላው ተጠቃሽ ጅምር ተግባራት ናቸው። በዚህ በኩል፣ መንግሥት የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዜጎች ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሠራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ለዚህም፣ ችግሮችን በጥናት ለይቶ በቴክኖሎጂ ታግዞ ከመሥራት አኳያ የተጀመሩ እና ወደ ተግባር እየተገባባቸው ስለመሆኑ አመላካቾች አሉ።

ከእነዚህ መካከል አንዱ እና የበዙ ችግሮችን ይፈታል፤ የዜጎችን ቅሬታም ቀርፎ ርካታን ያሳድጋል የተባለለት፣ “መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት” ነው።

ይሄው ማዕከል በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ እና 12 ተቋማትን (የብሄራዊ መታወቂያ አገልግሎት፣ የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የትምሀርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት፣ የኢትዮ ፖስታ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮምን) አቅፎ ወደ ሥራ እንዲገባ ሆኗል።

የማዕከሉን ወደ ሥራ መግባት አስመልክቶም፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ይኽን አዲስ ማዕከል የሚገልጡ ሶስት ቁልፍ አላባውያን አሉ። የቆየ እና የተጎዳ ሕንፃን ወደ ዘመናዊ እና ሥነውበታዊ ደረጃው ለሥራ ከባቢ አስደሳች ወደ ሆነ ሕንፃ መለወጡ አንዱ ነው። አገልግሎቶችን ለማስተሳሰር እና ለማቀናጀት በሀገር ውስጥ የለማ ሶፍትዌር በሥራ ላይ መዋሉ ብሎም በታደሰ አመለካከት ብቁ እና ክብር የሞላበት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች መዘጋጀታቸው ሌሎቹ አላባውያን ናቸው። 12 ተቋማት በአንድ ጣሪያ ሥር 40 የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የጀመሩ ሲሆን፤ ይኼም ዜጎች ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ እና አገልግሎቶችን በተሻለ ውጤታማ መንገድ ለማግኘት ያግዛል።” ብለዋል።

አያይዘውም፣ እንደዚህ ያሉ ሥርዓቶችን ማበልፀግ ለዜጎች የተለያዩ የአገልግሎት ርካታ መታጣቶች ምላሽ በመስጠት በሂደት ለሰፊው ማኅበረሰብ ርካታ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል። የዛሬው ምረቃ ትልቅ ርምጃ መራመዳችንን ያሳያል። ኢትዮጵያ በዚህ ማዕከል ላይ ጨምራ እና አስፋፍታ ለዜጎች ሁሉ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥን ታረጋግጣለች፤ ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ እንደ ሀገር በሁሉም አካባቢዎች እየተከናወኑ ካሉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች መካከል ደግሞ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ልናነሳው የሚገባን ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ሁሉም ሥራዎች ለኢትዮጵያ ብልፅግና፤ ለኢትዮጵያውያንም ልዕልና የየራሳቸው የማይተካ ሚና አላቸው።

የኮሪዶር ልማት ሥራዎቹም በሁሉም ቦታ ሲተገበሩ፤ ማዕከላቸው ሰው ነው፤ ዓላማቸውም የሰዎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤ የኢትዮጵያንም መልክና ውበት መግለጥ ነው። በዚህ በኩል አያሌ ሥራዎች ተከናውነዋል። ይሄን ማዕከል አድርጎ የተከናወነው የኮሪዶር ልማት፣ ጥንታዊቷን ሐረር በከፍታ እንድትገለጥ አስችሏል። የአባ ጅፋሯን ጅማ፣ የላቀ ገጽታ አላብሷል። የታሪክና ባሕል ማዕከል የሆኑትን ጎንደርና ባሕርዳርን የውበት ሰገነት አጎናጽፏል።

የአዲስ አበባ ጎስቋላ መንደሮችና ሰፈሮች እንደ አዲስ እንዲወለዱ አድርጓል። አዲስ አበቤዎች ከተማቸው በስሟ ልክ ሆና እንዲመለከቱም፤ የውበቷ ተመልካች ብቻም ሳይሆን በውበቷ ውስጥ ኖረው እንዲዋቡ፣ በውብ መንደሮቿ ውስጥ በሀሴት እንዲኖሩም እድል ሰጥቷል። የቆሸሹና የተበከሉ ወንዞቿ እንዲጠሩ፤ የወንዝ ዳርቻዎቿ ከቆሻሻ መጣያነት ወደ ውብ ማረፊያነትና ፓርክነት እንዲለወጡም አድርጓል። አዲስ አበባ በስም ብቻ ትኖርበት ከነበረው ሕይወቷ አላቅቆ፤ በግብርም አዲስ እና አበባ እንድትሆን፤ በዚህም የነዋሪዎቿን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያንን፣ የአፍሪካውያንን፣ አለፍ ሲልም የዓለምን ልብና ዓይን የማረከ ገጽታን እንድትጎናጸፍ አስችሏታል።

በዚህ ረገድ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተሠሩ የኮሪዶር እና የወንዝ ዳር ልማት ሥራዎች አያሌ ውጤት የታየባቸው ናቸው። የፒያሳ፣ የአራት ኪሎ፣ የቀበና፣ የሜክሲኮና ሌሎችም አካባቢዎች ደግሞ የኮሪዶር ልማቱ ተግባራት ትሩፋት በጉልህ የተገለጠባቸው አብነቶች ናቸው። በሁለተኛው ምዕራፍ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ የኮሪዶር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶችም በላቀ ከፍታ እየተገለጡ ናቸው።

የካዛንቺስ የኮሪዶር ልማት ሥራ የዚህ አንዱ አብነት ሲሆን፤ በዚህ ሥራ ካዛንቺስ ጎስቋላ ገጿን ቀይራ እንደ አዲስ የተወለደችበትና የተሞሸረችበትን እውነታን መመልከት ችለናል። ከሰሞኑ የተገለጠው የቡልቡላ ፓርክ እና ተያያዥ የመንገድ ብሎም የወንዝ ዳር ልማት ሥራዎች ደግሞ፤ እነዚህን እንደ ከተማም እንደ ሀገርም የተከወኑ የውበትና ምቾት ተግባራት በአንድ ቦታ ተሰባስበው እንዲገለጡ ያስቻለ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዓመቱ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ስለመሆኑ አብነታዊ ማሳያዎች አንዱ ስለሆነው ቡልቡላ ፓርክ ሲናገሩ፤ “በተለያዩ መስኮች እያከናወንን ያለነው የተቋም ግንባታ እና ልማት ጥረታችን የሀገራችን ማንሰራራት ግልፅ ምልክት ነው። ይኼ ስኬት በሁሉም መስኮች እየታየ ነው። የዚህ ስኬት አስገራሚ ምልክት የቡልቡላ ፓርክ ነው። በአንድ ወቅት የቆሻሻ መጣያ የነበረ ሥፍራ በጥቂት ወራት ውስጥ ዋጋው ከፍ ወዳለ የሕዝብ መጠቀሚያ ተቀይሯል።” በማለት ነበር በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ያሰፈሩት።

አያይዘውም፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ አመራሮች በራሳቸው ተነሳሽነት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ብሎም ማኅበረሰቡን በማስተባበር አስደናቂ ሥራ ስለመሥራታቸው በመጥቀስ፤ የባለቤትነት መንፈሱ እና ቀድመው አስበው የመሥራት ተነሳሽነታቸው በሁሉም ዘርፍ መቀዳት ያለበት ስለመሆኑም አሳስበዋል። በሥፍራው የፈሰሰው ሀብትም የዛሬውንም የነገውንም ትውልድ ያገለግላልና የአካባቢው ነዋሪ እንዲንከባከበው ጥሪ አቅርበዋል። ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ጅምር ጥረቱን በተቀሩት የከተማዋ እና የኢትዮጵያ ክፍሎች አሳድገው እንዲተገብሩ አደራ ብለዋል።

እርግጥ ነው፣ ይሄ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ምስጋና፣ አደራና ጥሪ፤ ከዛሬ ባለፈ ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ፣ ስለ ነገው ትውልድ የተሻለ ነገርን ከማለም የመነጨ ነው። ለሀገሩ እድገትን፣ ለልጆቹና ለመጪው ትውልድም ምቾትን አለመመኘት ደግሞ አይቻልም። ይሄን የማይመኝ ካለም ከጤነኝነት የሚመነጭ እንደማይሆን ይታሰባል።

እናም ዓመቱ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ማሳያ የሆኑ በርካታ ተግባራት ቢኖሩም፤ የእነዚህ ድምር ውጤት በቡልቡላ ፓርክ መስታወትነት እንዲገለጥ ሆኗል። ይሄ ተግባር ደግሞ በእርግጥ የሚያስመሰግን ተግባር ነው። ይሁን እንጂ እንደ ከተማም፣ እንደ ሀገርም ካለው ዘርፈ ብዙ ችግርና ፍላጎት አኳያ ከዚህ የላቁ በርካታ ጉዳዮችን አስቦ የመሥራት መነሳሳትን የሚፈጥር እንጂ የሚያኩራራና ሥራዬን ጨረስኩ ብሎ የሚያስተኛ አይደለም።

እናም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ተግባራት፤ እንደ ሀገር የማንሰራራት ጊዜን አመላካች ከሆኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በሐረር፣ በጎንደር፣ በባሕርዳር፣ በጅማ፣ በድሬ ዳዋ እና ሌሎችም ከተሞች የተሠሩት ሥራዎች ሲገጣጠሙም ሀገራዊ ስዕል መፍጠራቸው እሙን ነው።

እንደ ቡልቡላ ፓርክ አይነት ትናትን የቆሻሻ ማኖሪያ የነበሩ ሥፍራዎች የሚፈጥሩት ስሜትና መነሳሳት ደግሞ፤ ዓመቱ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ስለመሆኑ በአብነት የሚቀርቡ ሥራዎች ማንጸሪያ አውድ፤ ማሳያና መግለጫ መስታወት ሆኖ የሚነገርለት ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ስኬቶች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ፤ ማበረታቻዎች እንጂ ፍጻሜዎች አለመሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው።

በየኔነው ስሻው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You