ፌዴሬሽኑና ዩኒቨርሲቲው በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን በጥናትና ምርምር፣ በትምህርት ባለሙያዎች አቅም ግንባታ እና ስልጠናዎች ላይ ለመሥራት ከኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት አድርጓል። ስምምነቱ የባሕል ስፖርቶችን በኅብረተሰቡ ዘንድ ተዘውታሪ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተጠቁሟል።

በበርካታ ባሕልና እሴቶች የታደለችው ኢትዮጵያ በየአካባቢው የሚከወኑ በርካታ ባሕላዊ ጨዋታዎች አሏት። የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽንም ከእነዚህ ባሕላዊ ጨዋታዎች መካከል 11ዱን ለይቶ ሕግና ደንብ በማዘጋጀት ውድድር ያካሂድባቸዋል። ለእዚህም ከትምህርት ተቋማት ጋር በመጣመር ትውልዱ እንዲያውቃቸውና እንዲያዘወትራቸው በጋራ ይሠራል። አሁን ደግሞ በጥናትና ምርምር፣ በትምህርት ባለሙያዎች አቅም ግንባታ እና ስልጠናዎች ላይ ለመሥራት የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነት ከኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር አከናውኗል። ፌዴሬሽኑ ካለበት የኢትዮጵያ የባሕል ስፖርቶችን የማጥናት፣ የማልማት፣ እንዲዘወተሩ የማድረግና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቅ ለማድረግ ካለበት ተልዕኮ አንጻር ስምምነቱ ከፍተኛ አተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተመላክቷል።

ከዘመናዊነትና የከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የባሕል ጨዋታዎች ተዘውታሪነት በትውልዱ ዘንድ እየተቀዛቀዘ መምጣቱ ይታወቃል። በመሆኑም ስፖርቶቹ ታውቀው ኅብረተሰቡ በስፋት እንዲሳተፍባቸው ለማድረግ ጥናት መሠረታዊ ነገር በመሆኑ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናል። ከእነዚህ መካከል ከአንደኛ ደረጃ አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ትምህርት እንዲካተት ጥረት ማድረግ ነው። በእዚህም ታዳጊዎች ባሕላዊ እሴቶቻቸውን እንዲያውቁና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል። በይበልጥ ጥናት በማከናወን እና የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር መቀናጀት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። በመሆኑም ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተከናወነው ስምምነት የባሕል ስፖርቶችን በኅብረተሰቡ ዘንድ ተዘውታሪ በማድረግ ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው።

ከእዚህ ቀደም መሰል ሥራዎች የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስፖርት ማህበር እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ጋር የተለያዩ ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም ወጥ በሆነ መልኩ እንዳልነበር የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ህይወት መሃመድ ጠቁመዋል። በመሆኑም ስትራቴጂያዊ እቅድ በማዘጋጀት በጥናትና ምርምር የካበተ ልምድ ካለው የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥናትና ምርምር፣ በትምህርት፣ በሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ፣ የባህል ስፖርትን ከአካል ብቃት ጋር በማስተሳሰር እንዲሁም በአቅም ግንባታ ሥልጠና ላይ ለመሥራት ይቻላል። ይኸውም ያሉትን ስፖርቶች በማሳደግ፣ ወደ ውድድር ያልገቡ የባህል ስፖርቶችን በማጥናት እንዲሁም የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ ለማድረግ ያስችላል።

የባሕል ስፖርቶችን ለማሳደግና ተዘውታሪ ለማድረግ በሥርዓተ ትምህርት እንዲካተት ከማድረግ ጎን ለጎን በፕሮጀክቶች በማካተት ታዳጊዎችን እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑና እንደ ኦሮሚያ፣ አማራና አዲስ አበባ ያሉ ክልሎች ደግሞ ጥሩ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ፕሬዚዳንቷ አመልክተዋል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትምህርቱ ባሻገር በውድድሮቻቸው እንዲካተት፣ በትምህርት ቤቶች ሊግም አንዱ የውድድር ዘርፍ እንዲሆንና ፌዴሬሽኑም የሚያዘጋጃቸውን ውድድሮች ለማስፋት እየሠራ ነው። ይሁንና ትውልዱ አሁንም ከባሕል ስፖርቶች ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ለዘመናዊ ስፖርቶች እንደመሆኑ ፌዴሬሽኑ በሚጠበቅበት ልክ እየሠራ አለመሆኑን ያሳያል። ስለዚህም ኅብረተሰቡ ስፖርቱን እንዲያውቅ የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠርና ውድድሮችን ለማብዛት ታቅዷል።

በእዚህም መሠረት በቀጣይ በባሕል ስፖርት ከተመዘገቡ ውድድሮች መካከል የተወሰኑትን በመለየት (በመከፋፈል) ለማብዛት የታቀደ ሲሆን፤ የቀስትና የኩርቦ በወንድ፣ በሴትና በድብልቅ በቀጣዩ ግንቦት ወር 2017ዓ.ም ውድድር ለማካሄድ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው። ስልጠናዎችንም ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ የባሕል ስፖርት ትምህርት ለሚሰጡ መምህራን የሚሰጥ ይሆናል። በተያዘው ዓመት በዳኝነትና በአሰልጣኝነት ሁለተኛ ደረጃ ስልጠና ለመስጠትም ታቅዷል። በምሥራቅ አፍሪካ የባሕል ስፖርቶች ፌስቲቫል በማዘጋጀት ማስተዋወቅም በረጅም ጊዜ የተያዘ እቅድ ነው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You