የቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና ጥራትና ጣዕም መቆጣጠሪያ ማዕከል ባለሞያዋ ወይዘሮ ኑሪያ ጀማል ይህ ሀገራዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ እንደሚካሄድበት ከሰሙም ሰነባብተዋል። ባለፉት ጥቂት ወራቶች ባጋጠማቸው የኩላሊት ህመም ምክንያት ከሥራ ፍቃድ ጠይቀው ራሳቸውን ሲያስታምሙ ቆይተዋል።
የችግኝ ተከላ ጥሪውን ከሰሙ አንስቶም በችግኝ ተከላው እንደ ሌሎቹ ዜጎች ሁሉ እርሳቸውም ቢያንስ አንድ ችግኝ በመተክል የራሳቸውን አሻራ ለማስቀመጥ ሲብሰለሰሉ ነው የከረሙት።
አይደረስ የለ ችግኝ የመትከያ ቀኑ ደርሰ፤ይሁንና ይህን አላማቸውን ለማሳካት በአንድ ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለ አቋም መያዝ እንዳለባቸው ያምናሉ። ይኸውም የገጠማቸውን ሕመም ተቋቁመው መስሪያ ቤታቸውን በመወከል በችግኝ መርሐግብሩ መካፈል ነበር። እንዳሉትም ወሰኑ።
የችግኝ ተከላው የሚካሄድበት አካባቢ በኦሮሚያ ልዩ ዞን አቃቂ ወረዳ ቢሊቢሎ ተራራ ላይ በመሆኑ ከሕመማቸው ጋር ተዳምሮ ለእርሳቸው አደገኛ መሆኑ በሥራ ባልደረቦቻቸው ቢነገራቸውም አሻፈረኝ ብለው ማለዳ በቦታው ላይ በመገኘት ተራራውን መውጣት ተያያዙት። እንዳሰቡትም በቀላሉ ተራራው ሊገፋላቸው አልቻለም። እያረፉ ጉዟቸውን ቀጠሉ። ከሕመማቸው ጋር ትንቅንቅ ገቡ። የኋላ ኋላ ግን እንደምንም የተራራው አጋማሽ ላይ ደረሱ።
በጆሮ ግንዳቸው የሚንቆረቆረውን ላባቸውን በሻርፓቸው እየጠረጉ ለችግኝ መትከያ ወደተዘጋጁት ጉድጓዶች አጠገብ ደረሱ። ፊታቸው በፈገግታ ተሞላ። ትንሽ ትንፋሽ ወስደው በእጃቸው የያዟትን ችግኝ ተከሉ፤ አላማቸውንም አሳኩ። ከዚህ በኋላም በችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ሆነ በእንክብካቤ ለመሳተፍ ለራሳቸው ቃል ገቡ። እንዲህ ነው ከቆረጡ!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 23/2011
አስናቀ ፀጋዬ