የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ያስተላለፉትን መልዕክት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞ ላይ ናት፡፡ በለውጥ ጉዞ ላይ ናት ስንል የሚለወጥ ነገር አላት ማለታችን ነው፡፡ ከሚለወጡት ነገሮቻችን አንዱ የዜጎች የሰብአዊ መብት አያያዝ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ ታግለው የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ ካደረጉባቸው ምክንያቶች አንዱ ሰብአዊ መብታቸውን የሚያከብር ሥርዓት ለማስፈን ነበር፡፡ የሰብአዊ መብት አያያዝም ሆነ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመሠረታዊነት እውን ሊሆኑ የሚችሉት በግለሰቦች ፍላጎት መመራቱ ቀርቶ የጋራ ፍላጎታችን በወለዳቸው ተቋማት መመራት ሲጀመር ነው፡፡ ተአማኒ የሆኑ የዴሞክራሲያዊና የፍትሕ ተቋማት ባልተ መሠረቱበት ሁኔታ ግለሰቦች እንዳሻቸው ሲሆኑ መመልከት በታሪኩ በተደጋጋሚ ለተመለከተው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ አይሆንም፡፡
ሕዝባችን ሁልጊዜም ቢሆን አምባገነናዊ ሥርዓትን ለመገርሰስ ሲታገልና መስዋዕት ሲሆን ግፍ እንዲቆም፣ ፍትሕ እንዲሰፍን እንጂ ሌሎች ግፈኞችን ለመተካት አይደለም፡፡ በሕዝብ ትግል ሥልጣን ላይ የወጡ አካላት ግን ከራሳቸው ፍላጎት ውጪ የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም፡፡ ሕዝቡ ከነገ ዛሬ ይሻሻላል ብሎ በትእግሥት ቢጠብቅም፤ በተደጋጋሚ ድምፁንም ቢያሰማም ችግሩ ግን ከመሻሻል ይልቅ እየባሰ መጣ፡፡ በተለይም የዴሞክራሲ ምህዳሩ እየጠበበ፣ ዜጎች በብሔራቸውና በያዙት የፖለቲካ አስተሳሰብ ምክንያት የሚደርስባቸው በደል እየከፋ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እየባሰ፣ ሙስናው ሀገሪቱን እስከ አንገቷ እየዋጣት መጣ፡፡ ሕዝባችንን እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በደልና ግፍ በቃን ብሎ እንዲነሣ ያደረጉትም እነዚህ መከራዎች ነበሩ፡፡
ግፍ በአገር ሲናኝ፣ ኩበት ሰጥሞ ድንጋይ ይዋኝ እንደሚባለው ሀገር የሚዘርፉ ጁንታዎች በኩራት በከተሞቻችን እየተንፈላሰሱ፣ ሕግ ያልፈረደባቸው ዜጎቻችን ተፈጥሯዊ የሆኑትን መብቶቻቸውን በመጠቀማቸው ብቻ፣ውሃ ውሃ የሚያሰኝ ግፍ ይፈጸምባቸው ጀመር፡፡ በሀብት፣ በንብረትና በፖለቲካ ተሳትፎ ከሚሠራው ግፍ በባሰ በዜጎች ሰብአዊ መብት ላይ የሚሠራው ግፍ ምነው ባልተወለድኩ የሚያሰኝ ሆነ፡፡ በፖሊስ፣ በደኅንነት፣ በፍርድ ቤቶች፣ በማረሚያ ቤቶችና በሌሎችም የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ በሚገኙ ባለሥልጣናት ፈቃጅነትና መሪነት፣ ኅሊናቸውን ሸጠው ለሆዳቸው ባደሩ የግፍ ሠራዊት ተላላኪነት በዜጎቻችን ላይ አራዊት የማይፈጽሙት ሰቆቃ ይወርድባቸው ነበር፡፡ ግፍ ፈጻሚዎቹ ከሳሽም፣ ምስክርም፣ መርማሪም፣ አሣሪም፣ ዐቃቤ ሕግም፣ ዳኛም፣ ሆነው የግፉን ድራማ ተውነውታል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለምን በጎ አስተሳሰብ የቀረጹት የሦስቱ ታላላቅ እምነቶች፡- የክርስትና፣ የእስልምናና የይሁዲነት ሀገር ናት፡፡ ኣብዛኛው ሕዝባችን ሃይማኖተኛ ነው፡፡ ለሞራል ድንጋጌዎች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ ማኅበረሰብ አለን፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች እንዴት ነው ይሄንን ሁሉ ግፍ ሊፈጽሙ የቻሉት? እነዚህ ሰዎች ማኅበረሰባችንን ቢወክሉ ኖሮ ሊያጠፉ ቢችሉ እንኳን እንዲህ ግፍ በልተው ግፍ ባልተነፈሱ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ሰውነትንም አይወክሉም፡፡ ስግብ ግብነት፣ አምባገነንነትና የሥልጣን ጥማት ጫፍ ላይ ሲደርሱ ሰውን ወደ አውሬነት እንዴት እንደሚቀይሩት ማሳያ ናቸው፡፡
አሁን ወሳኙ ጥያቄ ምን እናድርግ? የሚለው ነው፡፡ መልሱ ሦስት ነው፡፡ የመጀመሪያው ግፈኞች የግፋቸውን ዋጋ በሕግ እንዲቀበሉ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፍርድ ለልጅ፣ ጥራጊ ለደጅ ይተርፋል እንዲሉ ይህ ግፍ በልጅ ልጆቻችን ዳግም እንዳይፈጸም የሚያደርግ አስተማማኝ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ሦስተኛው ከእነርሱ የተሻልን መሆናችንን በተግባር ማሳየት ነው::
ግፈኞች ግፍ ፈጽመው በሰላም ተኝተው እንዲያድሩ መፍቀድ የለብንም፡፡ እነርሱ ያንን ሁሉ ግፍ ፈጽመው ምንም ሳይመስላቸው በልተው የሚጠግቡ፣ ተኝተው የሚያድሩ ሆነዋል፡፡ እኛ ግን ግፉ ይሰቀጥጠናል፣ ያመናል፣ ዕረፍትም ይነሣናል፡፡ በተለይ ደግሞ የተፈጸመው በአንድ በኩል በዜጎቻችን ላይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በማናውቀው ሁኔታ በየመንደራችን በሚገኙ ድብቅ እሥር ቤቶች መሆኑን ስናውቅ ሕመሙ ይብስብናል፡፡ በሕዝባችንም ላይ ይህ አሰቃቂ ግፍ ማንም የማይረሳውን ጠባሳ ጥሎ ያልፋል፡፡ ስለዚህም ይህን ግፍ የፈጸሙ ሁሉ በሕግ ፊት ተገቢውን ቅጣት አግኝተው ተተኪዎቹ ትምህርት፣ ተጎጂዎቹም የኅሊና ዕረፍት እንዲያገኙማድረግ አለብን፡፡ እኛ ባንይዛቸው እንኳን የእነዚያ ንጹሐን ደም ካሉበት ይዞ ያመጣቸዋል፡፡
ይህ የእነርሱ አረመኔያዊነት ፈጽሞ መደገም የለበትም፡፡ እነርሱ ስለተቀጡና እኛ ስለተቆጨን ብቻ ግን ከመደገም አናስቀ ረውም፡፡ ይህንን ግፍ የፈጠሩትን ቀዳዳዎች መድፈን፣ ሕጎችን ማሻሻል፣ አሠራሮችን ማስተካከል፣ ተቋማትን ማብቃት፣ የዝርፊያንና የአምባገነንነት በሮችን መዝጋት አለብን፡፡ አሁን እያከናወንናቸው በሚገኙ የሪፎርም ሥራዎች ጠንክረን መግፋት ያለብን ለዚህ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎችን ዴሞክራ ሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶችን በሚገባ የሚያከብርና የሚያስከብር ሥርዓት መገንባት አለብን፡፡ በፍርድ ቤቶቻችን፣ በምርጫ ቦርድ፣ በሚዲያ ተቋሞቻችን፣ በመከላከያና በደኅንነት ተቋማት፣ በፖሊስና በማረሚያ ቤቶች፣ እየወሰድናቸው የሚገኙ ማሻሻያዎች ዓላማቸው ይሄንን ዘላቂ ሥርዓት እውን ለማድረግ ነው፡፡ ለወደፊቱም በሌሎች ተቋማት ላይ ማሻሻያው ይቀጥላል፡፡
ይህን ግፍ የፈጸሙ ሰዎች በሄዱበትም ሆነ እኛ እንድንሄድ በሚፈልጉት መንገድ መጓዝ የለብንም፡፡ እነዚህ ሦስቱ መርሆአችን ሊሆን ይገባል፡፡ ግፈኞች በጥላቻ ተሞልተው ይኼንን ሁሉ ፈጸሙ፡፡ እኛ ግን ጥላቻቸውን መውረስ የለብንም፡፡ ግፈኞች በጭፍን አእምሮ ይሄን ሁሉ ግፍ በወገናቸው ላይ አዘነቡ፤ የእኛን አእምሮ ግን በበቀል እንዲጨፈን ማድረግ የለባቸውም፡፡ ግፈኞች ሕግን የማያከብሩ፣ ፈጣሪን የማይፈሩ ሆነው የመከራ ዶፍ በሕዝባቸው ላይ አወረዱ፤ እኛ ግን ፈጣሪን እንፈራለን፤ ሕግንም እናከ ብራለን፡፡
በምንም መልኩ ግፈኞቹ ራሳቸውን እንጂ፣ ግፈኞቹ የበቀሉበትን ሕዝብ ግፋቸው እንደማይመለከተው እናምናለን፡፡ የትኛውም ብሔር ወይም የትኛውም ዘር ግፈኞችን፣ ገራፊዎችንና ጨቋኞችን ሊያበቅሉ ይችላሉ፡፡ አንድ ብሳና ባጠፋ ጫካውን ሁሉ እንደ ማንቀየመው፣ ግለሰቦች ባጠፉ የምንቀየመው ወይም ጣት የምንቀስርበት ብሔር አይኖርም፡፡ አብዲሳ አጋን፣ ጸጋዬ ገብረ መድኅንን ወይም ታደሰ ብሩን ያፈራው የኦሮሞ ሕዝብ ጽዩፍ የሆኑ እኩያንን የማያበቅልበት፤ ጀግናው አሉላ አባ ነጋን ወይም ማኅሌታይ ያሬድን ለሀገር ያበረከተው የትግራይ ሕዝብ ታሪክ የማይረሳው በደል የፈጸሙ ወንጀለኞችን የማያፈራበት፤ እነ ቴዎድሮስን፣ በላይ ዘለቀን ወይም ገብርዬን የሸለመው አማራ ሌሎች ግፈኞችን ከውስጡ ሊያስገኝ የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ወንጀለኛ ራሱን ችሎ ወንጀለኛ ለመሆን ከምንም ጋር መለጠፍ እና ማንም ላይ መደገፍ አያስፈልገውም፡፡
ወንጀለኛ እንዲሁ በቁሙ ወንጀለኛ ነው፡፡ ግፍ የሠራው ሰው የሚናገረው ቋንቋ ኦሮሚኛ ቢሆን ኦሮሞውን፣ ትግሪኛ ቢናገር ትግሬውን፣ ከአማራ ክልል ሲወለድ አማራውን፣ ከሲዳማ ሲመጣ ሲዳማውን የሚወቅስ ሰው ካለ እሱ ከታሪክ የማይማር ደካማ ነው፡፡ እኛ ታሪካችንን በሚገባ የምንረዳና ነጋችንን ለማቅናት የምንተጋ እንጂ፣ ለአንድ ገጽ ብለን መጽሐፍ የምንቀድ ሞኞች አይደለንም፡፡ ትናትም ሆነ ዛሬ፣ ነገም ወደፊትም ወንጀለኞች መፈጠራቸው አይቀርም፡፡ ሁሌም ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር፣ ወንጀለኞቹን ሊደበቁበት ከሚፈልጉት ብሔር ነጥለን ማየትና እስከ መጨረሻው ለፍርድ ማቅረብ እንደ ሚገባን ነው፡፡ እነርሱ ሊደበቁበት የሚፈልጉት ብሔር በምንም መንገድ የእነርሱን ግፍ ተመልክቶ የሚያለቅስ እንጂ ለእነርሱ ግፍ የሚያጨ በጭብ ነው ብለን አናምንም፡፡ ይህ ምንጊዜም የማይቀየር አቋማችን መሆን አለበት፡፡ ፈጽሞ የእነርሱን ስሕተት አንደግመውም፤ ፈጽሞም በቀደዱልን ቦይ አንፈስስም፡፡ እነርሱ እንደ እኛ እንዲሆኑ እንፈልጋለን እንጂ፣ እኛ እንደነርሱ አንሆንም፡፡
ቂምና በቀልን ልናስበው አይገባም፤ ፍርድና ፍትሕን እንጂ፡፡ ይህን ሁሉ የምናደርገው እንደነርሱ ከጥላቻ ተነሥተን ሳይሆን የሕግ የበላይነት መስፈን ስላለበት ነው፡፡ እንዳይደገም ስለምንፈልግ ነው፡፡ ሌሎች ትምህርት እንዲያገኙ ስለምንሻ ነው፤ ያንን የግፍ ታሪክ መዝጋት ስላለብን ነው፡፡
ወንጀለኞቹ ማንም ይሁኑ ማን፣ ከየትኛውም ብሔር ገብተው ይደበቁ፣ የትኛውም ወገን ይጩህላቸው፣ በወንጀል እስከተጠረጠሩ ድረስ ካሉበት አድነን ለሕግ ማቅረባችን ግን አይቀሬ ነው፡፡ ሀገራዊ ወሰንም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ድንበር ወንጀለኞችን ለፍርድ ከመቅረብ አይታደጋ ቸውም፡፡ ለዚህ መንግሥት ቁርጠኛ ነው፡፡ በአንድ በኩል ራሳችንን ከወጥመዳቸው እየተከላከልን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ግፈኞች ፍትሕ እንዲያገኙ መሥራታችንን እንቀጥ ላለን፡፡ ግፍ ሠርቶ መደበቅ፣ ዘርፎ መንደላቀቅ አይቻልምና፡፡
ከእንግዲህ እምነታችን በግለሰቦች ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን በጠንካራና ተአማኒ ተቋማት ላይ ነው፡፡ ግለሰቦች፣ ፍላጎታቸውና ጠባያቸው እንደየጊዜው ተቀያያሪ መሆኑን በታሪካችን ከበቂ በላይ ተጽፏል፡፡ አሁን አዲስ ታሪክ መጻፍ ይገባናል፤ ያስፈልገ ናልም፡፡ ሙሉ አቅማችንን ማፍሰስ የሚገባን የሁላችንም ፍላጎት ተቀናጅቶ በሚፈጥራቸው ጠንካራ ተቋማት ላይ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተቋማት ዘላቂና በጊዜ ሂደት የማይቀያየሩ፣ ሰቆቃን የሚያስቀሩ፣ ሁላችንንም እኩል የሚያይ ሥርዓት የሚዘረጉ እንጂ ለግለሰቦች ፍላጎት የሚገዙ አይደሉም፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና ኅብረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ታኅሣሥ 3፣ 2011 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011