ባህላዊ ምግቦች የእንግዶች መቀበያ፤ የቤተሰብ፣ የጎረቤት፣ የጓደኛ መገባበዣ፤ ከሀገር ወጥቶ የሚኖር ኢትዮጵያዊን በትዝታ መመለሻ ናቸው። እናም እነዚህን ባህላዊ የምግብ ማህደራችንን ልንገልጥ ለዛሬው የትግራይ ክልልን መረጥን።
በትግራይ ባህላዊ ምግቦች ስራ ላይ ተሰማርታለች፤ውልደቷም ሆነ እድገቷ በዚያው ነው ወይዘሪት አዝመራ የማነ፤ ከእናት፤ አያትና ቅድመአያቶች ሲወርድ ሲወሰረድ የመጣውን ባህላዊ የምግብ አሰራር እሷም እያስቀጠለች ትገኛለች፤ የባህላዊ ምግብ አዘገጃጀቶችን እንዲህ ስትል ታስረዳለች። ወይዘሪት አዝመራ እንደነገረችን፤ ህልበት ምንም እንኳን በአክሱሞች ዘንድ በስፋት ቢታወቅም የትግራይ መገለጫ ነውና ማንኛዋም እንስት የምትሰራው ባህላዊ ምግብ ነው።
ስለዚህም እናቶች ይህንን ባህላዊ የምግብ አሰራር በሚገባ ለልጆቻቸው ያስተምራሉ። “እኔም በትግራይ ውስጥ አሉ የተባሉ ባህላዊ ምግቦች አሰራርን ተክኛለሁ” ትላለች። እናም የህልበት አሰራርንም ከእናቷ በለመደችው መሰረት እንዴት እንደሚሰራ እንዲህ ታብራራለች።
ህልበት
ህልበት አክሱም አካባቢ በብዛት ለምግብነት የሚዘጋጅ ምግብ ነው። ብዙ ጊዜ የሚዘጋጀው ደግሞ ለጾም ሲሆን፤ ከባቄላ፣ ከምስርና ከአብሽ የሚዘጋጅ ነው። እነዚህ ጥሬ እህሎች ከሁለት ሳምንት በላይ ጸሐይ ሊያገኛቸው ይገባል። ምክንያቱም በሚገባ ደቀው እንዲፈጩ ምንም አይነት እርጥበት እንዲኖራቸው አይፈለግም። እናም ይህ ሁሉ ከተደረገ በኋላ ተቀላቅለው ይፈጫሉ። በደንብ ግን መላም ይኖርባቸዋል።
ከዚያ በመቀጠል ህልበቱ ለነገ የሚፈለግ ከሆነ ማታ ላይ እንደ አብሲት ቀጠን ተደርጎ ይሰራል። ይህ እንደአብሲት የሚሰራው ህልበት በሚገባ መንተክተክና በእሳት መመታት አለበት። ምክንያቱም ይህ ካልሆነ ሁለት አይነት ጣዕም ሊያመጣ ይችላል። የመጀመሪያው አብሲት አብሲት ማለት ሲሆን፤ ሁለተኛው ዱቄት ዱቄት ሊል ይችላል። ስለዚህ ትክክለኛውን የህልበቱን ጣዕም እንዲይዝ መንተክተኩ ግድ ነው። ከዚያ ቀዝቅዞ እንዲያድር ይደረጋል።
የቀዘቀዘው በአብሲት መልክ የተሰራው የህልበት ዱቄት ጠዋት ላይ ንጹህ ጎርጓዳ ሳህን ውስጥ ይደረግና እስኪነጣና ቀጠን እስኪል ድረስ ይመታል። ይህ አሰራር በጣም ጉልበት የሚጠይቅና ሴቶችን በሚገባ የሚፈትን ነው። ምክንያቱም ካልነጣና ካልተመታ አይጣፍጥም። እዚህ የተመታው ህልበት ላይ ጣዕሙ የበለጠ ጣፋጭ እንዲሆን የተለያዩ ቅመሞች ይጨመራሉ። ነጭ ሽንኩርትና ጨው ግን ግድ ናቸው። ከዚያ እንጀራ ላይ ይደረጋል። የህልበቱ አሰራር በዚህ መልኩ ከተጠናቀቀ በኋላ ብቻውን አይበላም ። ስለዚህም ማባያ መስራት ግዴታ ነው።
እንደ ወይዘሪት አዝምራ ገለጻ፤ ብዙ ጊዜ በትግራይ ባህል ያለተከታይ ማባያ ለምግብነት አይቀርብም። የህልበት ዋናው ማባያ ስልስ ነው ። ስለስ ዘወትር ከቲማትም እንደምንሰራው አይነት ነው። ስልሱ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ትንሽ ጨው ይጨመርበትና ክሽን ተደርጎ ይሰራል። የተለያዩ ማጣፈጫ ቅመሞችም ይጨመሩበታል። ከዚያ በትሪ እንጀራ ይቀርብና በላዩ ላይ የተሰራው ህልበት ይደረጋል። በመቀጠል እንደገንፎ መሀሉ ይከፈትና ለማባያነት የተዘጋጀው ስልስ ይጨመርበታል። ከዚያ ጣዕሙን እያጣጠሙ መመገብ ነው።
ጥህሎ
ወይዘሪት አዝመራ ይህ ሙያ ከእናቷ የተማረችው ብቻ እንዳልሆነ ትናገራለች። ከልጅነቷ ጀምሮ ደግሞ እየተመገበች። ሰዎች ሲሰሩ እና ለማን እንደሚቀርብ እያየች አድጋለች። ጥህሎ ለማንኛውም ሰው የሚቀርብ ምግብ ሳይሆን ትልልቅና የክብር እንግዳ በሚኖርበት ጊዜ ብቻ የሚቀርብ ባህላዊ ምግብ እንደሆነም ትናገራለች። ጥህሎ ለሰርግ፤ ለክርስትናና አጠቃላይ በደስታ ወቅት የሚዘጋጅ ባህላዊ ምግብ እንደሆነ ታስረዳለች።
ጥህሎ ከገብስ የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ገብሱ በሚገባ ተለቅሞ በሞቀ ውሃ ይነከራል። ከዚያ በወንፊት እየተጠለለ ይፈተጋል። በመቀጠል ገብስ ቢሆንም እንደ በሶ ሳይሆን እሳት ሳይገባው ለስለስ ተደርጎ ይቆላ እና ይፈተጋል። ምክንያቱም ጥህሎው ለስላሳ መሆን አለበት። ሆኖም በሚገባ ካልተፈተገ የገብሱ ገለባ ብዙም የሚሄድበት ሁኔታ ስለማይኖር ቀለሙንም ሆነ ጣዕሙን ይቀንሰዋል። እናም በሚገባ መፈተግን ይጠይቃል። ይህንን ሁሉ ሁኔታ ካለፈ በኋላ ይፈጫል።
ወይዘሪት አዝመራ እንደምትለው፤ የጥህሎ ዱቄት በማንኛዋም ትግሬ ሴት ቤት የማይጠፋ ባህላዊ ምግብ ነው። ምክንያቱም እንግዳ በድንገት ሊመጣ የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ከዱቄቱ በኋላ ያለውን አሰራር ማወቅ ያስፈልጋልና አዘገጃጀቱ እንዴት ነው ስንል ወይዘሪት አዝመራን መጠያየቁን ቀጠልን። አዘገጃጀቱ ዱቄቱ በቀዝቃዛ ውሃ ላላ ተደርጎ ይቦካል። በጣም መታሸትንም ይጠይቃል። ምክንያቱም ሲመገቡት አፍ ላይ የሚከብድ መሆን የለበትም።
ቡኬቱ የሚያስፈልገውን ያህል ጊዜ ወስዶ ሥራው ካለቀ በኋላ የትግራይ ባህላዊ እርቦ ላይ ይገለበጣል። ከዚያ ቆንጥሮ ለማድቦልቦል ይመች ዘንድ ውሃ በእጅ እየተነካ በእርቦው ላይ ሞልሞል ተደርጎ ይቀመጣል። ጥህሎ በባህሪው የብቻ ምግብ አይደለም። በህብረት የሚበላና ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር ባህላዊ ምግብ ነው። ስለዚህም በእርቦ ላይ ሞለል ተደርጎ የተቀመጠው ጥህሎ በትግራዮች ዘንድ በሚታወቀው ባህላዊ ገበቴ ወይም መሶብ ላይ ለበቂ ሰው የሚሆን እንጀራ ላይ አንዱ እንጀራ በአይኑ ተደፍቶ በላዩ ላይ እየተቆነጠረ እና እየተድቦለቦለ ይቀመጥበታል። ይሁን እንጂ ጥህሎ በእንጀራ የሚበላ አይደለም። ለእራሱ የተዘጋጀ ማባያም ሆነ መብያ መሳሪያ አለው።
ማባያው ሁለት አይነት ሲሆን፤ የመጀመሪያው ከቋንጣ፣ ዘይት፣ በርበሬ፣ ጨው፣ ነጭ ሽንኩርትና ቲማቲም ተከሽኖ የሚሰራ ነው።የተለያዩ ቅመሞችም ይታከሉበታል። ለአይን ሲታይ እጅ የሚያስቆረጥም ክሽን ያለ የዶሮ ወጥ ይመስላል። ሁለተኛው ማጣፈጫ ከእርጎ ወይም ከአሬራ የሚዘጋጅ ነው። የበሶ ዱቄትም ይጨመርበታል። ትንሽ በርበሬ፣ ነጭ ሽንኩርትም በላዩ ላይ ይታከልበታል። የተለያዩ ቅመሞችም ይጨመሩበታል።
በተለይም በባህሉ አጠራር ድቁስ እየተባለ የሚጠራውና ከጥቁር አዝሙድና ከጨው የሚዘጋጀው ቅመም ልዩ ጣዕም ይሰጠዋል ተብሎ ስለሚታመን እርሱ አይቀሬ ነው። ከዚያ በየተመጋቢው ፊት እየተድቦለቦለ ይቀመጣል። መሀሉ ላይ ደግሞ ማባያው በጣባ ይቀመጣል። መሃሉ እንደ ገንፎ ይከፈትና ሁለተኛው ማባያ ይደረባል። ቀጥሎ የሚሆነው በባህሉ «ሽንጣር» ተብሎ በሚጠራው ሹካ መሰል ከእንጨት የተሰራ መገልገያ መሳሪያን በመጠቀም ጥህሎውን እየወጉ ከፊት ለፊቱ በተቀመጠው ማባያ በማጥቀስ መመገብ ይጀመራል።
ጥህሎውን እያድቦለቦለች የምታስቀምጠው እንስት በምንም መልኩ በእጇ መብላት አይፈቀድላትም። ስለዚህ በባህሉ ዘንድ እንደማትበላ ስለሚታወቅ ሁሉም ያጎርሷታል። ነገር ግን ጥህሎው አልቆ እንጀራው ብቻ ሲቀር የጥህሎው ማባያ እንጀራው ላይ ስለሚዘረገፍ ሁሉም በህብረት ተሰብስበው እንዲበሉ ይሆናል። እርሷም እንጀራው ላይ በእጇ መሳተፍ ትችላለች። ምክንያቱም የክብር አስተናጋጅ መሆኗና የመጨረሻው ማዕድ የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን ለመንገር በማስፈለጉ ነው ስትል ታብራራለች።
ህብስት
ይህ ለአንድ አካባቢ ወይም ክልል የተሰጠ ልዩ ባህላዊ ምግብ አይደለም። ሆኖም በብዛት ትግራዮች ይታወቁበታልና አሰራሩን ልናገር የምትለው ወይዘሪት አዝመራ፤ ህብስት ብዙ አይነት የአገጋገር ስልቶች አሉት። ይሁንና በትግራይ አካባቢ የተለመደው የውሃ ዳቦ የምንለው ህብስት ነው። እናም የዚህ ህብስት ዝግጅት የሚጀምረው ውሃ በሳፋ ከማስቀመጥ ነው። ቀጥሎ ዘይት ይጨመርበታል። በመቀጠል ደግሞ ስኳር፣ ጨው፣ እርሾ፣ ቤኪንግ ፓውደር በመጨመር ከውሃው ጋር በደንብ ይቀላቀላል።
ፍርኖ ዱቄት ወይም የስንዴ ዱቄት ከዚያ ከተቀላቀለው ውሃ ውስጥ ይጨመራል። በሚገባ እየታሸ ይቆያል። ይህ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ ኩፍ እኪል ድረስ በንጹህ እቃ፣ ላስቲክ ሸፍነን እንጠብቃለን። ሊጡ ኩፍ ካለ በኋላ ደግሞ መጋገሪያው እንዳይዝ በዘይት ይቀባና ሊጡ ይገለበጣል። ይጠፈጠፍናም በቢላዋ እና በሹካ የተለያየ ቅርጽ ይወጣለታል።
ቀለም እንዲኖረው ከተፈለገ ደግሞ ትንሽ ሊጥ ላይ ቀለም እናደርግና እናቦካዋለን። ከዚያ በትንንሹ እየቆራረጥን የምንፈልገውን ቅርጽ በመስራት ህብስቱ ውበት እንዲኖረው ይደረጋል። ይህ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ውሃ በሰፊ ሳፋ እናፈላለን። ሊጡን ሊደግፍ የሚችል ማጥለያ በፈላው ውሃ ውስጥ እናስቀምጣለን። ከዚያ ያቦካነውንና ያስተካከልነውን ሊጥ እስከመጋገሪያው ማጥለያው ላይ እናደርገዋለን። ሀይል ባለው እሳት ሊጡ እስኪበስል ድረስ እናስመታዋለን። በመጨረሻ ቀስ አድርጎ በማውጣት ቀዝቀዝ ሲል መመገብ ነው።
ከትግራይ ባህላዊ ምግቦች እኛ በጥቂቱ አነሳን እንጂ ብዙ ባህላዊ ምግቦች ያሉባት ቦታ ነችና ጎብኟት በማለት ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው