በስምንት ወራት ከኢንዱስትሪው ዘርፍ 204 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ

በተኪ ምርቶች 2 ነጥብ 79 ቢሊዮን ዶላር ማዳን ተቻለ

አዲስ አበባ፡– ባለፉት ስምንት ወራት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በተሠራ ሥራ ወደተለያዩ ሀገራት ምርቶችን በመላክ 204 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድም 2 ነጥብ 79 ቢሊዮን ዶላር  ማስቀረት መቻሉን አመልክቷል።፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቦሉልታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በ2017 በጀት ዓመት አምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ በመደረጉ ባለፉት ስምንት ወራት ወደ 204 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ስምንት ወራት ጋር ሲነፃፃር 21 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ወይም 12 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

እንደሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ መንግሥት ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተለየ ትኩረት በመሰጠቱና በዘርፍ አንቀሳቃሾች የሚነሱ የመሬት፣ የፋይናንስ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎችም የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በተቀናጀና በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲመለሱ ሰፊ ርብርብ አድርጓል፡፡ በዋናነትም የኮቪድ 19 እና ዓለም አቀፍና ግጭቶች ባሳደሩት ጫና ምክንያት ዘርፉ ከገባበት አስቻጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለማውጣት ከፖሊሲ ማሻሻል ጀምሮ ምቹ መደላደል የሚፈጥሩ የአሠራር ሥርዓቶች ተነድፈው ተግባራዊ ተደርገዋል።

በዘርፉ ከፍተኛ እምርታ እንዲመዘገቡ ካደረጉ ሥራዎች መካከል ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› አንዱና ዋነኛው መሆኑን አንስተው፤ አሁን ላይ በዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት መፈጠሩን አመልክተዋል። በዚህም በ2014 ዓ.ም በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች ቁጥር 94 እንደነበር አስታውሰው፤ ኢንቨስትመንቱን ለመሳብ በተደረጉ ጥረቶች 2016 ዓ.ም ቁጥራቸውን ወደ 220 ማድረስ መቻሉን አስገንዝበዋል። በ2017 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት ደግሞ 130 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡

ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ባሻገር በርካታ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ዘርፉን መቀላቀላቸውን፤ ተሳትፏቸው አሁን ላይ በቁጥርም ሆነ በካፒታልም ደረጃ እያደገ መምጣቱን አቶ ታረቀኝ አስገንዝበዋል፡፡

በተመሳሳይ ሀገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታስገባቸውን የተለያዩ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ሰፊ ርብርብ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተው፤ ‹‹ይህም በመሆኑ በስምንት ወራት ውስጥ ብቻ 2 ነጥብ 79 ቢሊዮን ዶላር ማስቀረት ተችሏል›› ብለዋል፡፡ የሀገሪቱ ተኪ ምርቶች የገበያ ድርሻ ከአራት ዓመታት በፊት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 41 በመቶ ማደግ መቻሉን አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ከ2014 ዓ.ም 240 የሚጠጉ አምራች ኢንዱስትሪዎች የነበሩ ሲሆን 2016 ዓ.ም ላይ 899 የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ገብተዋል›› ብለዋል። ይህም በተለይም የኢኮኖሚ ሪፎርሙ መካሄዱ ከዚህ ቀደም ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎች በመፈታታቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው እንዲያመርቱ በመደረጉ በምርታማነት ላይ ተጨባጭ የሚባል ለውጥ ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በፓርኮቹ ከ50 በላይ የሚሆኑት ኢንቨስትመንቶች በኢትዮጵያውያን የተያዘ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም በተለይ ሀገሪቱ ተኪ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ለያዘችው የልማት ሥራና የሥራ እድል ፈጠራ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡

ይሁንና በዘርፉ የተመዘገበው እድገት አበረታች ቢሆንም ሀገሪቱ ካላት ሰፊ አቅም አኳያ አሁን ላይ ወደ ውጭ የምትልካቸው የኢንዱስትሪ ምርቶችና የምታገኘውም የውጭ ምንዛሬ በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል። ይህም በመሆኑ መንግሥት ከዘርፉ አንቀሳቃሾች ጋር ጥብቅ ቅንጅት በመፍጠር ቀጣይነት ባለው መልኩ ለዘርፉ እድገት የሚሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You