ሶማሊያ ለአሜሪካ ወደብ ለመስጠት ያቀረበችውን ሃሳብ ሶማሊላንድ ተቃወመች

ሶማሊላንድ የሶማሊያ መንግሥት በበርበራ የሚገኘውን ወደብ እና ወታደራዊ አየር ማረፊያ ለአሜሪካ ለመስጠት ያቀረበውን ሃሳብ ውድቅ አደረገች።

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሸህ ማህሙድ ከሁለት ሳምንታት በፊት ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፃፉት ደብዳቤ፣ ሀገራቸው በበርበራና በባሊዶግሌ የሚገኙ ወታደራዊ አየር ማረፊያዎችን እና የበርበራ እና ቦሳሶ ወደቦችን አሜሪካ በብቸኝነት እንድትቆጣጠራቸው ጠይቀዋል፡፡ ይህም የአሜሪካን የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን እንደሚያጠናክር መግለፃቸውን ሮይተርስ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲራህማን ዳሂር አደን የሞቃዲሾን ውሳኔ ‹‹ተስፋ የመቁረጥ ርምጃ›› በማለት አጣጥለውታል፡፡ ሚኒስትሩ ለሞቃዲሾ ደብዳቤ በኤክስ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ‹‹ለሶማሊላንድ የሚሰጠውን እውቅና ለማስቆም ማድረግ የሚችሉት ምንም ነገር የለም›› ብለዋል።

በቅርቡ ማስፋፊያ የተደረገለት የበርበራ ወደብ በሶማሊላንድ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ ላይ ይገኛል። ‹‹አሜሪካ ሞኝ አይደለችም፤ በርበራ ወደብን በሚመለከት ከማን ጋር መነጋገር እንዳለባት ታውቃለች›› በማለት ሚኒስትሩ ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡

በደብዳቤው ላይ የተገለፀው ሁለተኛው ወታደራዊ አየር ማረፊያ የሚገኘው ከዋና ከተማው ሞቃዲሾ በስተሰሜን ምዕራብ በኩል በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባሊዶግሌ ውስጥ ሲሆን፤ በስፍራው የሶማሊያ ወታደሮች አልሸባብን ለመዋጋት የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ የአሜሪካ ወታደሮች ሥልጠና እየሰጡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

ሌላዋ አሜሪካ በብቸኝነት እንድትቆጣጠራት በፕሬዚዳንት ሐሰን ሸህ ማህሙድ ደብዳቤ ላይ የተጠቀሰችው የቦሳሶ ወደብ ደግሞ ከፊል ራስ ገዝ በሆነችው ፑንትላንድ ትገኛለች። የፑንትላንድ ባለሥልጣናት በደብዳቤው ላይ እስካሁን አስተያየት ስለመስጠታቸው የተባለ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፣ የሞቃዲሾው መንግሥት ለአሜሪካ ደብዳቤውን የጻፈው የፑንትላንድ ባለሥልጣናትን ሳያማክር በመሆኑ የፑንትላንድ አስተዳደር በሞቃዲሾ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም በፑንትላንድ እና በሞቃዲሾ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ሊያሻከረው ይችላል ተብሏል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You