
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተለያዩ ርቀቶች በጅማ ከተማ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ያካሂዳል። ለመጀመሪያ ጊዜ በጅማ ከተማ እሁድ፤ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሚካሄደው “የኢትዮ ቴሌኮም ታላቁ ሩጫ በጅማ” ውድድር ምዝገባ መጀመሩም ታላቁ ሩጫ በላከው መግለጫ ጠቁሟል። ከአዲስ አበባ ለሚሄዱ ተሳታፊዎች በታላቁ ሩጫ ቢሮ እንዲሁም ለጅማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች በዳሸን ባንክ እና በቴሌ ብር አማካኝነት ምዝገባው እየተካሄደ ይገኛል።
ውድድሩ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በቅርቡ ያስተዋወቀው የ’’ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ” የተሰኘ በአራት ከተሞች የሚካሄድ ተከታታይ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር አካል ነው።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ የውድድሩን ዝግጅት በተመለከተ በመግለጫው እንደጠቆሙት፣ “የኢትዮ ቴሌኮም ታላቁ ጅማ ሩጫ” የአዋቂዎች የአስራ አምስት ኪሎ ሜትር እና የአምስት ኪሎ ሜትር እንዲሁም የህጻናት ሩጫ ውድድሮችን ያካተተ ነው።
መጋቢት 28 ለሚካሄደው የ 15 ኪሎ ሜትር ውድድር ከወዲሁ ከ12 የተለያዩ ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች መመዝገባቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጇ፣ በርካታ የቀድሞ የጅማ ነዋሪዎች እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ ብዙዎች ወደ ጅማ የሚጓዙበት ውድድር እንደሚሆን ገልፀዋል።
ውድድሩ ከሩጫው በተጨማሪ የሚድሮክ ሆራይዘን ፕላንቴሽን የቡና እርሻ እና የአባ ጅፋር ቤተመንግሥት ጉብኝት፣ የ 5.5 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ እና ሌሎች የመዝናኛ ዝግጅቶች የተካተቱበት ነው።
ውድድሩ በታሪካዊ ሥፍራዎቿ፣ በቡና እና የእንጨት ምርቶች ይበልጥ የምትታወቀው ጅማ ከተማን ተጨማሪ የሩጫ መዳረሻ ሥፍራ የሚያደርግ መሆኑንም ሥራ አስኪያጇ አክለዋል።
የዚሁ ውድድር አካል የሆነ የጎዳና ላይ ሩጫ ባለፈው የካቲት 02/2017 ዓም “የሃዋሳ ሐይቅ ግማሽ ማራቶን” በሚል ስያሜ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ የስምንት ኪሎ ሜትር የጤና ሯጮች ውድድርም ተካሂዷል። ከ24 ሀገራት የተውጣጡ ከ500 በላይ የሚሆኑ ለመዝናናት የሚሮጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ተሳታፊዎች ነበሩ። በ21 ኪሎ ሜትሩ ፉክክር በሴቶች ምህረት ገመዳ ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ በወንዶች አስቻለው ብሩ አሸናፊ ነበር።
በኢትዮጵያ እንደ አዲስ እየተጀመሩ ካሉ ኢንሼቲቮች አንዱ የስፖርት ቱሪዝም ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ላለፉት ዓመታት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፉት ከሃያ ዓመታት በላይ እስከ ሃምሳ ሺህ ሰው የሚሳተፍበትና በአዲስ አበባ ከተማ ከሚያካሂደው ዝነኛው የአስር ኪሎ ሜትር በተጨማሪ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ “ቅድሚያ ለሴቶች” አምስት ኪሎ ሜትር የሴቶች ብቻ የጎዳና ላይ ውድድር ለረጅም ዓመት እያከናወነ ይገኛል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ስፖርትን ከቱሪዝም ጋር በማቆራኘት ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የአትሌቶች ምድር በሆነችው የበርካታ ከዋክብት መፍለቂያ በቆጂ የጎዳና ላይ ውድድር እያከናወነ ይገኛል።
የብርቅዬ ከዋክብት አትሌቶች መፍለቂያ የሆነችው ኢትዮጵያን የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመሆን በተለያዩ ከተሞች ውድድሮችን በማድረግ ከተሞቹ ያላቸውን የባህልና የቱሪዝም ፀጋዎች በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ እድሎች ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም