ኢትዮጵያውያን በወርቅና ብር ሜዳሊያዎች ደምቀዋል

ትናንት ሁለተኛ ቀኑን በያዘው 20ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ባደረጉት የ3ሺህ ሜትር ውድድር በወርቅና ብር ሜዳሊያ ደምቀዋል።

በሴቶች 3ሺህ ሜትር አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች። በወንዶች ተመሳሳይ ርቀት ደግሞ ወጣቱ አትሌት በሪሁ አረጋዊ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል።

በአስደናቂ ብቃት በ8:37.21 ርቀቱን ማጠናቀቅ የቻለችው ፍሬወይኒ ሲጠበቅ የነበረውን ወርቅ ስታጠልቅ፣ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ብርቄ ኃየሎም በ8:39.28 ሰዓት 5ኛ በመሆን ፈፅማለች። አሜሪካዊቷ ሼልባይ ሆሊሀንና አውስትራሊያዊቷ ጄሲካ ሀል የብርና የነሐስ ሜዳሊያውን ወስደዋል።

በድንቅ አቋም ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያዊት አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ግላስጎ ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ባጠለቀች በዓመቱ ሌላ ወርቅ ማጥለቋ ተጠባቂ ነበር።

የ24 ዓመቷ ኮከብ በግላስጎው ተመሳሳይ ቻምፒዮና በ1500 ሜትር ስታሸንፍ በውድድር ዓመቱ በቤት ውስጥ ፉክክሮች አንድም ሽንፈት አልገጠማትም። ዘንድሮም የውድድር ዓመቱ ለወጣቷ አትሌት የተለየ አይደለም። የተለየ የሚያደርገው አምና ከተወዳደረችበት 1500 ሜትር ከፍ ብላ በ3000 ሜትር መወዳደሯ ነው። ፍሬወይኒ በ2022 በስምንት መቶ ሜትርም በቤት ውስጥ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወሳል።

ፍሬወይኒ 2025 የውድድር ዓመትን በአንፃራዊነት ለእሷ አዲስ ወደሆነው 3000 ሜትር ፉክክር አተኩራ ብትጀምርም የተሻለ ልምድ ካላቸው አትሌቶች ልቃ ነው መታየት የቻለችው። ትናንት ናንጂንግ ላይም ይህንኑ ብቃትና አሸናፊነቷን አስቀጥላለች።

ባለፈው የፈረንጆች የካቲት ወር ኦስትራቫ ላይ ባደረገችው ውድድር 8:24:17 የሆነ የራሷን ምርጥ ሰዓት አስመዝግባለች። ከዘጠኝ ቀን በኋላም ሌቪን ላይ ከኦስትራቫው የተሻለ 8:19:98 በማስመዝገብ በየጊዜው ብቃቷ እየተሻሻለና እያደገ እንደሚሄድ አሳይታለች። ይህ ሰዓቷም በቤት ውስጥ ውድድር ታሪክ ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኗል።

በሌቪኑ ውድድር የተሻለ ፈጣን ሰዓት ከማስመዝገቧ ባሻገር የሦስት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ቻምፒዮኗን ኢትዮጵያዊት አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ማሸነፏ በራስ መተማመኗን ይበልጥ አሳድጎላታል። ፍሬወይኒ እያሳየች የሚገኘው ድንቅ ብቃት በቀጣይም ትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተስፋ ከወዲሁ ያንፀባረቀ ሆኗል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የዘንድሮውን ሳይጨምር ካለፉት 11 የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የሴቶች 3000 ሜትር ውድድር ዘጠኙን ማሸነፋቸው ይታወቃል።

በተመሳሳይ ርቀት ትናንት በተካሄደው የወንዶች 3ሺህ ሜትር ፍፃሜ የፓሪሱ ኦሊምፒክ የ10ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ከባዱን ፉክክር ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ ሊያሸንፍ ችሏል። በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው ኖርዌያዊው አትሌት ጃኮብ ኢንግብሪግስተን እንደተጠበቀው በ7:46.09 ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያውን ወስዷል። አውስትራሊያዊው ካይ ሮቢንሰን 7:47.09 በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያው አሸናፊ ነው። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቢኒያም መሐሪ 7:49.18 ዘጠነኛ ፣አትሌት ጌትነት ዋለ 7:50.07 አስራ አንደኛ ደረጃ ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

ቻምፒዮናው ዛሬ ሲጠናቀቅ ጉዳፍ ፀጋይና ድሪቤ ወልተጂ የሚሳተፉበት የሴቶች 1500 ሜትር እንዲሁም ፅጌ ድጉማና ንግስት ጌታቸው የሚሳተፉበት የስምንት መቶ ሜትር ውድድር ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳሊያዎች የሚመዘገቡበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You