
ዓለም አቀፉን የሠራተኞች ቀን ሜይ ዴይን ምክንያት በማድረግ በሠራተኞች መካከል የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ተጀምረዋል። የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሰማኮ) በየዓመቱ ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች አንዱ የሆነው የሠራተኞች የበጋ ወራት ውድድር ተቋርጦ ተቋማት የሜይ ዴይ የጥሎ ማለፍ ውድድሮች በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የሜይ ዴይ ስፖርታዊ ውድድር ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ ባለፉት አምስት ዓመታት ተቋርጦ እንደነበር ይታወቃል። ዘንድሮ የሜይ ዴይ ውድድሮች ዳግም የተጀመሩ ሲሆን የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በአስር የስፖርት አይነቶች ካለፈው መጋቢት 6-7 በተከናወኑ ፉክክሮች መጀመራቸውን የኢሰማኮ የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ ተናግረዋል።
የጥሎ ማለፍ ውድድሮቹ ከአዲስ አበባ ውጪ በሌሎች ከተሞች በሚገኙ የኢሰማኮ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች እየተካሄዱ ሲሆን፣ በመጪው ሚያዝያ 05/2017 ዓም ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሜይ ዴይ ሚያዝያ 23-2017 በሚከበርበት እለትም በየስፖርት አይነቶቹ የጥሎ ማለፍ አሸናፊዎቹ ለዋንጫ የሚጫወቱ ይሆናል። የፍፃሜ ጨዋታዎችና የመዝጊያ መርሃግብሩ በየትኛው ከተማ እንደሚከናወን ግን ለጊዜው አልተገለፀም።
የጥሎ ማለፍ ውድድሮቹ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በተጀመሩበት ወቅት በተለያዩ ስፖርቶች በርካታ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ጠንካራ ፉክክር በሚያስተናግደው የእግር ኳስ ስፖርት ስድስት ጨዋታዎች ተከናውነዋል።
በዚህም መሠረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቃሊቲ ብረታ ብረትን 3ለ0 በሆነ የፎርፌ ውጤት ሲያሸንፍ፣ ረጲ ሳሙናና ዲተርጀንት በኢካፍኮ 3ለ1 ተሸንፏል። አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ሞኤንኮ ኩባንያን 5ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ሲያሸንፍ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዮሐንስ ቢፍ(ኢን ወተር)ን 3ለ2 በሆነ ጠባብ ውጤት ረቷል። ኢትዮጵያ መድን ድርጅት ኢትዮ ቴሌኮምን 7ለ6 ያሸነፈ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ዘመን ባንክን 4ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
በሴቶች ቮሊቦል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች አዲስ አበባ ከተማ አውቶብስን 2ለ0 ያሸነፈ ሲሆን፣ በወንዶች ቮሊቦል አዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ቃሊቲ ብረታ ብረትን 3ለ0 ረቷል።
በሴቶች ጠረጴዛ ቴኒስ በተካሄዱት ሁለት ጨዋታዎች ብርኃንና ሰላም ማተሚያ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎችን 3ለ2 አሸንፏል። ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3ለ0 ረቷል። በተመሳሳይ በወንዶች ጠረጴዛ ቴኒስ በተከናወነ አንድ ጨዋታ ብርኃንና ሰላም ማተሚያ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽንን 3ለ1 አሸንፏል።
በወንዶች የዳርት ውድድር ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደው መከላከያ ኮንስትራክሽን አዲስ አበባ ከተማ አውቶብስን 2ለ1 ሲረታ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ኢትዮ ቴሌኮምን 2ለ0 አሸንፏል።
በዳማ ውድድር በወንዶች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፋፋ ምግብን 3ለ2 አሸንፏል። ብርኃንና ሰላም ማተሚያ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ 3ለ0 ተረቷል።
የሜይ ዴይ የጥሎ ማለፍ ውድድር ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ቀጥለው ሲካሄዱም በበርካታ የስፖርት አይነቶች የተለያዩ ፉክክሮች ይደረጋሉ።
በእግር ኳስ የሚጠበቁ ስድስት ጨዋታዎች በተለያዩ ሜዳዎች ሲከናወኑ ኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወታሉ። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከኢትዮጵያ መድን የሚያገናኘው ጨዋታም ተጠባቂ ነው። ሁለቱ ጨዋታዎች ነገ በባንክ ሜዳ የሚካሄዱ ናቸው። በተመሳሳይ ነገ በቃጫ ሜዳ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ከመከላከያ ኮንስትራክሽን፣ ኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ከኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ የሚገናኙ ይሆናል። ባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ከአዲስ አበባ አውቶብስ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ደግሞ በጎፋ ሜዳ ይካሄዳሉ።
በርካታ የቤት ውስጥ ውድድሮች ዛሬ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የስፖርት ማዘውተሪያዎች ሲካሄዱ፣ በሴቶች ቮሊቦል አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ በወንዶች ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ይገናኛሉ።
ጠረጴዛ ቴኒስ በወንዶች የሚያስተናግዳቸው አራት ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ፋፋ ምግብን ከአዲስ አበባ አውቶብስ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከብራና ማተሚያ፣ ብርኃንና ሰላም ማተሚያን ከኢትዮ ቴሌኮም ያገናኛል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም