ኢትዮ- ሶማሊያ ጦርነት እና አንጸባራቂው የካራማራ ድል

እንደ መግቢያ፦ የእንግሊዝ ሶማሌላንድ የምትባለው ግዛት በ1952 ነጻነቷን ተቀዳጀች። ከአራት ቀናት በኋላ ደግሞ የ“ኢጣሊያ ሶማሊያ” የምትባለው ምድር ነጻ ሆነች። በወቅቱ “የተበታተኑትን የሶማሊያ ግዛቶች አንድ ላይ ሰብስቦ ታላቋ ሶማሊያን መፍጠር” የሚል እሳቤ ይንቀለቀል ስለነበር የሁለቱ ግዛቶች ፖለቲከኞችም የጉዞ መስመራቸውን በዚህ ፈር ለመቀየስ ወሰኑ። በመሆኑም ሁለቱ የሶማሊያ ግዛቶች ከስድስት ወር በኋላ በመቀላቀል “የሶማሊያ ሪፐብሊክ”ን መሰረቱ።

እነዚያ የሶማሊያ መሪዎች በያዙት መሬት ሳይብቃቁ “እያንዳንዱ የሶማሊያ መሬት በአዲሲቷ ሶማሊያ ስር መግባት አለበት” የሚል አቋም እንደ መርህ ያዙ። በመሆኑም “ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ የያዙትን መሬቶቻችንን እንፈልጋለን” የሚል ሰበካ ጀመሩ። በዚያ ወቅት ጅቡቲና ኬንያ ነጻነታቸውን አልተጎናጸፉም። ስለዚህ ሶማሊያዎቹ ከቅኝ ገዥዎቹ ፈረንሳይና እንግሊዝ ጋር መጋጠም እንደማያዋጣቸው ስላወቁ ትኩረታቸውን በኢትዮጵያ ላይ አደረጉ።

ከአንድ ዓመት በኋላም አነስተኛ የሰርጎ ገብ ኃይል በማደራጀት በምሥራቅ ኢትዮጵያ ያለውን ቆላማውን የኦጋዴንን ክልል ለመውረር ሞከሩ። ነገር ግን በጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም የሚመራው ሶስተኛ ክፍለ ጦር በአስር ቀናት ውስጥ ሶማሊያዎቹን አባረራቸው። ከዚያ በኋላ ሶማሊያዎቹ በኢትዮጵያ ላይ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት አፋፋሙ፡፡

በ1955 የተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊገስጻቸው ቢሞክርም እነርሱ ግን ከአድራጎታቸው አልታቀብ አሉ። መሪያቸው የነበረው አደን አብደላ ዑስማን ዳሂር በአዲስ አበባ በተሰበሰበው የአፍሪካ መንግሥታት ጉባኤ ላይ “ኢትዮጵያ መሬታችንን ወስዳለች” ሲል ከሰሰ። በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ማቋቋሚያ ቻርተርም ላይ “የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ሲወጡ ያላቸውን ድንበር ይዘው ይቆያሉ” የሚለውን አንቀጽ አልፈርምም አለ።

በ1957 ሶማሊያ በይፋ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አወጀች። ይሁንና ጦርነቱ ረጅም ጊዜ ሳይቆይ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ሶማሊያ ከ1957 ሽንፈት በኋላ ይፋዊ ጦርነቱን ትታ በእጅ አዙር መዋጋቱን መረጠች። ለዚህም ይረዷት ዘንድ “የኦጋዴን ሶማሊያ አርነት ግንባር” እና “የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር” (ም.ሶ.ነ.ግ) የተባሉ ድርጅቶችን አቋቋመች (የኦጋዴን ሶማሊያ አርነት ግንባር ከአሁኑ “የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር” ጋር አንድ አይደለም።

አሁን ያለው “ኦብነግ” በ1975 ነው የተመሰረተው)። የእነዚህ ድርጅቶች ዓላማ የኦጋዴንን ክልል ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ወደ ሶማሊያ መቀላቀል ነበር። ይሁንና ድርጅቶቹ ኦጋዴንን ሊገነጥሉት ይቅርና የሚረባ ውጊያ እንኳ ማድረግ አልቻሉም። በዚህም የተነሳ ከሁለቱ ድርጅቶች መካከል በደካማ አቋም ላይ የነበረው የኦጋዴን ሶማሊያ አርነት ግንባር ብዙም ሳይራመድ ከስሟል። ም.ሶ.ነ.ግ ግን እየተንደፋደፈም ቢሆን ውጊያውን ቀጥሏል።

ጄኔራል ሙሐመድ ዚያድባሬ ጥቅምት 1962 በመንፈቅለ መንግሥት ስልጣን ሲይዙ ደግሞ ሁሉም ነገር ከመሠረቱ ተቀየረ። “ሶማሊያ ከኢትዮጵያ የምትፈልገው ኦጋዴንን ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ የተወሰደብን መሬት የሐረርጌ፣ ባሌ እና ሲዳሞ ክፍለ ሀገራትን የሚያጠቃልል ነው” የሚል አዋጅ ታወጀ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የሶማሊያ መንግሥት የሶሻሊዝም ተከታይ መሆኑን በይፋ በማወጁ ከሶቪየት ህብረት ጋር የወታደራዊ ተራድኦ ስምምነት ተፈራራመ። በስምምነቱ መሰረት ከሶቪየት ህብረት አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን በገፍ አገኘ። ለሰባት ዓመታት ያህልም ሠራዊቱን ሲያሰለጥንና ሲያደራጅ ሰነበተ። በውጤቱም የዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ ከ70 የማያንሱ ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖችን የታጠቀ አየር ኃይል እና አራት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮችን ያቀፈ ግዙፍ የጦር ሠራዊት ባለቤት ለመሆን ቻለች፡፡

በሰርጎ ገብ ታጣቂዎች የተጀመረው ትንኮሳ

የሶማሊያ መንግሥት ይህንን ሁሉ ካደረገ በኋላ ፤ በቅድሚያ በድብቅ ያደራጃቸውን የምዕራብ ሶማሊያ ነጻ አውጪ ግንባር/Western Somali Liberation Front (ም.ሶ.ነ.ግ- WSLF) እና የሶማሊያ አቦ ነጻነት ግንባር/ Somali Abo Liberation Front (ሶ.አ.ነ.ግ- SALF) አሸማቂዎችን በማስቀደም ትንኮሳ ጀመረ፡፡

በዚህም መሰረት በመጋቢት ወር 1968 የም.ሶ.ነ.ግ ተዋጊዎች ከሀርጌሳ መስመር እየተነሱ በኦጋዴንና በደጋማው የሐረርጌ ክፍል ተሰማሩ። የሶ.አ.ነ.ግ ተዋጊዎች በበኩላቸው በባሌ ክፍለ ሀገር ወደ ውስጥ እየሰረጉ እስከ ጊኒር እና ጎሮ አውራጃዎች ድረስ ለመግባት ቻሉ።

እነዚህ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ በገቡበት ወቅት የደርግ መንግሥት ከኢህአፓ ጋር በገጠመው ትግል እየተናጠ ነበር። ጀብሃና ሻዕቢያም በሰሜኑ በኩል ወጥረው ይዘውታል።

ኢዲዩ የተባለው ድርጅትም የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የጠረፍ ከተሞችን ይዞ ደርግን በማስጨነቅ ላይ ነበር፡፡

የም.ሶ.ነ.ግ እና የሶ.አ.ነ.ግ ኃይሎች እንደሚፈልጉት ድል ሊቀናቸው አልቻለም። ራቅ ባሉ ጫካዎችና ጥሻዎች ከመመሸግ በስተቀር ወደ ከተሞች እየተጠጉ የኢትዮጵያን ሠራዊት ማስጨነቅ አልቻሉም። በመሆኑም የሲቪል ልብስ የለበሱ የሶማሊያ ሠራዊት አባላት በም.ሶ.ነ.ግ ውስጥ በብዛት እንዲቀላቀሉ ተደረገ።

ይህኛውም ስትራቴጂ ውጤት ማስገኘት አልቻለም። ሁለቱ የም.ሶ.ነ.ግ እና የሶ.አ.ነ.ግ. ኃይሎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የትኛውንም ከተማ መቆጣጠር ተስኗቸው ነበር። በዚህ ተስፋ የቆረጡት የሶማሊያ የጦር አዝማቾችም ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ መደበኛ ሠራዊታቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ይወተውቷቸው ጀመር።

ፕሬዚዳንት ዚያድ ግን ለጦር አዝማቾቹ ውትወታ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት አልፈለጉም። ይህም የሆነው ከሶቪየት ህብረት አማካሪዎቻቸው የተሰጣቸውን ተግሳፅ በመፍራታቸው ነው። ሶቪየቶቹ “ኢትዮጵያን እየወረራችሁ ነው” የሚል ስሞታ ሲያቀርቡባቸው “እኛ አይደለንም፤ የኦጋዴን ሶማሊያዎች ለነጻነታቸው የሚያደርጉት ትግል ነው” እያሉ ሲከላከሉ ቆዩ።

በግንቦት ወር 1969 ደግሞ ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ። የጎዴ ከተማን እንዲያጠቃ የታዘዘ አንድ የም.ሶ.ነ.ግ ሻለቃ ከኢትዮጵያ ጦር በገጠመው የመከላከል ርምጃ ሙሉ በሙሉ ተደመሰሰ። 300 ያህል ተዋጊዎቹ በአንድ ቀን አለቁበት። በርካቶችም ቆሰሉ። የሽምቅ ተዋጊውን ቡድን እንዲመሩ የተመደቡ አስራ አራት የሶማሊያ የጦር መኮንኖችም ከሟቾቹ መሀል ነበሩ። ይህ ክፉ ዜና በሞቃዲሾ ሲሰማ በጦር ኃይሉ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣ ተቀሰቀሰ።

በፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ ከፍተኛ አብዮታዊ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር አስቸኳይ ጠራ። በስብሰባው መጨረሻ ላይ በተደረሰበት ስምምነት መሰረትም ለአንድ ወር ያህል የድብቅ ወረራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተወሰነ፡፡

በዚህ ጊዜ ትኩረት የተደረገባቸው ከተሞች በኢትዮ-ሶማሊያ-ኬንያ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘው የዶሎ ኦዶ ከተማ፣ በደቡባዊ ኦጋዴን የምትገኘው የባሬ ከተማ እና በደቡባዊ ባሌ ያለው የኤልከሬ ቆላማ ስፍራ ነው። በዚህ የድብቅ ውጊያ ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የሶማሊያ ሠራዊት መደበኛ ዩኒፎርም እንዲለብስ አልተደረገም።

የዚህ ድብቅ ውጊያ ዓላማ የኢትዮጵያን ሠራዊት ማስበርገግና የውጊያ አቋሙን መፈተሽ ነበር።

ሐምሌ 15/1969። በድብቅ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ አበቃ። ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ የታላቋ ሶማሊያ ምስረታ እውነት የሚሆንበት ጊዜ የመጣ መስሎ ታያቸው። በመሆኑም ለዘመናት ሲያደራጁት የነበረው ሠራዊት በሙሉ ኃይሉ ማጥቃት እንዲጀምር ትዕዛዝ ሰጡ፡፡

ከትንኮሳ ወደ ሙሉ ጦርነት

ለዓመታት ለወረራ ሲዘጋጅ የነበረው የሶማሊያ የጦር ኃይል በኢትዮጵያ መሬት ላይ ዘመተ። የሶማሊያ ጦር ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሁለት መስመሮች ነው፡፡

  • የኦጋዴን መስመር በዚህ መስመር ወደ ኢትዮጵያ የገባው የሶማሊያ ጦር በኦጋዴን የፌርፌር ከተማ ትይዩ ካለችው የበለድወይን ከተማ ነው የተነሳው። የመጨረሻ ግቡ ደግሞ መላውን የኦጋዴን ቆላማ አውራጃዎች መቆጣጠር ነው።
  • የዶሎ ኦዶ መስመር፡ በዚህኛው መስመር የተሰለፈው ጦር የተነሳው ደግሞ ከሶማሊያዋ የባይዶዋ ከተማ ነው። ዶሎ ኦዶ ከምትባለው የድንበር ከተማ ከደረሰ በኋላም ለሁለት በመከፈል ወደ ባሌና ሲዳሞ ክፍለ ሀገራት እንዲዘምት ነው የታሰበው። በሁለት የተከፈለው ሠራዊት የመጨረሻው ግብ የባሌ ጎባ እና ነጌሌ ቦረና ከተሞችን መቆጣጠር ነው።

ከባይዶዋ አካባቢ የተነሳው የሶማሊያ ጦር ይህ ነው የሚባል መከላከል አልገጠመውም። በመሆኑም በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ወደ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ እየገሰገሰ ሄዶ ከነጌሌ ቦረና ከተማ 40 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ደረሰ። በባሌ ክፍለ ሀገር ደግሞ እስከ ዶሎ መና (መስሎ) ከተማ ያለውን መሬት ለመያዝ ቻለ፡፡

ሶማሊያዎች ውጊያው እንዲህ የቀለላቸው ብዛታቸው ስለረዳቸው አልነበረም። ይልቁንም ኢትዮጵያ በእነዚህ መስመሮች ጠንከር ያለ ሠራዊት ስላልነበራት ነው። የነጌሌ እና የጎባ ከተሞች እንኳ በጠላት እጅ ከመውደቅ የተረፉት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለእግረኛ ተዋጊዎቹ ከፍተኛ የሽፋን እገዛ በማድረጉ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የሶማሊያ ባለጋራውን በዐይነ ቁራኛ ሲጠብቅ የነበረው በኦጋዴን መስመር ነበር። በመሆኑም ከበለድወይን የተነሳው የሶማሊያ ሠራዊት የኦጋዴን አውራጃዎችን በቀላሉ ለመቆጣጠር አልቻለም፡፡

የኢትዮጵያ ተዋጊዎች ኦጋዴንን ላለማስነጠቅ እስከ መጨረሻው ተሟሙተዋል። በተለይም በሐምሌ አጋማሽ (1969) ማብቂያ ላይ የቀብሪደሃር ከተማን ላለማስለቀቅ በተደረገው ትግል በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ተሰውተዋል።

ሶስተኛው የወረራ ግንባር፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ኦጋዴንን ላለማስነጠቅ በሚታገልበት ወቅት ሶማሊያዎች በጦርነቱ ሂደት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተለ ርምጃ ወሰዱ። ይህም የሶስተኛ የወረራ ግንባር መከፈት ነው።

በዚህ የወረራ ግንባር የተሰማራው የሶማሊያ ሠራዊት የተነሳው ከሰሜን ሶማሊያዋ የሀርጌሳ ከተማ ነው። የመጨረሻ ግቡ ደግሞ የሐረርና የድሬ ዳዋ ከተሞችን ጨምሮ የደጋማውን የሐረርጌ ክፍል መቆጣጠር ነው። በሶስተኛው ግንባር የተሰማራው የሶማሊያ ጦር በብዛቱ በሌሎች ግንባሮች ከዘመተው ይበልጣል።

በጣም ምርጥ የተባሉ የጦር መሳሪያዎችንም ታጥቋል። ሶማሊያ ካላት አራት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮች መካከል ሁለቱ በዚህ ግንባር ተሰልፈዋል። የሶማሊያ አየር ኃይልም ሙሉ ሙሉ ትኩረቱን በዚህ ግንባር ላይ አድርጓል። የሶማሊያ የፕሮፓጋንዳ ኃይሎችም “ሐረር ተከበበች፣ ድሬዳዋ ተያዘች” እያሉ ማሸበር ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ሶማሊያ በሶስተኛው ግንባር ውጊያ ትከፍታለች ብለው አልጠበቁም ነበር። በመሆኑም ወረራውን ለማስቆም ምን ዓይነት ርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ከውሳኔ ላይ ለመድረስ ተቸገሩ።

የሶማሊያ ጦር የመጨረሻ ጉዞ የት ሊሆን እንደሚችል ማወቅም ተሳናቸው። በመሆኑም ሊቀመንበር መንግሥቱና ሌሎች ጓዶቻቸው በጉዳዩ ዙሪያ ለመወሰን አስቸኳይ የዝግ ስብሰባ ተቀመጡ (በስብሰባው ላይ የሶቪየት አማካሪዎችም ተገኝተው ነበር)።

በዝግ ስብሰባው ኦጋዴንን በስልታዊ ማፈግፈግ መልቀቅና ድሬዳዋና ሐረርን ማዳን የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት አገኘ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ጦር ከኦጋዴን ለቆ በጅግጅጋና ጉርሱም አውራጃዎች ውስጥ እንዲሰፍር ተደረገ።

ወረራውን ለመቀልበስ የተደረሱ ውሳኔዎች

የሶማሊያ ኃይሎች ኦጋዴንን በድብቅ በወረሩበት ጊዜ ኢትዮጵያ በውስጣዊ ፖለቲካ ተቀስፋ የተያዘችበት ጊዜ ነበር። ከዚህ የተነሳም የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ለሶማሊያ ጉዳይ ሙሉ ትኩረት መስጠት የጀመረው በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር ። በጊዜው በድንበር አካባቢ ያለው ግፊት እየተጠናከረ መምጣቱ ሪፖርት መደረጉን ተከትሎ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም አቤቱታቸውን በድንገት ወደ አዲስ አበባ ለመጡት የኩባው ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ሩዝ አሰሙ።

ፕሬዚዳንት ካስትሮም ሊቀመንበር መንግሥቱንና ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬን የደቡብ የመን ዋና ከተማ በሆነችው አደን ላይ ሰበሰቧቸው። ሁለቱ መሪዎች በተናጠልና በጋራ ባደረጉት ውይይት ሊስማሙ አልቻሉም፡፡

የዚህም ምክንያት ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ያቀረቡት የመሬት ስጡን ጥያቄ በኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዘንድ ተቀባይነት በማጣቱ ነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ልዑካን “ሶማሊያ ውጊያ ጀምራለች” በማለት ላቀረቡት ክስ የሶማሊያው መሪ “ውጊያ አልጀመርንም፤ ውጊያ ማለት ምን እንደሆነ ወደፊት ታያላችሁ” የሚል ዛቻ አዘል ምላሽ መስጠታቸው የውይይቱን መንፈስ ረብሾት እንደነበረ ይነገራል፡፡

በኤደን የተደረገው ውይይት ያለ ውጤት ከተበተነ በኋላ ሊቀመንበር መንግሥቱ ለመጪው ውጊያ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተገነዘቡ። በመሆኑም “ስጋ ሜዳ” በሚባለው ቦታ የሚገኘውና የቀድሞ የድኩማን ማቋቋሚያ ድርጅት ወላጅ አልባ ሕጻናትንና ረዳት የሌላቸውን አረጋውያንን የሚንከባከብበት ማዕከል ተወስዶ የጦር ማሰልጠኛ ካምፕ እንዲሆን ተወሰነ፡፡

ማሰልጠኛውም “ታጠቅ” በሚል ስያሜ ተጠራ። የጦርና የሲቪል ከፍተኛ ካድሬዎች ለስልጠና በደብረ ብርሃን የመምህራን ማሰልጠኛ እንዲከቱ ታዘዙ። ጡረታ ለወጡ ወታደሮች የሰርኩላር ጥሪ ተላለፈ። በየክፍለ ሀገሩ እጩ ሚሊሻዎች እንዲመለመሉ ትዕዛዝ ተሰጠ።

ይህ ሁሉ ከተደረገ በኋላ ሊቀመንበር መንግሥቱ ሚያዚያ 4/1969 በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገሩን እንዲያድን የሚያሳስበውን ታሪካዊውን የእናት ሀገር ጥሪ አደረጉ። ጥሪውን የሰማው የአዲስ አበባ ሕዝብም ድጋፉን ሚያዚያ 6/1969 በአብዮት አደባባይ ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ገለጸላቸው።

በክፍለ ሀገር ከተሞችም የድጋፍ ሰልፎች ተደረጉ። በቀበሌ ደረጃ በተዋቀሩ የእናት ሀገር ጥሪ አስተባባሪ ኮሚቴዎች አማካኝነትም ለሠራዊቱ ስንቅ የሚሆኑ ደረቅ የምግብ ዓይነቶችን (በሶ፣ ቆሎ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ብስኩት ወዘተ..) ማዘጋጀት ተጀመረ። እንደ ኩባያ፤ ሳህን፤ ማንኪያ፤ ድስት ወዘተ.. የመሳሰሉ ቁሳቁሶችም የማብሰያና የመሰብሰቢያ እቃዎችም ከሕዝቡ ተሰበሰቡ።

ሰኔ 19/1969 ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቅ ወታደራዊ ሰልፍ አሳየች። ከዚህ ጎን ለጎን በመገናኛ ብዙኃን የሚደረገው የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ተፋፍሞ ቀጠለ። የወታደራዊ ሰልፉም ሆነ የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱ ዓላማ በሶማሊያ ላይ የስነ- ልቦና ሽብር መፍጠር ነበር።

ነገር ግን ሶማሊያዎች ለኢትዮጵያ የስነ-ልቦና ጦርነት ተበግረው ወረራውን ከመፈጸም አልተቆጠቡም። የዚህም ምክንያቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት የሰው ብዛት እንጂ ለውጊያ የሚረዱ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ያልታጠቀ መሆኑን የሚያውቁ መሆናቸው ነበር።

የኢትዮጵያ ሠራዊትን ለማስታጠቅ የገጠሙ ፈተናዎች

ሶማሊያ ወረራውን በጀመረችበት ወቅት በሁለቱ ሀገሮች የጦር ሠራዊቶች መካከል ከፍተኛ ልዩነት ነው የነበረው። ለምሳሌ የሶማሊያ የምድር ጦሩ አወቃቀር ይህንን ይመስል ነበር።

  • እግረኛ ክፍለ ጦር =8 (ኢትዮጵያ አራት ክፍለ ጦር ነው የነበራት)
  • ኮማንዶ ብርጌድ= 4 (ኢትዮጵያ ምንም አልነበራትም)
  • ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር= 4 (ኢትዮጵያ ምንም አልነበራትም)
  • ታንከኛ ክፍለ ብርጌድ= 4 (ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ነው የነበራት)
  • መድፈኛ ብርጌድ= 4 (ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ነው የነበራት)
  • ቢኤም ሮኬት ሻለቃ= 7 (ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ነው የነበራት)
  • የቀላል ሚሳይል አየር መቃወሚያ ሻለቃ= 5 (ኢትዮጵያ ምንም አልነበራትም) ሶማሊያ የታጠቀችው የከባድ መሳሪያ ዓይነትና ብዛትም የሚከተለው ነው።
  • ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች 253 (ኢትዮጵያ 51 ነበራት)
  • ታንኮች = 608 (ኢትዮጵያ 132 ነበራት)
  • መድፎች = 260 (ኢትዮጵያ 48 ነበራት) የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 14
  • ቢ.ኤም ሮኬቶች = 125 (ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ነበራት)
  • አየር መቃወሚያ ሚሳይሎች = 75 (ኢትዮጵያ ምንም አልነበራትም)
  • ተዋጊ አውሮፕላኖች= 65 (ኢትዮጵያ 8 ብቻ ነው የነበራት) ኢትዮጵያ ያኔ የታጠቀችው አሜሪካ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የሠራቻቸውን T-2 ታንኮችን ናቸው። የሠራዊቱ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችም “ካርባይን” እና “ኤ.ም. ዋን” የሚባሉ አሮጌ ጠመንጃዎች ነበሩ።

በመሆኑም የሶማሊያ ሠራዊት በመሳሪያ ብዛት ብቻ ሳይሆን በጥራትም ብልጫ ነበረው። ኢትዮጵያ ከሚያዚያ ወር መጨረሻ ጀምሮ የመሳሪያ ልመናውን ጉዳይ አጠናክራ ቀጠለች። ሊቀመንበር መንግሥቱ በየመን ከተደረገው ውይይት በኋላ ለመሳሪያ ጥያቄ ወደ ሶቪየት ህብረት ቢጓዙም፤ የክሬምሊን መንግሥት በቀላሉ ፊት አልሰጣቸውም። ለዚህም አንደኛው ምክንያት ሶቪየት ህብረት ከሶሻሊስቷ ሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ተራድኦ ስምምነት የነበራት መሆኑ ነው።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሶቪየቶች በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ በነበረው ለውጥ ላይ ጥርጣሬ የነበራቸው መሆኑ ነው። በመሆኑም ሊቀመንበር መንግሥቱ ሶቪየትን ትተው ወደ ሌሎች የምሥራቅ አውሮፓ ሀገሮች ተጓዙ። ይሁንና ከእነዚህም ሀገራት መሳሪያ ለማግኘት የሶቪየትን ይሁንታ ይፈልግ ስለነበር በለስ ሊቀናቸው አልቻለም፡፡

ሊቀመንበር መንግሥቱ ከሶቪየት ወደ ቻይና ሲያመሩ ግን ያላሰቡት እድል ገጠማቸው። የቻይና መሪዎች ከሶቪየትም ሆነ ከሶማሊያ መሪዎች ጋር የማይጣጣሙ በመሆናቸው ለኢትዮጵያ የመሳሪያ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት አላመነቱም። በመሆኑም ታንኮችንና መድፎችን የማያካትት ለሁለት ክፍለ ጦር የሚበቃ ትጥቅ ለኢትዮጵያ ሰጡ፡፡

እንደ ቻይና ሁሉ ከሶቪየት መሪዎች ጋር የማይጣጣሙት የዩጎዝላቪያው መሪ ጆሲፍ ብሮዝ ቲቶም የኢትዮጵያ አርበኞች ከዩጉዝላቪያ ጓዶች ጋር የነበራቸውን የጋራ የትግል ወኔ በማስታወስ 70 አሜሪካ ሰራሽ ታንኮችንና እጅግ በርካታ ቀላል መሳሪያዎችን ከበቂ ጥይቶች ጋር አበረከቱ፡፡

ሊቀመንበር መንግሥቱ ለአሜሪካ መሪዎችም የ“መሳሪያ ሽጡልን” ጥያቄ ማቅረባቸውን ይናገራሉ። ይህም የተደረገው በኢራንና በእስራኤል በኩል በተደረጉ ምስጢራዊ ግንኙነቶች አማካኝነት ነው። አሜሪካኖቹ ለመሳሪያ ግዥ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ ጥቂት የመጓጓዣ አውሮፕላኖችን፣ ራዳሮችን፣ ጸረ ታንክ መሳሪያዎችንና 12 መድፎችን ሰጡ። ሆኖም ከአንድ ወር በኋላ ያለምንም ቅድመ ማስታወቂያ የመሳሪያ ሽያጩን አቆሙ።

“አሜሪካኖቹ ለግዥው መቋረጥ የሰጡት ምክንያት ግልጽ አይደለም፤ ነገር ግን ሶሻሊዝምን በማወጃችን በዚህ ቂም ይዘው ነበር” ይላሉ-ሊቀመንበር መንግሥቱ። በአንዳንድ ፋይሎች ተጽፎ እንደሚታየው ከሆነ ደግሞ አሜሪካ “መሳሪያውን የከለከልኩት ሁለቱም ሀገራት መዋጋት የለባቸውም የሚለውን የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔን ተከትሎ” ነው ትላለች።

የዓለም አቀፍ ኃይሎች አሰላለፍ መቀየር፤ ሶማሊያ የሶሻሊዝም ተከታይ መሆኗ የታወጀው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ በመንግሥት ግልበጣ ስልጣን በያዙ በዓመቱ (እ.ኤ.አ. 1970) ነው። በዚህ አዋጅ መሰረት ነው ሀገሪቱ ከሶቪየት ህብረት ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ለማግኘት የበቃችው።

በ1967 ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ከስልጣን ያወረደው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በታህሳስ ወር 1967 ኢትዮጵያ የሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ሥርዓት ተከታይ ሀገር መሆኗን ቢያውጅም የሶቪየቶችን ሙሉ ይሁንታ ለማግኘት ቸግሮት ቆይቷል።

ሶቪየቶች የኢትዮጵያ ወታደራዊ መሪዎችን እንደ ሀገር ወዳድ አብዮታዊያን እንጂ እንደ እውነተኛ ኮሚኒስቶች ለመቀበል ተቸግረው ነበር። በመሆኑም በክፍል ሶስት እንደተገለጸው፤ የሶማሊያ ወረራ ባንዣበበት ወቅት ሀገራችን ከአሜሪካም ሆነ ከሶቪየት ህብረት (USSR) የጦር መሳሪያዎችን ለማግኘት አልቻለችም፡፡

ሚያዚያ ወር/ 1969። በዚህ ወር የኢትዮጵያ መሪዎች አንድ ያልታሰበ ፖለቲካዊ ርምጃ ወሰዱ። ይህም በኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊና ሲቪል ተቋማት እንዲዘጉ ማድረጋቸው ነው። በዚህ መሰረት በአስመራ የሚገኘው የቃኘው ወታደራዊ መረጃ ጣቢያ (ቃኘው ሰቴሽን)፣ በምጽዋ የነበረው የአሜሪካ የባሕር ኃይል መደብ (በተለምዶ “ናምሩ” የሚባለው)፣ በአዲስ አበባ የነበረው የአሜሪካ ወታደራዊ አማካሪ ቡድን (ማግ-MAG)፣ የአሜሪካ የማስታወቂያ አገልግሎት (USIS) ተዘጉ፡፡

በማስከተልም በአሜሪካ የሰብዓዊ ርዳታ አገልግሎት ድርጅቶች ላይ ገደብ ተጣለ። የኢትዮጵያ መሪዎች አሜሪካዊ ተቋማትን ለመዝጋት የወሰኑት ሆን ተብሎ የሶቪየቶችን ቀልብ ለመግዛት በተወጠነ እቅድ አይደለም። ነገሩ የተከሰተው ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ኢትዮጵያ አስቀድማ የከፈለችበት የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዲታገድ በማድረጋቸው ነው።

በጊዜው አሜሪካ የሶማሊያ ደጋፊ ባትሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ ሶሻሊዝም በመታወጁ ከሀገራችን ጋር የነበራትን ግንኙነት አለዝባ ነበር። የመሳሪያ ሽያጩንም ያገደችው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ መተማመን በማጣቷ ነው። የኢትዮጵያ መሪዎች በአሜሪካ ተቋማት ላይ በወሰዱት ርምጃ የሶቪየት መሪዎች በኢትዮጵያ ላይ የነበራቸው እይታ በአንድ ጊዜ እንዲቀየር አደረገ።

በመሆኑም የሶቪየት ህብረት መሪዎች ያዝ ለቀቅ ሲያደርጉት የነበረውን የኢትዮ-ሶማሊያ አጀንዳ እንደ ራሳቸው ጉዳይ በመቁጠር ቅድሚያ ሰጡት። በግንቦት ወር 1969 ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሞስኮን እንዲጎበኙ ተጋበዙ። በዚህ ፕሮግራም ከጓድ ሊዮኒድ ብሬዥኔቭ ጋር ከፍተኛ መግባባት ላይ ደረሱ። በመስከረም ወር በድብቅ በተያዘ ፕሮግራም አማካኝነት ሶቪየት ህብረት ኢትዮጵያ ላቀረበችው የወታደራዊ መሳሪያዎችና የቴክኒክ ድጋፍ ጥያቄዎች ሙሉ ምላሽ ሰጠች፡፡

ሶቪየት ህብረት ይህንን ስታደርግ ከሶማሊያ መሪዎች ተቃውሞ እንደሚመጣባት አላጣችውም።

ነገር ግን ሶማሊዎቹ በነበራቸው ከገደብ ያለፈ የመሬት ጥያቄ ተሰላችታ ስለነበር ለተቃውሞው ብዙም ግድ አልሰጠችውም። ለዚህም ነው በቅድሚያ ኢትዮጵያን ይዛ ሶማሊያዎቹን “ ይህንን ነገር ብትተውት ይሻላችኋል” ማለቱን ነው የመረጠችው። በዚህም የሶማሊያ መሪዎች የሶቪየትን ርምጃ እንደ ክህደት በመቁጠር በወረራው ማግስት (በህዳር ወር 1970) በሀገራቸው ውስጥ የነበሩትን ከሁለት ሺህ የማያንሱ የሶቪየት የሲቪልና ወታደራዊ አማካሪዎችን፣ የሚዲያ ሰዎችን፣ ቴክኖራቶችንና በነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችን (ከነቤተሰቦቻቸው) አባረሩ፡፡

የሶቪየት ኃይሎች ከሶማሊያ መባረራቸው ለኢትዮጵያ ሠርግና ምላሽ ሆነ። የኢትዮጵያ የጦር ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ ሶቪየት ሰራሽ T-34 ታንኮችን፣ መድፎችን ቢ.ኤም ሮኬቶችን የሚታጠቅበት ሁኔታ ተመቻቸ ። አሮጌ የነፍስ ወከፍ መሳሪያቹ በክላሽኒኮቭ (AK-47) እና ኤስ.ኤስ. እንደሚተኩም ቃል ተገባ። የግርኖቭ መትረየሶችና ላውንቸሮችም ከሶቪየት ህብረት እንደሚመጡ ተነግሯል። የአየር ኃይሉም የሚግ ጄቶችና ለወታደራዊ አቪየሽን የሚያገለግሉ አንቶኖቭ አውሮፕላኖችን ሊታጠቅ ተዘጋጅቷል።

ይሁንና ኢትዮጵያ ቃል የተገባላትን መሳሪያ በቶሎ ማግኘት ባለመቻሉ ፤ ከሐምሌ 1969 እስከ ህዳር 1970 ድረስ ድሮ በነበሯትና ከቻይናና ከዩጎዝላቪያ ባገኘቻቸው መሳሪያዎች መከላከል የግድ ነበር። ከዚሁ ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ መደበኛ ሠራዊትና የአየር ኃይል ከፍተኛ የውጊያ ስልጠና ያስፈልገው ነበር።

የተጠቀሱትን ሁኔታዎች በማጤን የኢትዮጵያ መሪዎች አንደኛ መደበኛ ሠራዊቱን ለማጠናከር የሚረዳ ተጨማሪ ኃይል በብዛት ተመልምሎ በስልጠና ላይ እንዲቆይ

ሁለተኛው በታጠቅ ካምፕ ሲሰለጥን የነበረው የሚሊሻ ሠራዊት በቶሎ ወደ ግንባር ተልኮ ወረራውን በመከላከል ላይ የነበረውን ሠራዊት እንዲያግዝ የሚል ውሳኔ አስተላለፉ። ውሳኔው ከወታደራዊ ስልት አንጻር ሲታይ በጣም ትክክል ነው ተብሎ ተወድሷል፡፡

የመከላከል ውጊያ በምሥራቅ ግንባር

ሶማሊያ አደገኛ ወረራ ያደረገችው በሀርጌሳ ግንባር ነው። የኢትዮጵያ ሠራዊትም በዚህ ግንባር ተጠቃልሎ በመግባት ከፍተኛ የመከላከል ውጊያ ሲያደርግ ነበር። በወቅቱ ለኢትዮጵያ መሪዎች ያስቸገረው የሶማሊያ ጦር የስምሪት አቅጣጫዎችንና የመጨረሻ ዒላማዎችን ማወቁ ነው። ቀደም ሲል በነበረው ግምት የሶማሊያ ሠራዊት ጅግጅጋን ከያዘ በኋላ በማስከተል ወደ ሐረር ይመጣል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

ነገር ግን የሶማሊያ ሠራዊት በነሐሴ አጋማሽ ላይ ጅግጅጋንም ሆነ ሐረርን ሳይነካ ከጭናክሰን ከተማ ጀርባ ወደ ሰሜን ምዕራብ መጓዝ ጀመረ። የኢትዮ የኢትዮጵያ የጦር መሪዎች የሶማሊያ ሠራዊት በጉርሱም አውራጃ ውስጥ በማሳበር ወደ ሐረር ከተማ የሚያመራ ነበር የመሰላቸው።

በመሆኑም በሐረር ዙሪያ የነበረውን ጥበቃ አጠናከሩ።

የሶማሊያ ኃይሎች በቀጥታ ወደ ድሬዳዋ እየገሰገሱ መሆናቸው ታወቀ። በዚህም ጊዜ በኢትዮጵያ መሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ ተፈጠረ። “ለድሬዳዋ የሚረባ መከላከያ አልተደረገም” በሚል መወቃቀስ ተጀመረ። ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም በነገሩ ዙሪያ ከጦር መሪዎቻቸው አስቸኳይ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ በከተማዋ የነበሩትን ሁለት ሚሊሻ ክፍለ ጦሮችና አንድ ነበልባል ብርጌድ ከከተማዋ ወጥተው የመከላከያ ምሽጋቸውን እንዲያበጁ ትዕዛዝ ተላለፈ።

ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ተደራቢ ሆኖ የሚዋጋ አንድ ሜካናይዝድ ብርጌድም በአፋጣኝ ተመደበ። ከዩጎዝላቪያ የተገኙት ሰባ ታንኮችም በዚህ ግንባር እንዲሰለፉ ተደረገ። አንድ ሚሊሻ ክፍለ ጦርና አንድ መደበኛ ብርጌድም ደግሞ የድሬዳዋን ከተማ እንዲጠብቁ ተደረገ። ደቡብ የመን ለኢትዮጵያ የሰጠችው ሰላሳ ሶስት ታንኮችም ከስፍራው ደረሱ።

የኢትዮጵያ ሠራዊት የመከላከያ ጣቢያውን “ጀልዴሳ” በተባለ ስፍራ ላይ መሰረተ። (ይህ ስፍራ ከድሬዳዋ በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ በ50 ኪሎ ሜትር ላይ ነው የሚገኘው)። ነሀሴ 5 ቀን 1969 ወደ ድሬዳዋ የሚያመራው የሶማሊያ ሠራዊት “ጀልዴሳ” ሲደርስ ያልጠበቀው ውጊያ ገጠመው። ሶስት ቀናት ሙሉ ቢዋጋም ጀልዴሳን ማለፍ አቃተው።

ተጨማሪ ጦር አስመጥቶ እንደገና ሌላ ጥቃት ከፈተ። ነገር ግን የኢትዮጵያ ኃይሎችን አንበርክኮ ለማለፍ ሳይችል ቀረ። የሶማሊያ ሠራዊት በዚህ ተስፋ ሳይቆርጥ ለሶስተኛ ጊዜ ኃይለኛ የሜካናይዝ ውጊያ ከፈተ። ይሁን እንጂ የሶስተኛው ዙር ጥቃት ለሶማሊያዎቹ ከበፊቱ የባሰ ውድቀትን ነው ያስከተለው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሠራዊት የውጊያ ስልቱን በመለወጡ ነው።

ይህም ማለት ሠራዊቱ እንደ በፊቱ መከላከሉን ትቶ ወደ ማጥቃቱ እንዲገባ ነው የተደረገው። የኢትዮጵያ የጦር ኤክስፐርቶች ይህንን ለውጥ ያደረጉት የአካባቢው ሜዳማነት ለሜካናይዝድ ውጊያ የሚያመች መሆኑን በማጤናቸው ነው። ከዚህም ሌላ በኮሎኔል ፋንታ በላይ የሚመራው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሙሉ ትኩረቱን በዚህ ግንባር ላይ እንዲያደርግ ታዝዞ ነበር፡፡

እነ ኮ/ል አሸናፊ ገብረጻዲቅ፣ ኮሎኔል ለገሠ ተፈራ እና ኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስን የመሳሰሉ ተዋጊዎች የሶማሊያን ሠራዊት ከአየር ወደ ምድር ቀጥቅጠውታል። በመሆኑም የሶማሊያ ጦር ያልጠበቀው ሽንፈት ገጥሞታል። ለውጊያው ካሰለፋቸው ታንኮች መካከልም ብዙዎቹ ተቃጥለውበታል። በዚህም የተነሳ ሶማሊያዎቹ በነሐሴ ወር መገባደጃ ላይ ድሬዳዋን የመያዝ እቅዳቸውን እርግፍ አድርገው በመተው ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ጅግጅጋና ሐረር አዞሩት።

በመስከረም 1970 የሶማሊያ ጦር ጅግጅጋን ለመያዝ ውጊያ ከፈተ። በከተማዋ የቀረው የኢትዮጵያ ኃይል ባለው አቅም ሁሉ ከተማዋን ላለማስነጠቅ ተከላከለ። ይሁንና የሶማሊያ ጦር በሰው ኃይልም ሆነ በመሳሪያ ብዛት ስለሚበልጥ ሁለት ብርጌድ ብቻ ይዞ በሚዋጋው የኢትዮጵያ ጦር የሚመለስ አልሆነም። በተጨማሪም የሶማሊያ አየር ኃይል በውጊያው ላይ በከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ነበር።

ጳጉሜን 5/1969 የኢትዮጵያ ጦር በስልታዊ ማፈግፈግ ጅግጅጋን እንዲለቅ ታዘዘ።

በዚሁ መሰረት ጦሩ ከከተማዋ ወጥቶ በጅግጅጋና በሐረር መሀል ካለችው አነስተኛዋ የቆሬ ከተማ አቅራቢያ (ከጅግጅጋ በስተምዕራብ በኩል በ40 ኪሎ ሜትር ላይ) የመከላከያ ጣቢያውን መሰረተ። ከኦጋዴን ያፈገፈገው ጦርም በዚህ ግንባር ተሰልፎ የሶማሊያ ጦር ወደ ሐረር ከተማ እንዳይገፋ ገትሮ እንዲይዝ ተደረገ።

ሐረርን የመከላከል ውጊያ፤ የሶማሊያ ሠራዊት ከምሥራቅና የደቡብ ኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ከፍተኛ ትኩረት ያደረገው በሐረር ላይ ነው። ለዚህም ምክንያት አለው። ሐረር ረጅምና ጥንታዊ ታሪክ ያላት ከተማ በመሆኗ የሶማሊያ መሪዎች የእኛ ከተማ ናት ይሏት ነበር።

በተለይም ሐረርን ከኢማም አህመድ ኢብራሂም አል-ጋዚ ታሪክ ጋር በማያያዝ ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ ይነዙላት ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ሐረር የዘመኑ ትልቁና ሀብታሙ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር የነበረው የሐረርጌ ዋና ከተማ ነበረች። በሶስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ከነበሯት አራት ክፍለ ጦሮች መካከል በጣም ግዙፍ የሆነው የሶስተኛ ክፍለ ጦሮች ዋና የማዘዣ ጣቢያ የሚገኝባት ከተማ ነበረች።

በአራተኛ ደረጃ ሐረር ብቸኛው የአትዮጵያ የጦር አካዳሚ የሚገኝባት ከተማ ነበረች። የሶማሊያ መሪዎች ይህንን ሁሉ በማመዛዘን ነው ሐረርን የትልቋ የድል ብስራት ማወጃ ማዕከል በማድረግ ያተኮሩባት። የሶማሊያ ጦር ሐረርን የመያዝ ጥረቱን የጀመረው በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ነው።

ውጊያውንም የጀመረው ከሐረር በስተምሥራቅ በ70 ኪሎ-ሜትር (ከጅግጅጋ በስተምዕራብ በ40 ኪ.ሜ) ርቀት ላይ ባለው የቆሬ ግንባር ነው። ኢትዮጵያውያኑ በዚህ ውጊያ ሲወጠሩ፣ የሶማሊያ ሠራዊት ከጭናክሰን ከተማ አቅራቢያ ተነስቶ በጉርሱም አውራጃ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት በመራመድ የኤጀርሳ ጎሮ ከተማን ያዘ።

በዚህም ሳያበቃ ኃይሉን ለሶስት በመክፈል አንደኛውን ቡድን በትንሿ የፈላና ከተማ ከተማ አቅጣጫ ወደ ሐረር ላከው። ሁለተኛው ኃይል ከሐረር በስተሰሜን በመገስገስ የኮምቦልቻ ከተማን ከያዘ በኋላ ወደ ሐረር መግፋት ጀመረ። ሶስተኛው ኃይል ማንንም ባስደነቀ የጦር ሜዳ ጥበብ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ተጉዞ ከሐረር በስተምዕራብ ካለችው የአዴሌ ከተማ አጠገብ ደረሰ (የዚህኛው ግብረ-ሀይል ዓላማ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከድሬዳዋ አቅጣጫ ድጋፍ እንዳይመጣለት መከላከልና ሐረርን ከጀርባ መክበብ ነው)። የኢትዮጵያ ሠራዊት ሐረርን ላለማስነጠቅ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ ጀመረ።

ለውጊያው ከተሰለፈው ኃይል በተጨማሪ በተጠባባቂነት የተያዙ የመደበኛና የሚሊሻ ሠራዊት አባላት በሙሉ ሐረርን ለመከላከል እንዲሰማሩ ታዘዙ። ነገሮች ሁሉ እንዲህ በከረሩበት ጊዜ ደግሞ የሶማሊያ ሠራዊት አንድ ግብረ ኃይል ሌላ ያልታሰበ የውጊያ ግንባር ከፈተ። ይኸውም ኃይል የመጣው ከሐረር ከተማ በስተደቡብና በደቡብ ምዕራብ በኩል ነበር። በዚህ በኩል ወደ ሐረር የደረሰው የሶማሊያ ሠራዊት ከሁለት አካባቢዎች ነበር የተነሳው። የአንደኛው መነሻ በባሌ ክፍለ ሀገር የምትገኘው የኤል-ከሬ ከተማ ናት።

ከዚያች ከተማ የተነሳ አንድ የሶማሊያ ብርጌድ ሽቅብ ወደ ላይ እየተጓዘ የዋቢ ሸበሌን ወንዝ በማቋረጥ ከሐረር ከተማ በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ከምትገኘው ትንሿ የ“ፊቅ” ከተማ ገባ። ሁለተኛው ኃይል ደግሞ በኦጋዴን ካለችው የደጋሀቡር ከተማ ከተነሳ በኋላ ወደ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ እየገሰገሰ “ፊቅ” ከተማ ደረሰ። እነዚህ ሁለት ኃይሎች አንድ ላይ በመጣመር በቀድሞው የሐረር ዙሪያ አውራጃ ውስጥ ካለው የፈዲስ ወረዳ ከገቡ በኋላ ለሁለት ተከፈሉ፡፡

አንደኛው ኃይል የሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫን በመያዝ ሐረርን በደቡብ ምሥራቅ የሚያዋስነውን የሀኪም ጋራ እንዲቆጣጠር ግዳጅ ተሰጠው። ሁለተኛው ኃይል ቀጥታ ወደ ሰሜን እየተጓዘ የሐረር ከተማ ምዕራባዊ ድንበር የሆነውን የአቦከር ተራራን እንዲይዝ ታዘዘ። የሶማሊያ ኃይሎች ፍጥነት በታየበት በዚህ ዘመቻቸው ሐረርን ሙሉ በሙሉ ለመክበብ ቻሉ። አልፎ ተርፎም በደቡብና በሰሜን በምዕራብ የመጡት ግብረ ኃይሎች መድፎቻቸውን የሐረር ከተማ ተጎራባች በሆኑት የአው ሀኪም እና የድሬ ጠያራ ቀበሌዎች ውስጥ በማስቀመጥ ከተማዋን መደብደብ ጀመሩ (ኮሎኔል መንግሥቱ በመጽሐፋቸው ገጽ 472 ላይ “የሶማሊያ ጦር ሐረርን ያዘ” ይላሉ።

አንዳንድ ምንጮች ደግሞ “የሐረር ከተማ የተወሰኑ ክፍሎች በሶማሊያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ወድቀው ነበር” በማለት ጽፈዋል፤ ይሁንና በሐረር ከተማ ቆይታዬ ያነጋገርኳቸው የከተማዋ ነዋሪዎችና የያኔው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት የሐረር ከተማ ከሁሉም አቅጣጫዎች ብትከበብም በሶማሊያ ሠራዊት እንዳልተያዘች አረጋግጠውልኛል። የሶማሊያ ሠራዊት ሐረርን ቢይዝ ኖሮ ከተማዋን ማስመለስም ሆነ ለቀጣዩ ጦርነት የኢትዮጵያን ሠራዊት መልሶ ማደራጀቱ በጣም አስቸጋሪ ይሆን ነበር)። የሶማሊያ ጦር ከሐረር ከተማ በአራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደርሷል።

ታዲያ ከተማዋን ለመያዝ ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው? ሶስት ምክንያቶች አሉት። አንደኛው ኢትዮጵያ በስልጠና ላይ የነበረውን የሚሊሻ ጦር በከፊል አስመርቃ በውጊያው እንዲሳተፍ ለማድረግ መቻሏ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የነበሩትን የጦር ኃይሎች በፍጥነት አጓጉዞ በመከላከሉ ውጊያ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ መቻሉ ይጠቀሳል። ይሁንና እነዚህ ሁለት ምክንያቶች እንደ ደጋፊ ተደርገው የሚወሰዱት እንጂ ዋናዎቹ ምክንያቶች አይደሉም።

ሐረርን በሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት ከመወሰድ የዳነችበት ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያደረገው ተጋድሎ ነው። የኢትዮጵያ አየር ኃይል በወቅቱ ጥቂት የጦር አውሮፕላኖች ናቸው የነበሩት። ከሶቪየት የተገኙት አውሮፕላኖችም በዚያን ጊዜ ወደ ሀገር ቤት አልገቡም። ነገር ግን የአየር ኃይሉ አብራሪዎች በጣም የተዋጣላቸው በመሆናቸው ዒላማቸውን ሳይስቱ ይመቱ ነበር።

በድሬዳዋ (ጀልዴሳ) ግንባር በርካታ ታንኮችን ከጥቅም ውጪ እንዳደረጉት ሁሉ በዚህም ግንባር የሶማሊያ መድፎችንና ሞርታሮችን በመደምሰስ ከዒላማቸው አሰናክለዋል። ታዋቂው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪና የህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሜዳይ ተሸላሚ ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ብቃቱን ካሳየባቸው ግዳጆች አንዱ ያ ሐረርን ለመከላከል የተደረገው ውጊያ ነው። በነገራችን ላይ የሶማሊያ ሠራዊት ሐረርን ለመያዝ በተደረገው ዘመቻ መድፍና የቢ ኤም ሮኬቶችን እንጂ ታንክ መጠቀሙ አልተዘገበም። ይህም የአካባቢው ተራራማነት ለሜካናይዝድ ውጊያ የማያመች በመሆኑ ይመስለኛል፡፡

የሶቪየት፣ የኩባና የደቡብ የመን አጋርነት

ነሀሴ ወር 1970። ሶቪየት ህብረት ለመጨረሻ ጊዜ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬን ወደ ሞስኮ ጠራቻቸው። በኃይል የያዙትን የኦጋዴንን ግዛት እንዲለቁ እና ጉዳዩን በሰላም እንዲጨርሱም መከረቻቸው። ፕሬዚዳንት ዚያድ ግን በእምቢታቸው ጸኑ። በመሆኑም የኢትዮጵያ መሪዎችን “ታገሱ! አትቸኩሉ” እያለች ስትመልስ የነበረው ታላቋ ሶቪየት የጦርነቱን አካሄድ የቀየረ ተግባራዊ ርምጃ ወሰደች።

ቀደም ሲል በተስማማችው መሰረት በመስከረም 1970 ለኢትዮጵያ የ385 ሚሊዮን ዶላር መሳሪያ የሚሸጥበትን ሂደት ገቢራዊ ማድረግ ጀመረች። በመርከቦቿ ወደ ሶማሊያ ነዳጅ ማጓጓዙን አቋረጠች። ለሶማሊያ የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭንም አቆመች። ሶማሊያ የሶቪየትን ርምጃ “ሕገ-ወጥነት ነው” ስትል ኮነነችው።

በማስከተልም በህዳር ወር 1970 በሀገሯ የነበሩትን የሶቪየት ወታደራዊ አማካሪዎችና ሲቪል ሠራተኞች አባረረች። ይህንንም ተከትሎትም ሶቪየት ህብረት ለመጀመሪያ ጊዜ ሶማሊያን “ወራሪ” በማለት አወገዘቻት። ወረራውን ለመቀልበስ ከኢትዮጵያ ጋር በሙሉ ፍላጎት እንደምትሰራም አስታወቀች። በዚህም መሰረት እንደ እርሷ ሁሉ የኢትዮ-ሶማሊያ ውዝግብን በሰላም ለመቋጨት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩትን ኩባና ደቡብ የመንን የሚያካትት ወታደራዊ “ህብረት” ተመሰረተ።

የኩባ ሶሻሊስት ሪፐብሊክ በጦርነቱ ሂደት በቀጥታ ከተሳተፉት ሁለት ሀገራት አንዷ ናት። በወቅቱ ኩባ ያስመጣችው የተዋጊ ብዛት ከ16, 000 እስከ 20, 000 ይገመታል። ከዚህ ኃይል መካከል ሁለቱ ሜካናይዝ ብርጌድ ነው። ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኩባ ጦር የሚመራው የሀገሪቱ ም/የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩት በጄኔራል አርናልዶ ኦቾዋ ሲሆን፤ በዘመኑ በአንጎላ ተመድቦ የነበረውንም የኩባ የጦር ኃይል የሚያዙት እርሳቸው ናቸው። ኩባ ከወታደሮቿ በተጨማሪ የህክምና ሠራተኞችን ልካለች፡፡

ደቡብ የመን (የመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ) ደቡብ የመን ለጦርነቱ የመደበችው 2000 መድፈኞችን ነው። እነዚያ መድፈኛ የመኒዎች በቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆኑም አልሞ-ተኳሽ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ ተደንቆላቸዋል። ደቡብ የመን ለኢትዮጵያ 30 ታንኮችን ሰጥታለች። ሶስቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ የሶማሊያ አጋር ነበሩ። ሶማሊያ የመሬት ጥያቄዋን ባነሳችበት ጊዜም ሀሳቧን እንድትቀይር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ከዚህም አልፎ ፕሬዚዳንት ካስትሮ “ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያና ደቡብ የመን በኮንፌዴሬሽን ተያይዘው አንድ ታላቅ ህብረት መመስረት አለባቸው” የሚል ሃሳብ እስከ ማቀንቀን ደርሰው ነበር ፡፡

ይህን ተከትሎም ሶማሊያ በግልጽ የሶሻሊዝምን ካባ ወርውራ ወደ ምዕራቡ ዓለም መጓዝ ጀምራለች ። ቀደም ብሎም ቢሆን ከምዕራባዊያን ጋር ድብቅ ግንኙነቶችን ማድረግ እንደ ጀመረች አንዳንድ ምንጮች ያወሳሉ። ለምሳሌ ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ካለው አንድ ተቋም የተገኘ ጥናታዊ ጽሑፍ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸጥ በድብቅ የተስማሙት ወረራው በተጀመረበት የሐምሌ ወር (1969) መሆኑን ይገልጻል። ከዐረብ ሊግ ሀገራት መካከል ግብጽና ሳዑዲ ዐረቢያ በድብቅ ሶማሊያን ይረዷት ነበር። ሊቢያና አልጄሪያ ግን የኢትዮጵያ ደጋፊ ነበሩ።

የኢትዮጵያ የመልሶ ማጥቃት ቅድመ-ዝግጅት

የሶማሊያ ሠራዊት ሐረርን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት ከከፈሸበት በኋላ ይዞታውን ለማስፋት አልሞከረም። ሶቪየት ህብረት፣ ኩባ እና የመን ኢትዮጵያን በመደገፍ በጦርነቱ ውስጥ መግባታቸውን ሲረዳ በያዛቸው አካባቢዎች መከላከያውን ማጠናከሩን ነው የመረጠው፡፡

ኢትዮጵያ በበኩሏ የመልሶ ማጥቃት ዝግጅቷን አጧጧፈች። ሶቪየት ህብረት በቃሏ መሰረት በታህሳስ ወር 1970 (ስድሳ ሰባት) የሚግ ተዋጊ ጄቶችን ለኢትዮጵያ ሰጠች። 600 ታንኮች፣ ከ200 በላይ ብረት ለበሶች፣ 150 ያህል መድፎች፣ 100 የቢ.ኤም ሮኬት ማስወንጨፊያዎች፣ ዙ-23 የአየር መቃወሚያዎች፣ ቀላልና ከባድ መትረየሶች፣ ቦምቦች፤ ሮኬቶች፣ ወዘተ… ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡

ዘመናዊ የሆኑ ሶቪየት ሰራሽ ዋዝ ጂፖች፣ ሽፍን ወታደራዊ መኪናዎች፣ “ኦራል”፣ “አይፋ” እና “ካማዝ” የሚባሉ ከባድ መኪናዎችም ለኢትዮጵያ ተሰጡ። የአውሮፕላንና የሂሊኮፕተር አብራሪዎች፣ ወታደራዊ መኮንኖችና የውጊያ አሰልጣኞች፣ የፈንጂ መሐንዲሶች፣ ወዘተ…. በአስቸኳይ ወደ ሶቪየት ህብረት እየተላኩ ተጨማሪ ስልጠና እንዲወስዱ ተደረገ፡፡

በሀገር ውስጥ ደግሞ ቀደም ብለው የተጀመሩት የፓራ-ኮማንዶ፣ የአየር ወለድ፣ የባህር ወለድ፣ የከባድ መሳሪያ ተኳሾች፣ የበታች አዛዦች፣ የመደበኛ ተዋጊዎች እና የሚሊሻ ወታደሮች ስልጠናዎች ተጠናክረው ቀጠሉ።

የያኔውን ታሪክ በትክክል ለማወቅ እንዲቻለን የኢትዮጵያ መንግሥት ስልጠና ያካሄደባቸውን ማዕከላት ዝርዝር ማሳወቅ ያለብኝ ይመስለኛል። “ታጠቅ የጦር ሰፈር”፡- በሸዋ ክፍለ ሀገር ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ (20 ኪሜ) የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ በታሪኳ የገነባችው ትልቁ የጦር ማሰልጠኛ ማዕከል ነው፡፡

በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት በታጠቅ ይሰለጥኑ የነበሩት ሚሊሻዎች ናቸው። ይህ ማዕከል በአንድ ጊዜ መቶ ሺህ ሰልጣኞችን ለመቀበል ይችላል።

  1. “ኩሃ የጦር ሰፈር”፡- በትግራይ ክፍለ ሀገር የሚገኝ የጦር ማሰልጠኛ ነው። በዚህ ማዕከል የሰጠለኑት የመደበኛ ጦር አባላት ናቸው፡፡
  2. “አዘዞ ጦር ሰፈር”፡- በጎንደር ክፍለ ሀገር ነው የሚገኘው። በዚህኛውም ማዕከል የሰለጠኑት የመደበኛ ጦር አባላት ናቸው።
  3. “ለምለም ጦር ሰፈር” (ለምለም ግቢ)፡- በሸዋ ክፍለ ሀገር በደብረ ዘይት ከተማ የሚገኝ የጦር ማሰልጠኛ ነው። በዚህ ማዕከል የሰለጠኑት መደበኛ ተዋጊዎችና አየር ወለዶች ናቸው።
  4. ዝዋይ ጦር ሰፈር፡- በሸዋ ክፍለ ሀገር ነው የሚገኘው። በዚህ ማዕከል የሰለጠኑት ፓራኮማንዶዎች ናቸው።
  5. አዋሳ የጦር ሰፈር፡- በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ከአዋሳ ሀይቅ ዳር ነው የሚገኘው። በዚህኛውም የጦር ሰፈር የሰለጠኑት የፓራኮማንዶ ተዋጊዎች ናቸው፡፡
  6. ለገዳዲ የጦር ማሰልጠኛ፡- ከአዲስ አበባ በሰሜን አቅጣጫ በ20 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። በዚህኛውም ማዕከል የሰለጠኑት ፓራኮማንዶዎች ነበሩ።
  7. አዋሽ አርባ የጦር ትምህርት ቤት፡- በሸዋ እና በሐረርጌ ድንበር አቅራቢያ (ከአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ) ነው የሚገኘው። በዚህ ማዕከል የሰለጠኑት በአብዛኛው የታንክ፣ የመድፍና የሌሎች ከባድ መሳሪያ ተኳሾች ሲሆኑ አንድ የፓራኮማንዶ ብርጌድም በማዕከሉ ሰልጥኗል። የተዋጊ ወታደሮች፣ የመኮንኖችና የከባድ መሳሪያ ተኳሾች ስልጠና በተጧጧፈበት ወቅት የጦር መሳሪያዎቹ ወደ ኢትዮጵያ በመጓጓዝ ላይ ነበሩ። ታዲያ ከባድ መሳሪያዎቹ በታቀደላቸው ጊዜ ለመልሶ ማጥቃት ዘመቻው መዋላቸውን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ መሪዎች የታንከኛና የመድፈኛ ተኳሾችን ስልጠና ከአዋሽ አርባ ወደ አሰብ ለማወዛር ተገደዋል።

ይህም የተደረገው በጉዞ የሚባክነውን ጊዜ ለመቆጠብ እንዲቻል ተብሎ ነው (ታንኮቹን ከአሰብ ወደ ምሥራቅ ግንባር በማጓጓዙ ሂደት የኩባ ጓዶች ተሳታፊ ነበሩ)።

የኢትዮጵያ የፕሮፓጋንዳና የዲፕሎማሲ ሥራዎች፤ ኢትዮጵያ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ለመክፈት ያቀደችው በየካቲት ወር ሁለተኛው አጋማሽ (1970) ነበር። ከዚያ በፊት በሁሉም የእርከን የሚሠሩ ተግባራትን ማከናወን  ነበረባት። ከእነዚህ ተግባራት መካከል አንዱ ቅስቀሳ እና ፕሮፓጋንዳ ነው። ይህም በሶስት ዘርፎች የተከፈለ ነው።

  1. በኢትዮጵያ ሕዝብና ሠራዊት ላይ ያነጣጠረ ቅስቀሳ እና ፕሮፓጋንዳ፡ ዓላማው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጨረሻው ድል እስኪገኝ ድረስ ለዘመቻው ደጀን ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ነው። የፕሮፓጋንዳ ሥራው በዋናነት የሚካሄደው በመገናኛ ብዙኃንና በጋዜጦች ነው። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና የኢትዮጵያ ሬድዮ በፕሮፓጋንዳው ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ሲሆን የአዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦችም ለጦርነቱ ሙሉ ሽፋን እንዲሰጡት ተደርገዋል፡፡

ከዚህ ሌላ ለሠራዊቱ አባላት የሚሰራጭ “ታጠቅ” የተሰኘ ጋዜጣ በወረራው ማግስት ተፈጥሯል። የኢትዮጵያ አርቲስቶችና ደራሲያን በቅስቀሳው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ስለሀገር እና ስለ ዳር ድንበር የሚያወሱ ዘፈኖች፣ ድራማዎችና ጭውውቶች እየተዘጋጁ ለሕዝቡና ለሠራዊቱ እንዲቀርቡ ተደርገዋል።

በየቀበሌውም የቲያትርና የድራማ ቡድኖች ተቋቁመው ሕዝቡን ይቀሰቀሱት ነበር። የመልሶ ማጥቃት ውጊያ ሲጀመር ደግሞ የኢትዮጵያ ሬድዮ የጦርነቱን ውሎ በቀጥታ ይዘግብ ነበር። በዚያ ዘመን ለቅስቀሳ ሥራ በስፋት ያገለገለው ዋነኛ መፈክር “አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት” የሚለው ነው፡፡

  1. በሶማሊያ ሕዝብና ሠራዊት ላይ ያነጣጠረ ፕሮፓጋንዳ ዓላማው የሶማሊያን ሕዝብ ከዚያድ ባሬ አመራር መነጠልና በሶማሊያ ሠራዊት ላይ ሥነ-ልቦናዊ ሽብር መፍጠር ነው። በዚህም መሰረት ሐረር እና አዲስ አበባ ያሉት የኢትዮጵያ ሬድዮ ቅርንጫፎች በሶማሊኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የዚያድ ባሬን መንግሥት ነውር እና ውስጣዊ ገመና የሚተረትሩ ተከታታይ ፕሮግራሞችን እንዲያስተላልፉ ተደርጓል። በተጨማሪም ልዩ ሌላ በራሪ ጽሑፎች እየተዘጋጁ በአውሮፕላንና በተወንጫፊ ሮኬቶች አማካኝነት ለሶማሊያ ሕዝብ እንዲበተኑ ተደርገዋል።
  2. በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረ ፕሮፓጋንዳ ዓላማው የሶማሊያን መንግሥት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት ማዋረድና ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ድል ተጨማሪ ድጋፍ ማስገኘት ነው። በዚህ መሰረት ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ መረጃ የሚሰጥ ራሱን የቻለ ጽ/ቤት ተቋቁሟል።

“የፕሬስ ሳምንት” በተባለ ፕሮግራም አማካኝነትም የውጪ ጋዜጠኞች ኢትዮጵያን እየገበኙ ጦርነቱ ያደረሰውን ጥፋት እንዲመለከቱ ተደርጓል። በሌላ በኩል የዘመኑ የኢትዮጵያ መሪዎች በዓለም ዙሪያ ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራ ሠርተዋል። በውጤቱም የሶሻሊስቱ ካምፕ የሶማሊያን ወረራ ሊያወግዝ በቅቷል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም የሶማሊያን ወረራ በማውገዝ ከኢትዮጵያ ጋር ቆሟል፡፡

የምዕራብ ሀገራት ግን ሶማሊያ ወራሪ መሆኗን እያወቁ እንኳ ሊያወግዟት አልፈቀዱም። ይህም የሆነው ሶቪየት ህብረት የኢትዮጵያ አጋር ሆና በመገኘቷ ነው፡፡

ኢትዮጵያ- ከመከላከል ወደ ማጥቃት፤ የካቲት 1970። ኢትዮጵያ የማጥቃት ዘመቻዋን የምትከፍትበት ወሳኝ ወቅት መምጣቱን የሀገሪቱ መሪዎች ተናገሩ። በመሆኑም ስልጠናውን በብቃት ያጠናቀቀው ሠራዊት በሚከተለው ሁኔታ ተደራጀ።

  1. በምሥራቅ ግንባር

 

  • አራት ታንከኛ ብርጌድ
  • ሁለት መድፈኛ ብርጌድ
  • ሁለት የከባድ መሳሪያ (ቢ.ኤም) ተኳሽ ብርጌድ • ሁለት መደበኛ ክፍለ ጦር
  • አራት ሕዝባዊ ሚሊሻ ክፍለ ጦር
  1. በደቡብ ግንባር
  • ሁለት ሕዝባዊ ሚሊሻ ክፍለ ጦር
  • አንድ መድፈኛ ሻለቃ
  • አየር ኃይል

 

  • የኢትዮጵያ አየር ኃይል በጠቅላላው ከታጠቃቸው 75 አውሮፕላኖች መካከል 40 የሚሆኑትን ለግዳጅ አሰልፏል። የኢትዮጵያ ጦር ካሰለፈው ኃይል በተጨማሪ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው አንድ ክፍለ ጦር የሚሆን የኩባ ሠራዊትና አንድ የደቡብ የመን መድፈኛ ብርጌድም በምሥራቁ ግንባር ተሰልፈዋል፡ ፡ (የኢትዮጵያ ሠራዊት ለረጅም ጊዜ ሲከላከል የቆየው በሁለት መደበኛ ክፍለ ጦሮች፤ ሶስት ሚሊሻ ክፍለ ጦሮች፣ ሁለት ሜካናይዝድ ብርጌድና ሁለት ነበልባል ብርጌድ ብቻ ነው)።

የኢትዮጵያ ሠራዊት የማጥቃት ዘመቻውን በሚከተለው ሁኔታ ለመፈጸም ነበር ያቀደው፡፡

  1. ሶስት ፓራኮማንዶ ብርጌዶችን ከጅግጅጋ በስተሰሜን ባሉት የጭናክሰን እና የማርዳፓስ ገዥ መሬቶች ላይ በጃንጥላ (ፓራሹት) በማውረድ ድንገተኛ ጥቃት መክፈት
  2. ከአሰብ የተነሳ አንድ ታንከኛ ብርጌድና አንድ መድፈኛ ብርጌድ በጅቡቲ ድንበር ጥግ እየተጓዘ አውበሬ (ተፈሪ በር) በምትባለው ከተማ አቅጣጫ ወደ ጅግጅጋ እንዲመጣና ጥቃት እንዲከፍት ማድረግ
  3. በቆሬ ግንባር ያለው የኢትዮጵያ ጦር ወደ ምሥራቅና ወደ ሰሜን እንዲነቃነቅ በማድረግ በጅግጅጋና በጉርሱም አውራጃ ያለውን የሶማሊያ ሠራዊት እንዲከብብ ማድረግ
  4. በተመሳሳይ መንገድ ከአሰብ የተነሳ ሁለት ታንከኛ ብርጌድና አንድ መድፈኛ ብርጌድ በድሬዳዋ በስተምሥራቅ በኩል እየተጓዘ ጀልዴሳ በተባለው ቦታ የተከማቸውን የሶማሊያ ሠራዊት እንዲያጠቃ ማድረግ
  5. የሶማሊያ ጦር ከላይ በተጠቀሰው መንገድ በተከፈበት ጥቃት ሲበረገግ በኃረር የሚገኝ አንድ ግብረ ሀይል ወደ ሰሜን ተጉዞ በኮምቦልቻና ኤጄርሰ ጎሮ የከተመውን የሶማሊያ ሠራዊት እንዲያጠቃ ማድረግ
  6. በሀረር ያለ ሌላ ግብረ ኃይል ወደ ደቡብ ተነቃንቆ ሀኪም ጋራ እና አቦከር አቅራቢያ የከተመውን የሶማሊያ ሠራዊት ካጠቃ በኋላ እግር በእግር እየተከተለው በፈዲስ ወረዳ በኩል ወደ ፊቅ አቅጣጫ እንዲጓዝ፤ ብሎም ወደ ኦጋዴን እንዲገሰግስ ማድረግ
  7. በባሌ እና ነጌሌ ቦረና የተመደቡት ሁለት ሚሊሻ ክፍለ ጦሮች ከአየር ኃይል ጋር በመሆን በደቡብ አቅጣጫ እንዲያጠቁ ማድረግ ኮሎኔል መንግሥቱ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ይህንን የውጊያ እቅድ ያወጣችው የሶቪየትና የኩባ አማካሪዎች ከመምጣታቸውና ኢትዮጵያ ከሶቪየት ያኘችውን የመሳሪያ ድጋፍ ከመረከቧ በፊት ነበር።

በዚያ ዕቅድ መሰረት የታንክና የመድፍ ተኳሾች በአሰብ ላይ ስልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ታንካቸውን ይዘው ወደ ጦርነቱ ቦታ እንዲሄዱ ነበር የተፈለገው። የውጊያው የመጨረሻ ፕላን ላይ ውይይት በሚደረግበት ወቅት የሶቪየት አማካሪዎች “ዕቅዱ ሶማሊያን ለመውረር የተዘጋጀ ይመስላል” በማለታቸው ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ውጥን ለመከለስ ተገዳለች።

ሶቪየቶች ይህንን እንዲሉ ያደረጋቸው ኢትዮጵያ ካደራጀችው ሜካናይዝድ ጦር ውስጥ ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው ለሰሜን ሶማሊያ ቅርብ በሆነችው የጅግጅጋ መስመር እንዲሰለፍ በመደረጉ ይመስላል (ሀርጌሳ ከጅግጅጋ በቅርብ ርቀት ላይ ያለች መሆኗን ልብ በሉ)፡፡

የሶቪየት ህብረት እና የኩባ አጋሮች ከሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ብዙ ከተወያዩ በኋላ የኢትዮጵያ ጦር በሚከተለው አኳኋን እንዲያጠቃ ተወሰነ።

  1. የፓራኮማንዶ ጦር በአውሮፕላን ተጓጉዞ ከጅግጅጋ ጀርባ ባለችው የ“ጭናክሰን” ቀበሌ ላይ እንዲከማችና ውጊያውን ከዚያ እንዲጀምር
  2. በቆሬ ግንባር ያለው ጦር በሜካናይዝድ ተጠናክሮ ውጊያውን እንዲጀምር
  3. የኩባ ሜካናይዝድ ጦር እና የየመን መድፈኛ ብርጌድ ከኢትዮጵያ ሜካናይዝድ ጦር ጋር በመቀናጀት በጀልዴሳ አካባቢ ያለውን የሶማሊያ ሰራዊት እንዲያጠቁ፣ ግዳጃቸውን ከጨረሱ በኋላም ወደ ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ በማምራት በስፍራው ያሉ የኢትዮጵያ ከተሞችን ነጻ እንዲያወጡ
  4. ከሐረር የተነሳው ጦር በኮምቦልቻ እና በፈዲስ አቅጣጫዎች ማጥቃት እንዲጀምር፣ ከዚያም ፊቅን ይዞ ወደ ኦጋዴን እንዲዘምት
  5. በባሌና በነጌሌ ቦረና አቅጣጫዎች የተመደቡ ሚሊሻ ክፍለጦሮች በተመሳሳይ ቀን ማጥቃት እንዲጀምሩ
  6. የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሁሉም አቅጣጫዎች የተጠናከረ ድብደባ እንዲፈጽም ተወሰነ።

የተጠናከረ የማጥቃት ዘመቻ እና የማይቀረው ድል

የካቲት 23/1970። የኢትዮጵያ ጦር በጭናክሰን እና በቆሬ በኩል በጅግጅጋ ላይ የተጠናከረ ጥቃት ከፈተ። የሶማሊያ ጦር ጥቃት ይመጣብኛል ብሎ ባልጠበቀው አቅጣጫ በመወጋቱ ተደናገጠ። ጅግጅጋን ላለመልቀቅ መሟሟት ጀመረ። ሶማሊያዎች በዚህ ውዥንብር ውስጥ እያሉ በጀልዴሳ ግንባር ሌላ ጥቃት ገጠማቸው። የኢትዮጵያ አየር ኃይልም እስከ ሶማሊያ ድንበር እየገባ የሶማሊያ ሠራዊትን የአቅርቦትና የእደላ መስመሮችን በመደብደብ ከጥቅም ውጪ አደረጋቸው።

የሶማሊያ ሠራዊት ጅግጅጋን ከለቀቀ ትልቅ የሞራል ውድቀት እንደሚገጥመው ያውቃል። በመሆኑም ከጅግጅጋ በስተምዕራብ በኩል ባለው የካራማራ ተራራ ላይ ማዘዣውን በመሥራት በከፍተኛ ደረጃ ተከላክሏል። ሆኖም በለስ አልቀናውም። ጥቃቱ በሁሉም ግንባር የተከፈተ በመሆኑ አጋዥ ሠራዊት ከየትም ማንቀሳቀስ አልቻለም፡፡

በመሆኑም የካቲት 26/1970 በካራማራ ተራራ ላይ ከባድ ሽንፈት ገጠመው። ጅግጅጋን ለኢትዮጵያ ሠራዊት በመልቀቅ ወደ ሀርጌሳ መስመር አፈገፈገ። የኢትዮጵያ ሠራዊትም የካቲት 27/1970 ንጋት ላይ የጅግጅጋ ከተማን ያዘ። የኢትዮ-ኩባ-የመን ጥምር ጦር በጀልዴሳ የተከማቸውን የሶማሊያ ሠራዊት ለሶስት ተከታታይ ቀናት ወጋ። ይህ ውጊያ ታንክ ከታንክ ጋር የተፋጨበት በመሆኑ በርካታ የጦር መሪዎች “የጦርነት ፊልም ይመስል ነበር” እያሉ አድናቆታቸውን ሰጥተውታል፡፡

የሶስቱ ሀገራት ጥምር ጦር ከሶስት ቀን በኋላ ግዳጁን በማጠናቀቅ በቆላው ምድር ላይ ገሰገሰ። የካቲት 30/1970 ግዳጁን በማጠናቀቅ ከኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር በስተደቡብ ያሉ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ። ከሀረር የተንቀሳቀሰው ጦር ደግሞ በሰሜን በኩል ግዳጁን በቀላሉ በመወጣት ኮምቦልቻን አልፎ እስከ ኤጀርሳ ጎሮ ድረስ ገስግሷል። ከሐረር በስተደቡብ የተነቃነቀው ግብረ ኃይል ግን ከሶማሊያ ሠራዊት ከፍተኛ የሆነ መከላከል ገጥሞታል። የኢትዮጵያ ጦር የካቲት 29/1970 ፈዲስን የተቆጣጠረው ከባድ መስዋዕትነት ከከፈለ በኋላ ነው።

በባሌ እና በነጌሌ ቦረና ግንባር የተሰለፈው ጦር ግን ጠንካራ መከላከል ሳያጋጥመው እስከ ጠረፍ ድረስ እየገሰገሰ የኢትዮጵያ ከተሞችን ሁሉ በቀላሉ ለመቆጣጠር ችሏል። የኢትዮጵያ ጦር ባገኘው ድል ተብቃቅቶ አልቆመም።

ከመጋቢት 1/1970 ጀምሮ ሁሉም ኃይሎች ወደ ኦጋዴን አቅጣጫ ዘምተዋል። ሆኖም የሶማሊያ ሠራዊት በከፍተኛ የሞራል ውድቀት ውስጥ ገብቶ ስለነበር ጠንካራ ጦርነት ይደረግበታል ተብሎ በታሰበው የኦጋዴን መሬት ላይ የሚረባ ውጊያ ለማድረግ አልተቻለውም።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ጦር መጋቢት 1/1970 ፊቅን፣ መጋቢት 3/1970 ደጋሃቡርን፣ መጋቢት 4/1970 ቆራሄን፣ ሰገግንና ቀብሪ ደሃርን፣ መጋቢት 5/1970 ወልወልንና ዋርዴርን፣ መጋቢት 7/1970 ጎዴን ያለ ምንም ውጊያ ተቆጣጥሯል።

የኢትዮጵያ ጦር የመልሶ ማጥቃት ውጊያውን በከፍተኛ ፍጥነት ያገባደደ በመሆኑ አካሄዱ የሶማሊያ መሪዎችን በጣም አስፈርቶአቸው ነበር። ይህን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ “ኢትዮጵያ ሀገራችንን ልትወርር ስለሆነ እያንዳንዱ ዜጋ ለውጊያው ይሰለፍ” የሚል አዋጅ አስነግረዋል። ይሁንና የኢትዮጵያ ጦር ኦጋዴንን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ በኋላ በድንበሩ ላይ ቆሟል፡፡

ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ሶማሊያን ማሸነፋቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ የድሉን ብስራት በድምቀት እንዲያከብር አዋጅ አስነገሩ። በተለይም የኢትዮጵያ ጦር ስትራቴጂካዊውን የካራማራ ተራራን የተቆጣጠረበት ውጊያ የድሉን ቁልፍ ያስጨበጠ በመሆኑ በብሄራዊ ደረጃ መዘከር እንዳለበት አስታወቁ። መላው ኢትዮጵያ ሕዝብ የካራማራውን ድል በቅድሚያ በአውራጃ ደረጃ በተቋቋሙ ኮሚቴዎች አማካኝነት በየአካባቢው አከበረ። በማስከተልም ድሉ በጅግጅጋ ከተማ በብሄራዊ ደረጃ በተዘጋጀው ታሪካዊ ክብረ-በዓል ተከበረ።

/የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ ጽሁፍ በከፊል የተወሰደ/

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You