ሱቱሜ ከበደ በቶኪዮ ማራቶን ተከታታይ አሸናፊ ሆነች

የፕላቲንየም ደረጃ በተሰጠው የቶኪዮ ማራቶን አስቀድሞ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነቱን በመያዝ አጠናቀዋል:: ከዋና ዋናዎቹ የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው የቶኪዮ ማራቶን ስመጥር ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች የተካፈሉበት በመሆኑ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ ነው:: እንደ ቶኪዮ ማራቶን ባሉ ታላላቅ ውድድሮች የሚመዘገበው ሰዓት የዓመቱ ተጠባቂ የሆነውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ጨምሮ ለሌሎች ውድድሮች አትሌቶችን ሊያስመርጥ የሚችል በመሆኑም ትልቅ ትኩረት የሚሰጠውም ነው::

ያለፈው ዓመት የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊዋ አትሌት ሱቱሜ ከበደ በድጋሚ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን በታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት መሆን ችላለች:: ርቀቱን ያጠናቀቀችበት 2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ በጃፓን ከተመዘገቡ ፈጣን ሰዓቶች ቀዳሚ ሆኗል። አትሌት ሱቱሜ ውድድሩ ከመጀመሩ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች በኋላ ወደፊት በመውጣት ግማሽ ማራቶኑን ለማጋመስ የፈጀባት 1ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ነበር:: በሁለተኛው አጋማሽ ግን ፍጥነቷ ዝግ በማለቱ የተሻለ ፈጣን ሰዓት ሳታስመዘግብ ቀርታለች። ያም ሆኖ ያለተቀናቃኝ ሩጫውን ተቆጣጥራ እስከ መጨረሻ በመጓዝ አሸናፊነቷን ልታረጋግጥ ችላለች::

በውድድሩ የሱቱሜ የበላይነት በግልጽ የታየበት ቢሆንም ኬንያዊቷ ዊንፍሪዳ ሞሲት ግን ፍጥነቷን እየጨመረች በመጨረሻዎቹ ርቀቶች እጅግ በመቅረቧ ለአሸናፊነት የሚያበቃት ሁኔታ ላይ ነበረች:: በቅርቡ የቤንጋዚን ግማሽ ማራቶንን በአሸናፊነት ያጠቀቀችው አትሌት 25 ሰከንዶችን ብቻ ዘግይታ በመግባትም በቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ፈፅማለች:: ኢትዮጵያዊቷ ሃዊ ፈይሳ ደግሞ 2ሰዓት ከ17 ደቂቃ ከ00 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆናለች::

በርካታ ኬንያውያንና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተካፈሉበት የዘንድሮው የቶኪዮ ማራቶን በውድድሩ ልምድ ካላት ሱቱሜ ባለፈ የቀድሞ የዓለም ቻምፒዮኗ ጎተይቶም ገብረስላሴ፣ ደጊቱ አዝመራው፣ ሮዝመሪ ዋንጂሩን የመሳሰሉ አትሌቶች የተካፈሉበት ሲሆን፤ እነዚህ አትሌቶችም እስከ 10ኛ ባለው ደረጃ ውድድራቸውን ፈጽመዋል::

ኬንያዊያን አትሌቶችን ጨምሮ ኡጋንዳዊው የ5ሺ እና 10 ሺ ሜትር ክብረወሰን ባለቤቱ ጆሽዋ ቼፕቴጊ የተሳተፉበት የወንዶቹ ውድድር ከባድ ፉክክር ይታይበታል በሚል አስቀድሞ ግምት ያገኘ ነበር:: እስከ 25ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ርቀቱን በሚመሩት አትሌቶች መካከል ብርቱ ፉክክር የታየ ቢሆንም ከዚያ በኋላ በነበሩት ርቀቶች ግን መቀጠል አልቻለም። ከ30ኛው ኪሎ ሜትር አንስቶም ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ታደሰ ታከለ፣ ደረሰ ገለታ እና ኬንያዊው ቲቱስ ኪፕሩቶ አሸናፊ ሊያደርጋቸው በሚችለው ፍጥነት የእርስ በእርስ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል:: በተለይ የኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች የእርስ በእርስ እልህ አስጨራሽ ፉክክር የስፖርት ቤተሰቡን የሳበና በጎዳና ላይ ውድድሮች ከተለመደው ውጪ የሰከንዶች ልዩነት የታየበት ነበር::

በዚህም እአአ በ2023 የበርሊን ማራቶን ተሳትፎ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት ታደሰ ታከለ ከታላላቆቹ የማራቶን ሩጫዎች አንዱ በሆነው የቶኪዮ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ ሊሆን ችሏል:: ከሀገሩ ልጅ ጋር ከፍተኛ ፉክክር በማድረግ ያስመዘገበው ሰዓትም በርሊን ላይ ከገባበት በአንድ ሰከንድ በማሻሻል 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ ገብቷል:: እአአ በ2021 ከ20 ዓመት በታች የ3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ ታደሰ በማራቶን ውድድር ሲሳተፍ ይህ ሦስተኛው ነው:: አትሌቱ ከድሉ በኋላም ‹‹በደንብ የተዘጋጀሁ ቢሆንም ውጤቱ ከጠበቅኩት በላይ ነው፤ በእርግጥ እስከ ተወሰነ ርቀት አሸናፊ ስለመሆኔም እርግጠኛ አልነበርኩም:: ከዚያም ለራሴ ለድል መሮጥ እንዳለብኝ ነገርኩት፤ በዚህም ደስ ብሎኛል›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል::

በውድድሩ የአሸናፊነት ግምት ያገኘውና እስከ መጨረሻ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ያደረገው አትሌት ደረሰ በበኩሉ 28 ሰከንዶችን ዘግይቶ በሁለተኛነት አጠናቋል። ኬንያዊያኑ ቪሰንት ኪፕኬሞይ እና ቲቱ ኪፕሩቶ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያኑን አትሌቶች ተከትለው በመግባት አጠናቀዋል። በመም የረጅም ርቀት ሩጫ ስመጥር የሆነውና የኦሊምፒክ የወቅቱ የ10ሺ ሜትር ባለድል ኡጋንዳዊ አትሌት ጆሹዋ በበኩሉ 9ኛ በመሆን ፈጽሟል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You