
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ማጣሪያ ከዩጋንዳ አቻቸው ጋር ዛሬ የመልስ ጨዋታቸውን በሜዳቸው ያከናውናሉ። ሉሲዎቹ ያለፈውን ሽንፈት ለመቀልበስ ዩጋንዳን በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍም ይጠበቅባቸዋል።
በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ከቀናት በፊት በዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን የ2 ለምንም ሽንፈት የደረሰበት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) የመልስ ጨዋታቸውን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ዛሬ ከሰዓት በኋላ ሲያከናውን፣ ሁለተኛውን ዙር ማጣሪያ ለመቀላቀል ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።
በአዲሱ አሠልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የሚመሩት ሉሲዎቹ ከካምፓላ መልስ ወደ ልምምድ የተመለሱ ሲሆን፤ ከቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የገባው የዩጋንዳ ቡድንም ጨዋታው በሚካሄድበት የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
32 ቡድኖች የሚሳተፉበት ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ዙሮች ያሉት ሲሆን፤ በደርሶ መልስ ጨዋታ ድምር ውጤት አሸናፊ የሚሆኑ 16 ቡድኖች ቀጣዩን ዙር የሚቀላቀሉ ይሆናል። ከጠንካራዋ ዩጋንዳ ጋር በማጣሪያው የተደለደለችው ኢትዮጵያም ወደ ቀጣዩ ዙር ለመግባት በዛሬው ጨዋታ ያለፈውን ሽንፈት መቀልበስ የግድ ይላታል።
በመጀመሪያው ጨዋታ ባለቀ ሰዓት 2 ግብ የተቆጠረባቸው ሉሲዎቹ ለሁለተኛው ዙር ጨዋታ ለማለፍ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት ቢያንስ 3 ግብ በማስቆጠር መረባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣት ይጠበቅባቸዋል። በሁለት ፕሮፌሽናልና በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ለተገነባውና ለአንድ ዓመት ያህል ከመሰል ግጥሚያዎች ርቆ ለቆየው የሉሲዎቹ ቡድን ይህ ከባድ ቢሆንም ከሜዳቸው ውጪ የደረሰባቸውን ሽንፈትና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የሠሩትን ስህተት አርመው በቁጭት እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ ካምፓላ የተጓዙት ሉሲዎቹ በሀምዝ ስታድየም የዩጋንዳ አቻቸውን በገጠሙበት የመጀመሪያ ጨዋታ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ግን ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ነበር የተጠናቀቀው። በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ግብ አስቆጥረው በአሸናፊነት ብልጫውን ለመውሰድ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ነበር ድል የቀናው። ዛይናህ ናሙሌሜ እና ፋዚላ ኢክዋፑት በ89ኛው ደቂቃና በጭማሪ ሰዓት ባስቆጠሩት ግብም ቡድናቸውን አሸናፊ ሊያደርጉ ችለዋል።
የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅ አፍሪካ ጠንካራ ተብለው ከሚጠቀሱ ቡድኖች አንዱ ሲሆን፤ ከሉሲዎቹም ጋር በተደጋጋሚ የመገናኘት ዕድል ነበረው። በውጪ ሀገር ክለቦች በሚጫወቱ በርካታ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች የተዋቀረው የዩጋንዳ ቡድን የአሸናፊነት የበላይነቱንም ይዟል። ከቀናት በፊት በተደረገው የመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ግን ሉሲዎቹ ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታውን ተቆጣጥረው በመጫወት ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ግብ ባለማስተናገድ ተፎካካሪነታቸውን ማሳየት ችለዋል። ይሁንና ባለቀ ሰዓት በተገኘ ቅጣት ምትና በተጨማሪ ደቂቃ የቆመ ኳስ የመከላከል ድክመታቸው ሁለት ግብ ተቆጥሮባቸው በሜዳቸው የሚያደርጉት የመልሱ ጨዋታ እንዲከብድባቸው ምክንያት ሆኗል።
አሠልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድን ለሁለት ዓመት የዋናው ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ በማድረግ የሾመው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቡድኑን ሞሮኮ በ2026 ለምታስተናግደው 16ኛው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የማሳለፍ ግዴታን በውሉ ማካተቱ የሚታወስ ነው። በመሆኑም የዛሬው የሉሲዎቹ ጨዋታ የሞት ሽረት ትግል እንደሚሆን ይጠበቃል።
ዛሬ በሚኖረው የደርሶ መልስ ጨዋታ ድምር ውጤት አሸናፊ የሚሆነው ቡድንም ከታንዛኒያና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር በቀጣይ ዓመት ጥቅምት ወር በመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ የሚፋለም ይሆናል። በሁለተኛው ዙር ከሚሳተፉ 16 ቡድኖች መካከልም 11ዱ በቀጣዩ ዓመት መጋቢት ወር በሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ የሚፋለሙ ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም