
በረጅም ርቀት አትሌቲክስ ስኬታማ የሆነችው ኢትዮጵያ እንደየዘመኑ አስደናቂ ብቃት ያላቸው አትሌቶችን በማፍራት የአትሌቲክሱ ዓለም ድምቀት ሆና ቀጥላለች። በየሳምንቱ በተለያዩ ከተሞች በሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች ላይ በውጤታማነት ከሚጠቀሱ ታዋቂ አትሌቶች ባለፈም አዳዲስ አትሌቶች እየሆኑ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከልም የቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ሻምፒዮኑ አትሌት ሰለሞን ባረጋ አንዱ ነው።
በዓለም አትሌቲክስ የኤሊት ደረጃ በተሰጠው የሴቪላ ማራቶን በሁለቱም ፆታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነትን በመያዝ ፈጽመዋል። አስደናቂውና የስፖርቱን ቤተሰብ ቀልብ የሳበው ደግሞ አሸናፊዎቹ አትሌቶች በመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፏቸው ውጤታማ መሆናቸው ነው። ሰለሞን በመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፎው የመም ውድድሮች ብቃቱን ማስቀጠል የቻለ አትሌት ሲሆን፤ በሀገር አቋራጭና የቤት ውስጥ ውድድሮችም በርካታ ሜዳሊያዎች ማጥለቁ ይታወቃል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኦሊምፒክን በመሳሰሉ ታላላቅ መድረኮች ውጤት እየራቀው የነበረው ሰለሞን፣ በአዲሱ 2025 የውድድር ዓመት ግን ለረጅም ዓመት አብሮት ሲሠራ ከቆየው ናይኪ ጋር ተለያይቶ ከቻይናው ሊ ኒንግ ጋር ውል በማሰርና በአዲስ ርቀት አዲስ አቋም በማሳየት የስፖርት ቤተሰቡን አስገርሟል።
በአሯሯጮች የታጀበው የሴቪላ ማራቶን ውድድር የርቀቱ አጋማሽ በ1 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ45 ሰከንድ የተሸፈነ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት የተመዘገበውን የቦታውን ክብረወሰን ሊያሻሽል ይችላል በሚል እንዲጠበቅ አድርጎት ነበር። ይሁን እንጂ የቀሩት ኪሎ ሜትሮች እንደተጠበቁት ሳይሆን የጥቂት ደቂቃዎች መዘግየት የታየበት ሊሆን ችሏል። በዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ እና 10 ሺ ሜትር ብርና ነሐስ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀውና በቤት ውስጥ ሻምፒዮናዎችም ስኬታማ የሆነው ሰለሞን ርቀቱ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩት ከተፎካካሪዎቹ ቀድሞ በመውጣት አሸናፊነቱን አረጋግጧል። ርቀቱን የፈፀመበት ሰዓትም 2:05:15 በመሆን ተመዝግቧል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ተፈራ አዲሱ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ሰለሞንን ተከትሎት ሲገባ ሞሮኳዊው ሞሐመድ ሬዳ አል አራብይ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።
ከውድድሩ በኋላም አሸናፊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ‹‹ከእኔ ብዙ እንደሚጠበቅ አውቃለሁ ነገር ግን በውጤቴ ደስተኛ ነኝ። በእርግጥ ሴቪላ ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ ምቹ የሆነች ከተማ ናት፤ ነገር ግን ከ35 ኪሎ ሜትር በኋላ የነበረው ርቀት ለእኔ ከባድ ነበር። ቢሆንም በቀጣይ ከዚህ ልምድ በመነሳት በውጤታማነት እመለሳለሁ›› ሲልም ተናግሯል።
በሴቶች በኩልም በኢትዮጵያውያን፣ የፈረንሳይ፣ የሞሮኮ እና የባሕሬን አትሌቶች መካከል ፉክክር የታየበት ውድድር ተካሂዷል። አትሌቶቹ የመጀመሪያውን ግማሽ ለመሸፈን 1:10:56 የሆነ ሰዓት የፈጀባቸው ሲሆን፤ 40ኛው ኪሎ ሜትር አካባቢ መሪዎቹ አትሌቶች መካከል የታየው መዳከም ለኢትዮጵያዊቷ አትሌት አንቺንአሉ ደሴ ትልቅ ዕድልን የፈጠረ ሊሆን ችሏል። በድንቅ አጨራረስ ርቀቱን 2:22:17 በሆነ ሰዓት በመፈጸም አሸናፊነቷን ልታረጋግጥ ችላለች። የ22 ዓመቷ ወጣት አትሌት በ10ኪሎ ሜትር እንዲሁም ግማሽ ማራቶን ተሳትፎ ልምድ ያላት ቢሆንም በመጀመሪያው የማራቶን ውድድር ለድል መብቃቷ ተስፋ እንዲጣልባት አድርጋል። በተፎካካሪነት ተከትለዋት የገቡት አትሌቶች ደግሞ ፈረንሳዊቷ ማኖን ትራፕ እና ኬንያዊቷ ሲንቲያ ኮስጊ ናቸው።
የዓለም አትሌቲክስ የፕላቲንየም ደረጃ ከሰጣቸው መካከል አንዱ በሆነው የዴጉ ማራቶንም በሁለቱም ፆታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማ ሆነዋል። በሴቶች አትሌት መሠረት በለጠ ስታሸንፍ የሀገሯ ልጅ ትዕግስት ግርማ ደግሞ ሦስተኛ ሆናለች። በወንዶች መካከል በተደረገው ውድድርም ከወር በፊት በሂውስተን አራምኮ የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸናፊ የነበረው አትሌት አዲሱ ጎበና ሁለተኛ ደረጃን ሊይዝ ችሏል። ደጀኔ መገርሳ ደግሞ በጥቂት ሰከንዶች ልዩነት ተከትሎት በመግባት የሦስተኛነት ደረጃን አግኝቷል።
በጃፓኑ የኦሳካ ማራቶንም በተመሳሳይ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ተጠናቋል። የወንዶች አሸናፊው አትሌት ይሁንልኝ አዳነ ሲሆን የቦታውንና የራሱን ሰዓት በማሻሻል ጭምር ድል ቀንቶታል። አትሌት ዋጋነሽ መካሻ ደግሞ በሴቶች በኩል ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ የውድድሩ አሸናፊ ልትሆን ችላለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም