የከበሮው ጌታ

“ከበሮ በሰው እጅ ያምር፣ ሲይዙት ያደናገር”። ይህ የማይሸሹት ሀቅ ነው። ከበሮው በሚያምረው እጅ ላይ ያምራል። አያያዙን ላላወቀው ግን ከማደናገርም አልፎ ሌላውንም ያደናብራል። በመቺው ካላማረ፣ ለሰሚው አይጥምም። ምቱ ካላማረም ድምጹ የሚያቅር ይሆናል።

“ከበሮን በሚገባ ለመጠቀም ከቻልን መሳጭ ድምጽ ይሰጠናል። ካላወቅንበት ግን የሚሰጠን የሚረብሽ ድምጽ ነው” የሚለው ራሱ የከበሮው ጌታ ነው። በከበሮ መንፈስን ማደስም፣ መንፈስን መረበሽም ይቻላል። በርሱ መዳፎች የከበሮው ሆድና ፊት የተዳሰሱ እንደሆን ግን፣ ለጆሮ ፈውስን ይሰጣል። ከበሮ ይዞ ልብን ማሽኮርመም እንጂ ማደናገር አይነካካውም። ተደናግሮ ጆሮን ማስደንበር አያውቀውም። ለዚህም የሙዚቃ ጠበብት ሁሉ በአንድ አፍ መስክረውለታል። “ከበሮ ከተያዘች አይቀር በርሱ፣ ከተመታች አይቀርም በተፈሪ አሰፋ እጅ ነው” ሲሉ አምነዋል። ከበሮን ለተፈሪ እንጂ ለሌላ ለማንም አያጯትም። የኢትዮጵያን ቱባውን ከበሮ ይዞ፣ ከየማህበረሰቡ ጓዳ የባሕል ንጥረ ሙዚቃ እየሰበሰበ፣ ነጋሪት ጎስሞ ለመላው ዓለም አስደምጧል፡፡

“በሳማ በቆንጥር

ባጋም በጋሬጣ

በእሾህ ተከበሻል

በየት በኩል ልምጣ”

እያለ አንድ በአንድ መልቀሙን ተያይዞት ከርሟል። በድምጻዊ አዲስ ለገሰ ድምጽ ዳግም ተሠርቶ “እጅ ከምን…” ያልንበት ይህ ሙዚቃ፣ በከበሮው ውብ አድርጎ የሠራው ተፈሪ አሰፋ ነው፡፡

ተፈሪ ድሮም ቢሆን በልጅነቱ ለሙዚቃ ያለው ስሜት ቀላል አልነበረም። በተለይ ጆሮው የሰላ ነው። ሰምቶ ማጣጣምን ያውቅበታል። ስንዴውን ከእንክርዳዱ የመለየት ልዩ ችሎታ አለው። ወላጆቹ ግን ልክ እንደ አብዛኛው ወላጆች፣ ለትምህርት እንጂ ጊዜውን ለሌላ ለምንም እንዲሰጥ አይወዱም ነበር። ገባ ወጣ ለምትለው የሙዚቃ ፍላጎቱ ከወላጆቹ አንጻር ይሰጋላታል። ወላጆቹም ፍራቻው ቢኖርባቸውም ሙዚቃን ከመስማት ግን አላገዱትም።

በሚያዝያ 15 ቀን 1964ዓ.ም አዲስ አበባ ተወልዶ፣ ኑሮውን ገና ከጅምሩ ያጀበው በከበሮ ነው። አጋጣሚ ፈጥሮ ሙዚቃ መስማትና መጫወት ይወዳል። ከበሮን ብቻ ሳይሆን ከቤታቸው እቃዎች መካከል እንደ ከበሮ ያልደበደበው ነገር የለም፡፡

ተፈሪንና ከበሮን ማንስ አፋቀረ? ያገናኘውም ያፋቀረውም፣ የወላጅ አባቱ ዓመታዊ የልደት በዓል ነው። ልጅ ሳለ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ይሠሩ የነበሩት አባቱ፣ በዕድሜ አንድ ዓመት የሚጨምሩባት የልደት በዓላቸው ይከበርላቸው ነበር። የተወለዱባት ዕለት ዓመት ጠብቃ በመጣች ቁጥር ሁሉ፣ ቤተሰቡ ሰብሰብ እያለ ቀናቸውን ያደምቅላቸዋል። ለዚህ ታዲያ ቤታቸው ውስጥ ከበሮ አለ። ታላላቅ ወንድምና እህቶቹ ከበሮ ይዘው ልደቱን ሲያደሩት፣ በዓይኖቹ ጭምር በቁም ነገር ይከታተላቸዋል። ጆሮው በከበሮ ከታጀበው የሙዚቃ ድምጽ ጋር ቢሆንም ልብና ዓይኑ ግን ከበሮው ላይ ነው። አጋጣሚውን ሲያገኝም እያነሳ ይደልቀዋል። ከበሮው በተቀመጠበት ቦታ ሆኖ “ተፈሪ!” ብሎ የተጣራ ያህል ልብ ይሰማል። ቀልቡም ወዲዚያው ይሳባል። ቀስ በቀስ በከበሮ ፍቅር መውደቁ አልቀረም።

በዚህ ጊዜ ተፈሪ በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪና በሙዚቃ ክበቡ ውስጥ ተሳታፊ ነበር። ስለሙዚቃ እንዲለይለት ያደረገው ወሳኝ አጋጣሚ አንድ ቀን ላይ ሆነ። የኢትዮጵያ የጃዝ አባት የሆኑት ሙላቱ አስታጥቄ ወደ ትምህርት ቤቱ መምጣት ነበር። አመጣጡም የጃዝ ሙዚቃን ለማስተማር ነው። እንዲህ ያሉ ሰዎች ትምህርትም መሆን የምንፈልገውን ብቻ ሳይሆን፣ ያላሰብነውንም ሊያደርጉን ይችላሉ። የጃዝ ሙዚቃ ያለ ከበሮ ምት የሚሄድ አይደለምና ሙላቱ አስታጥቄም ለተማሪዎቻቸው፣ በዚህ ብዙ ነገሯቸው። ከመሃከል ሆኖ የውስጡን ስሜት ከውጭ ሲያደምጥ የነበረው ተፈሪም፤ ያሳተማሩትና የነገሩት ነገር ሁሉ ግልጥልጥ ብሎ ከወደፊት መንገዱ ጋር ታየው። ከሙላቱ አስታጥቂ የሰማው ብዙ ነገር፣ ጠይቆ ያገኘው እልፍ ምላሽ፣ ውስጡ የነበረውን ፍላጎት እውን ለማድረግ እንዲነሳ፣ ቆራጥ አድርጎ አጀገነው። ከበሮን በተለየ ፈጠራ መጫወት እንደሚቻልም ተመለከተ። የጃዝ ሙዚቃና የከበሮ ፍቅሩን በልቡ አንጠልጥሎ፣ ላይመለስ ወደፊት ገሰገሰ፡፡

የቆራጥነት ጉዞው ታዲያ ወስዶ ከልዩ ልዩ ባንዶች ጋር ትውውቅ እንዲፈጥር አደረገው። ያኔ ገና 19 ዓመቱ ነበር። ያገኛት አድናቆት፣ በልጅነት ፍቅር የጀመረው የከበሮ ምት ትልቅ ቦታ መድረሷን አሳወቀችው። እጅግ ድንቅ ሙዚቀኞች የነበሩበት የአይቤክስ ባንድ ቀርቦ ልምድና እውቀት ከሸመተባቸው ባንዶች ቀዳሚው ነው። ትልልቆቹን እየተመለከተና እየተማረ ራሱን ለመገንባት የሚረዳውን ትልቁን ትምህርት አግኝቶበታል። የሙዚቃ ፍቅሩም በእንቅስቃሴ የታጀበ እንዲሆን አደረገው። ትምህርቱ ላይ እንዲያተኮር ሲያደርጉት የነበሩ ወላጅ አባቱ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ ሲመለከቱት ግን፣ ከሚወደው ነገር ጋር ሊለያዩት አልፈለጉም። ይልቅስ ልቡን ያን ያህል ከሰጠለትና ሙዚቀኛ መሆኑ ካልቀረ፣ ጎበዝ ሙዚቀኛ እንዲሆን ነገሩት። ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ በትምህርት እንዲያዳብረውም መከሩት። ልጃቸውን ወደ ፖላንድ ሀገር በመስደድም፣ የሕይወት ህልሙ የሆነውን መንገድ እንዲያሳምር አደረጉት፡፡

በ1980 ዎቹ አጋማሽ ተፈሪ በፖላንድ ተገኘ። የሚወደውን የሙዚቃ ትምህርት ከመማሩ አስቀድሞ ቋንቋ ማወቁ የግድ ነበርና ያንኑ ማድረግ ጀመረ። ቀጥሎም የጓጓለተን ትምህርቱን አስከተለ። የመጀመሪያውን የሙዚቃ ማዕረግ እንዳገኘ፣ ወደ ሀገሩ መመለስን ትቶ በማስትሬት ዲግሪ ለማዳበር ወሰነ። በምት የሙዚቃ መሳሪያዎች ክህሎቱን አጎልብቶ ሲወጣም ሰባት ዓመታትን ፈጀ። የሀገራችንን ከበሮ ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ የባሕል የምት መሳሪያዎች ችሎታና እውቀቱን አዳበረ። ከእነዚህም መካከል በማሊና ሴኔጋል ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኘው “ካላባሽ” አንዱ ነው። ከቂጡ ከፍ ተብሎ የቆረጡት እንስራ የሚመስለውን ቁሬማት፣ ቀን ቀን ውሃ እያመላለሱ፣ ማታ ማታ ለሙዚቃ መሳሪያነት ይጠቀሙበታል። ተፈሪም ያለውን የመጫወት ብቃት በመጠቀም “የደጋ ሰው” በተሰኘው አልበም፣ በዋናነትም “ራያ” በሚለው ሙዚቃ ውስጥ ተጠቅሞበታል፡፡

የከበሮው ጌታ ከበሮን እንደ ድራም፣ ድራምን እንደ ከበሮው ማለት ጀምሮ ነበር። በመሃል ግን ተነስቶ አሜሪካ ገባ። በዚያው የነበረው የኑሮ መስመርና የጠበቀው የሕይወት ዕጣ ፈንታ ግን ሙዚቃ አልነበረም። ቢታገልም ሊሆንለት አልቻለም። እናም የአካውንቲግ ትምህርት በመማር አቅጣጫውን ቀየረ። ነገሩን ቢመለከተው ግን በተሳሳተ ባቡር ውስጥ መሳፈሩን ተገነዘበ። ሙዚቃን ትቶ በዚህ ሕይወት ውስጥ መኖር እንደማይችል ሲረዳ፣ ዳግም ወደ ሙዚቃ ለመመለስ ወሰነ። ወደየትም ሳይሄድ በዚያው በአሜሪካ መሠረቱን ያጸናለትን “ላስታ ሳውንድ” የሙዚቃ ባንድን ለማቋቋም ቻለ። የሙዚቃ ትንፋሽ ከሚያውዳቸው ሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆኑ ባንዱን እውን አድርጎ በስኬት መጓዝ ጀመረ። ትልቁን ዕድል ከትልቁ የሙዚቃ ሰው፣ ከጥላሁን ገሠሠ ጋር አብሮ ለመሥራትም በቃ።

የሙዚቃ ባንዱን ሲያቋቁም አብረውት ከነበሩት ጋር በመሆን፣ በባንዱ ስያሜ “ላስታ ሳውንድ” የተሰኘ አልበም ሠሩ። ከተፈሪ ጋር በዋናነት ሲሠሩ የነበሩ ሦስቱ ሙዚቀኞች፣ ኢትዮጵያዊና ሙዚቀኛ ከመሆናቸው በስተቀር፣ ሙያዊ የዘርፍ መስመራቸው ከተፈሪ ጋር ለየቅል ነበር። የመረጧቸው የሙዚቃ ስልቶች እንኳ የማይገናኙ የሚመስሉ ናቸው። ቱባ የሆኑትን የኢትዮጵያ ባሕላዊ የሙዚቃ አጨዋወትን ከሬጌ፣ ከላቲንና ከጃዝ ጋር በማዋሃድ አዲስ ዓይነት ፈጠራዎች ያሉበት ሥራ ነው።

የመጀመሪያቸው የሆነውን የላስታ አልበምን በፍጹም ውህደት ውስጥ ሆነው ለመሥራት መቻላቸው ተፈሪንም ያስገርመዋል። የአልበም ሥራቸው ተቀባይነትና የነበረው ተደማጭነትም እጅግ ከፍ ያለ ነበር። ከእነዚህም መካከል የቪዲዮ ቅንብር የተሠራለት “ጥቁር ሴት” የሚለው ሙዚቃ በሀገራችን እጅግ ተወዶ በስፋት ተደምጧል። ባንዱን በዝና ያናኘው “ጆርኒይ ኦፍ ላስታ” የተሰኘ ፊልም ደግሞ ተሠራ። በላስታ ሙዚቀኞች ሕይወት ላይ የሚያተኩረው ይህ ፊልም፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝቷል። ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዓለም መድረክ ከፍ ብለው እንዲታዩ አድርጓል። “መንገድ ላይ የሚያገኙኝ ብዙዎች፤ ላስታ! ላስታ! እያሉ ይጠሩኛል” ሲል አልበሙ ዝነኛ እንዳደረገው በአንድ ወቅት ተናግሮት ነበር።

በርካታ ሥፍራዎች፣ ከበርካቶች ጋር ሙዚቃን ለሠራው ተፈሪ አሰፋ ለውዳሴ ባንድ ልዩ ቦታ አለው። የርሱን ችሎታ በስፋት ያሳየበትን “ሰላም” የሙዚቃ አልበምን የሠራው ከዚህ ባንድ ጋር ነበር። እዚህ አብረውት ከነበሩት አንዱ ፋሲል ውሂብ ነው። “እንደ አባ ገሪማ” የተሰኘው ታሪካዊ ሙዚቃ በጣም ከተወደዱት ግንባር ቀደሙ ነው። የቴዎድሮስ ታደሰ “አንቺ ሀገር እንዴት ነሽ” በውዳሴ ባንድ ውስጥ በልዩ ጥበብ ተቀምሞ የተሠራ ድንቅ ሙዚቃ ነው። ሌላው ከወደኋላው “ነጋሪት” የተሰኘ ባንድ ውስጥ መሰሎቹን አሰባስቦ ግሩም ድንቅ የሆኑ ሥራዎችን ሲሠራ ነበር። ከበሮን በብዙ ዓይነት የሙዚቃ ስልቶች ውስጥ በድንቅ ሁኔታ ተጫውቷል። ከቅርብ ጊዜያቶች ወዲህ ግን ሙሉ ትኩረቱን ጃዝን ከቱባ ባሕሎቻችን በማቆራኘቱ ተጠምዶ ነበር። “ኦሪጅንስ” የተሰኘው የአልበም ሥራም ይህንኑ የሚመሰክር ነው። ዓለም አቀፍ እውቅናም አስገኝቶለታል። የእንግሊዙ የሶንግ ላይን ጋዜጣም፣ በ2024 የጥርና የካቲት ቅጂዎች፤ “አርባ ምንጭ” የሚለውን ሙዚቃ ከዓለም ቁንጮዎቹ ውስጥ አካቶታል።

በተፈሪ አሰፋ የሙዚቃ መልክ ውስጥ፣ በራሱ ማንነትና በራስ መተማመን የተገነባ ደም ግባቱ ደምቆ ይታያል። ብዙ ነገሮች ላይ አስቀድሞ የነበረውን እንደወረደ ከመጠቀም ይልቅ የራሱን አዳዲስ የፈጠራ ግብዓቶችን በመጨመር መሥራትን ይወዳል። ከልጅነቱ ጀምሮ ያደገበትን ባሕላዊ ከበሮ እስከናካቴው ጥሎ ወደ ዘመናዊው ድራም አልገባም። ከዚያ ይልቅ በሁለቱ መካከል ድልድይ ሠርቶ ማገናኘቱን መርጧል። ልዩ የሆነ የፈጠራ ችሎታ እንዲኖረው ያደረገውም፣ ሁሌም የእዚህን ሃሳብ መንገድ የሚከተል በመሆኑ ነው። በቤላሩስ፣ በሩሲያ፣ በካዛኪስታን እና በሌሎች ሀገራት ውስጥ እየተዘዋወረ ሙዚቃን ሲጫወት ይዞ የሚቀርበው፣ ከኢትዮጵያ ቱባ ባሕሎች ውስጥ ተሸልቅቆ የወጡ ሥራዎቹን ነበር። ወደ እያንዳንዱ ማህበረሰብ እየወረደ ቱባውን ይዞ ለመምጣት አይታክትም። በባሕል ብቻ ሳይሆን ትልልቅ የሀገር ባለውለታዎችን በሙዚቃው ከፍ ማድረግን አይዘነጋም። “እንደ እማሆይ ጽጌ ማርያም ለሙዚቃ የኖረ የለም” የሚለው ተፈሪ ሙዚቃ ሠርቶላቸዋል። ከታላቁ የያሬድ ጥበብ ቀምሷልና እርሱንም የሚያስታውስ ሥራ አኑሮለታል።

በሙዚቃ አጨዋወቱ ውስጥ የሙዚቃ ሊሂቃን ሳይቀሩ ከሚያደንቁለት ነገር አንዱ በምት (በሪትም) የሚራቀቅ መሆኑ ነው። ፊቱ የተሰለፉትን ከበሮዎች አንድ በአንድ እየመታ ሲያዋህድ ሌሎች የከበሮ ተጫዋቾች ይደመሙበታል። አስበውትና ሞክረውት የማያውቁትን ነገር ሲመለከቱ፤ ለካስ እንዲህም ሊጫወቱት ይቻላል ያሉት ብዙዎች ናቸው። የሚናገሩለት ስለ አጨዋወቱ ብቻ ሳይሆን፤ ስለ መድረክ አያያዙም ነው። የመድረኩንና የታዳሚውን ድባብ በዓይኖቹ እያሸተተ የመጫወት ልዩ ብቃት አለው። በብዙ ታዳሚ ፊት ዘና ብሎ የሚጫወትበት አኳኋን፣ በሌላ ሃሳብ ውስጥ ሆኖ የሚጫወት ነው የሚመስለው። የተዝናኑት በራስ መተማመኑ መጠን ከፍ ብሎ በደም ነብስ እንኳን ሊጫወተው እንደሚችል ስናይ፣ ምን ያህል ከውስጡ ጋር የተዋሃደ እንደሆነ እንገነዘባለን።

የከበሮ ተማሪ የመሆን ፍላጎት እምብዛም ነው። እንደ ሌሎቹ የሙዚቃ መሳሪያ ተማሪዎች፣ የከበሮ ተማሪዎች በቁጥር አይበዙም። በአንድ ክፍል ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ ከመሆን አያልፉም። ተፈሪ ግን በአንዲት ክፍል ውስጥ አንድ ተማሪ ብቻ አስተምሯል። በሙዚቃ ውስጥ ለተፈሪ አሰልቺና ድካም መስሎ የሚታይ ነገር የለም። በሙዚቃና በከበሮው ቀልድ አያውቅም። በየትኛውም ባሕልና ሥርዓት ውስጥ ቱባ የሆነው ነገር ሲሸራረፍ ማየትና መስማት አይፈልግም። ተፈሪ በጣም ይናደዳል፤ የሚናደደውም በሥራዎቻቸው መሃል እንዲህ ያሉ ነገሮችን በሚሰማበትና በሚመለከትበት ቅጽበት ነው። የልጅነት አስተዳደጉ በኢትዮጵያዊ ወግና ሥርዓት የተገራ በመሆኑ ለባሕል እሴቶቻችን ያለው ቦታ የተለየ ነው።

ሙዚቃን ባስተማረባቸውም ሆነ በሠራባቸው ቦታዎች ላይ ሁሉ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርና ማህበረሰባዊ ሥርዓትን ከእርሱ መማራቸውን የሚመሰክሩ ብዙ ናቸው። የመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ እና የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በሌሎችም ሥፍራዎች ሙዚቃን አስተምሯል። የእርሱ ትልቅነት የመነጨውም በከበሮ ተጫዋችነቱ ብቻ ሳይሆን በአስተምሮው ሊቅነቱም ጭምር ነው። ሲበዛ ታሪክ አዋቂ እንደሆነ ይናገሩለታል። የሙዚቃን ታሪክ ከእርሱ አንደበት መስማት፣ የተለየ ስሜትና አቀባበል እንዳለውም ተማሪዎቹ የነበሩ ይመሰክሩለታል፡፡

ከጊዜ ጋር የተሰፋው ሕይወቱ በከበሮ ሙዚቃ ቢሆንም፤ በጎን እጅግ የሚወደውና የሚያዘወትረው ሌላ አንድ ነገርም ነበረው። ይህም የኑንቻኩ ስፖርታዊ ሰርከስ ነው። ከ20 ዓመታት በፊት እንደሰለጠነና አብዝቶም እንደሚወደው ተናግሮ ነበር። በእጅና እግር ቅልጥፍና ላይ የተመሠረተና ቀለል ባለ መልኩ አካላዊ ጤናና ውስጣዊ መንፈስን የሚያድስ እንቅስቃሴ ነው። ተፈሪ ይህን የሰርከስ ዓይነት ምርጫው አድርጎ ሲሰለጥንበት ግን ሌላ ሦስተኛ ግብ አስቀምጦ ይመስለኛል። ባሕላዊው የከበሮ አጨዋወት በእጅ ብቻ የሚጫወቱት ቢሆንም የተፍታታ መዳፍ ከእጅ ቅልጥፍና ያስፈልገዋል። ዘመናዊው ከበሮ(ድራም) ደግሞ ልዩ የሆነ የእጅና እግር ፍጥነት ከውህደት ጋር ግድ ይለዋል። ግራና ቀኝ ላይ ታች፣ ሁለት እግሮች ከሁለት እጆች ጋር ባተሌ ናቸው። ዘመናዊው ከበሮ የሚመታው እንደ ባሕላዊው በመዳፍ ጥፊ ሳይሆን፣ የራሱ በሆነ ዱላ ነው። አያያዝን ማሳመር አንድም ከዚህ የመምቻ ዱላ ጋር ነው። ታዲያ በኑንቻኩ ስፖርት ማለፍ፣ ለዚህ ፍቱን መድኃኒቱ እንደሆነ እንገነዘባለን። ፍጥነትን ከጥንካሬ ጋር ይሰጣል። ተፈሪም በሙዚቃ ችሎታው ምን ያህል ርቆ ስለመሄድ ያስብ እንደነበር የሚያሳየን ነው፡፡

የከበሮው ጌታ ወደ 20 ለተጠጉ ዓመታት፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ከነብሲያው ጋር ሲፈስ ኖሯል። እየኖረ ገና ብዙ የመሥራት ህልምና ተስፋ ነበረው። በሀገራችን ከሚገኙ ማህበረሰባዊ የባሕል እሴቶች መካከል ከግማሽ በላይ በሚሆኑት፣ ለሙዚቃ ሥራው የሚሆኑ የተንቀሳቃሽ ምስልና መሰል ግብዓቶችን አሰባስቦባቸው ነበር። ኢትዮጵያን ተሻግሮ በመላው አፍሪካ የባሕል ሙዚቃ የመሥራት ትልቅ ምኞት እንዳለው ገልጾ ነበር። ይህቺ ዓለም ግን እንዳሰቡ ብቻ የሚኖርባት አይደለችም። ሞት የሚሉት ክፉ ችንካር አለባት። ይሄው ችንካርም ጉዞውን ገታው። ጥር 16 ቀን 2017ዓ.ም አረፈ። “ከበሮ ለእኔ ልክ እንደ ልብ ትርታ ነው” ብሎ ነበር። የእርሱ የልብ ምት ቀጥ ብትልም፣ ሥራዎቹ ለእኛ የልብ ትርታ ሆነው ይቀጥላሉ።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You