የታዳጊዎች ስፖርት ልማት ለብሔራዊ ቡድን ውጤታማነት

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስድስት ወራት የሴክተር ጉባዔውን ሰሞኑን በሐዋሳ ከተማ አካሂዷል፡፡ ከጉባዔው ጎን ለጎን በሲዳማ ከተማ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ልማትን ጨምሮ ሌሎች በስፖርቱ ላይ የሚከሚከናወኑ ሥራዎች የመስክ ምልከታም ተደርጓል። በዚህም በሐዋሳ ከተማና ዙሪያዋ የሚገኙ የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች በከተማዋ ባለ ሰው ሠራሽ ሳር ሜዳ ተገኝተው የሥልጠና ሂደታቸውን በማሳየት ማበረታቻ አግኝተዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ ብዙነህ ታቦታ፣ ዘንድሮ በአዲስ መልኩ 37 የታዳጊ ወጣቶች የስፖርት ሥልጠና ማዕከላትን ማቋቋማቸውን ይጠቁማሉ፡፡ በእያንዳንዱ ወረዳ ቢያንስ አንድ ፕሮጀክት እንዲኖር ታሳቢ ያደረገው ሥልጠናም በ11 የስፖርት ዓይነቶች እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ሲቋቋሙም እንደየስፖርት ዓይነቱ የተሻለ አቅም ያለባቸውን አካባቢዎች ታሳቢ አድርገው በመሆኑ ውጤታማነትን ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡ ክልሉ በፕሮጀክቶቹ በመሰልጠን ላይ የሚገኙ ታዳጊዎችም 3 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግም መሠረቱን በሐዋሳ ከተማ ካደረገው ኦሜጋ ጋርመንት የትጥቅ አምራች ጋር ውል በመግባት ለሠልጣኞች እንዲከፋፈል አድርጓል። ይህም በሥልጠናው ሂደት ሊነሱ የሚችሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እንዲሁም የሀገር ውስጥ የትጥቅ አምራች ድርጅቶችን ለማበረታታት ያስችላል ብለዋል፡፡

ለሥልጠናው በየትምህርት ቤቱ ያሉ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ግልጋሎት የሚሰጡ ሲሆን፤ በየክፍለ ከተማው ያሉና ምርጥ ስፖርተኞችን ያፈሩ ሜዳዎች (ቄራ ሜዳ፣ ኮረም ሜዳ፣ ጨፌ ሜዳ፣ ኮምቦኒ ሜዳ) አሁንም ድረስ የተተኪዎች መፍለቂያ መሆናቸውን ቀጥለዋል። ሥልጠናውን ለመለካትም ክልሉ የራሱን የውስጥ ምዘና ካደረገ በኋላ ወደ ሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሸጋገር መሆኑን ምክትል ኃላፊው አብራርተዋል፡፡ እንድ ሰው ሠራሽ ሳር ሜዳ እንዲሁም የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ደግሞ የሊግ ጨዋታዎችን ጨምሮ ሌሎች ቻምፒዮናዎች ይስተናገዱበታል፡፡

ሥልጠናውን በአካል ተገኝተው የተመለከቱት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ ክልሉ በተለያዩ ስፖርቶች ታዳጊዎችን እያሠለጠነ እንደሚገኝ በሪፖርት ከቀረበው በላይ ትልቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በአካል መመልከት እንደቻሉ ጠቁመዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የታዳጊዎች ስፖርት ልማት ውጤታማ እንዲሆን በእቅድ እየሠራ መሆኑንም ሚኒስትራ ገልፀዋል፡፡ በተለያዩ ስፖርቶች ሥልጠናውን እየተከታተሉ የሚገኙት ታዳጊ ወጣቶችም ጠንክረው በመሥራት ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ ማድረግ እንዲችሉ አበረታተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጂራ በበኩላቸው፣ የእግር ኳስ ስጦታዎችን በማበርከት ሠልጣኞችን አበረታተዋል፡፡ ከሳውዲ አረቢያ መንግሥት ጋር በመነጋገር ከተገኙ ኳሶች መካከል 50 የሚሆኑትን በክልሉ ለሚገኙ የእግር ኳስ የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶች ሰጥተዋል፡፡ ለክልሉ የተበረከቱት ኳሶች ግምታዊ ዋጋ ከ500 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ሁኔታ በመሥራት ወጣቶችን ማነሳሳት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡

በተመለከቱት ነገር ደስተኛ መሆናቸውን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ‹‹ብዙ ጊዜ እዚህ ያለውን ሥልጠና ትተን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እናስባለን፤ የሳትነው እዚህ ጋር በመሆኑ መሥራት ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡ አቶ ኢሳያስ አክለውም፣ እንደ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፊፋ በመነጋገር አዲስ አበባና ሐዋሳ ላይ ለስድስት ወር የሚቆይ ፓይለት ፕሮጀክቶች ውድድር እንደሚዘጋጁ ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም ሲዳማ ላይ ያሉት 40 ምንጭ፣ ሶዶ፣ ዲላና በዙሪያው ያሉትን ሲያካትት አዲስ አበባ ያሉት ደግሞ በአቅራቢያው ያሉትን በመያዝ 96 ጨዋታዎች በመያዝ አንድ መንፈቀ ዓመት የሚቆይ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ስለዚህ በሀገሪቷ በወንድና በሴት ያሉ ፕሮጀክቶች በመደገፍ፣ ለአሠልጣኞች የኪስ ገንዘብ በመስጠት፣ ቤተሰብ ደግሞ በምግብ እንዲችላቸው ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ውጤታማ ለመሆን ወላጆችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ታዳጊዎች ላይ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን መሥራት እንዳለባቸውም አቶ ኢሳያስ አሳስበዋል፡፡ በየክልሉ ያሉ የስፖርት ኮሚሽነሮችም ትኩረታቸውን ታዳጊዎች ላይ በማድረግ ስፖርት አካዳሚዎችን እንዲመግቡ እንዲሁም የውጪ ሀገራት የሥልጠና እድሎችን ማመቻቸትም ተገቢ ነው ብለዋል። በዚህ ደረጃ ተያይዞ መሥራት ካልተቻለ ግን የብሄራዊ ቡድን ውጤት ረጅም ጊዜ የሚወስድ ይሆናል፡፡ ‹‹የእግር ኳስ ውጤት በማሸነፍ እንጂ በሪፖርት አናሻሽልም፡፡ በታዳጊ ሥልጠናና ክለቦች ውስጥ ያልተሠራን ተጫዋች የብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ በቀናት ዝግጅት ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ በመሆኑም ይህንን በማሰብ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እኛም ባሉን ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ድጋፍ እናደርጋለን፤ ግለሰቦችም በተመሳሳይ የማሰልጠኛ ማዕከላትን ሊይዙ ይገባል›› በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You