አፍሪካን ከሌሎች አሕጉራት ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- አፍሪካን ከሌሎች አሕጉራት ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ የቴክኖሎጂ አቅምና አጠቃቀምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት ገለጹ።

ሙሳ ፋኪ መሐመት በ38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የቴክኖሎጂው ዘርፍ የተለየ ትኩረትን ይሻል። አፍሪካን ከሌሎች አሕጉራት ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ የቴክኖሎጂ አቅምና አጠቃቀምን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከሌሎች አሕጉራት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የቴክኖሎጂ አቅምና አጠቃቀምን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው፤ በተለይ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ነው ያሉት።

በሥራ ዘመን ቆይታቸው 55ቱን የአፍሪካ ሀገራት መጎብኘት እንደቻሉ የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ ይህም የአፍሪካን ታሪክ፣ እምቅ አቅም እንዲሁም ማነቆ የሆኑባትን ጉዳዮች እንድመለከት አስችሎኛል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ በአፍሪካ ያለው ግጭት፣ ኮቪድ 19፣ የዩክሬን እና የራሺያ ጦርነት አፍሪካን በእጅጉ እንደጎዳት ገልጸው፤ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ችግሩን መፍታት የሚያስችል የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

ያለፉት ዓመታት አፍሪካ ዓለም አቀፋዊ በሆኑ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች እንደተፈተነችም አስውስተው፤ በአባል ሀገራቱ ያሉ ግጭት እና ያለመስማማቶች፤ በምግብ ዋስትና፣ በሰላም እና ፀጥታ እንዲሁም ተለዋዋጭ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አመላካች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የአጀንዳ 2063 አንዱ ግብ አሕጉሪቱን የሰላም ቀጣና ማድረግ ቢሆንም በአሕጉሪቱ አንዳንድ ሀገራት በሚፈጠሩ ግጭቶች በርካቶች ለኅልፈትና ለሰብዓዊ ቀውስ እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

አፍሪካ በራሷ መቆም የምትችልበትን መሠረት ለመጣል በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ የልማት ግቦችን ለማሳካት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።

 

“በሥራ ዘመኔ ማጠናቀቂያ የማስተላልፈው የመጨረሻ መልዕክት በመሆኑ ላቅ ያለ ደስታ ይሰማኛል” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ በተለዋዋጩ የዓለም ጂኦፖለቲካ ሂደት ውስጥ አፍሪካውያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድነታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአፍሪካ መሪዎች በተለዋዋጩ የዓለም ጂኦፖለቲካ ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ሁሉም የሚመኛትን አፍሪካ እውን ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸው፤ አፍሪካ የዓለም አቀፉን የትምህርት ሥርዓት መነሻ በማድረግ አዲስ የትምህርት ሥርዓት ቀርጻ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባትም ተናግረዋል።

የኅብረቱ አባል ሀገራት ለኅብረቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ ያለምንም ማመንታት በማስቀጠል ኅብረቱን ነፃና ገለልተኛ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በተያያዘ ዜና በየዓመቱ የሚቀያየረው የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበርነትን በ2024 ስትመራ የነበረችው ሞሪታኒያ ሥልጣኑን ለአንጎላ አስረክባለች።

የኅብረቱ ሊቀመንበር የነበሩት የሞሪታኒያው ፕሬዚዳንት ሞሐምድ ኡልድ ጋዝዋኒ ለወቅቱ የኅብረቱ ሊቀ-መንበር ሆነው ለተመረጡት የአንጎላ ፕሬዚዳንት ዧው ማኑኤል ጎሳዌስ ሎሬንሶ መልካም የሥራ ዘመን ተመኝተዋል።

የኅብረቱ ሊቀ-መንበር ሆነው ለተመረጡት የአንጎላ ፕሬዚዳንት ዧው ማኑኤል ጎሳዌስ ሎሬንሶ በወቅቱ እንደገለጹት፤ አጀንዳ 2063 መሳካት የድርሻዬን እወጣለሁ። እኛ አፍሪካውያን በጋራ የምንፈልጋትን አፍሪካ ለመገንባት መሥራት አለብን ብለዋል።

ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በመስጠት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የአንጎላን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተገቢ ቦታ እንድታገኝ እንደሚሠሩ ጠቅሰው፤ አፍሪካ በተመድ በቂ ውክልና እንድታገኝ ከሁሉም ወገኖች ጋር በትብብር እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል።

በቀጣይ አፍሪካውያን ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሠሩም ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምስጋና አቅርበዋል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You