የአትሌቲክሱን ውጤት ለመመለስ የስልጠና ማሻሻያ ይደረጋል

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ስሟ እንዲጠራና ሰንደቋ ከፍ እንዲል ያደረገው የአትሌቲክስ ስፖርት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ኦሊምፒክን በመሳሰሉ ታላላቅ ውድድሮች በውጤት ረገድ እየደበዘዘ መጥቷል። ለዚህ አንዱ ምክንያት ተደርጎ በባለሙያዎች ተደጋግሞ የሚገለጸው ከስልጠና ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው።

በተለያዩ አሰልጣኞችና የስልጠና ስልቶች ውስጥ ያለፉ አትሌቶች ሀገራቸውን በሚወክሉባቸው ውድድሮች ያለመዋሃድና ያለመግባት ችግሮች ሲገጥማቸው ባለፉት ቅርብ ዓመታት በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለመታዘብ ተችሏል። በመሆኑም የዚህ ችግር ምክንያት የሆነው የስልጠና ጉዳይ ፈር መያዝ እንዳለበት የስፖርቱ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይጠቁማሉ፡፡

በቅርቡ ወደ ኃላፊነት የመጣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዳዲስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለመሥራት ያሰበው ጊዜያዊ መፍትሔ ባይኖርም ወደ ፊት ግን በእቅድ የተያዘ ጉዳይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

እንደ ቀድሞው ውጤታማ የአትሌቲክስ ዘመን አትሌቶች በቡድን ስሜት በጋራ ሆነው የሚሰሩበትና በጤናማ መንፈስ ፉክክር የሚያደርጉበት የስልጠና ደረጃ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን በፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የጥናትና ምርምር ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንስትራክተር አድማሱ ሳጂ ያስረዳሉ።

በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሀገራቸውን በዓለም መድረክ ወክለው ለመወዳደር ሲዘጋጁ አንዱ ከሌላው ተደብቆ አሊያም በተቃራኒ መንገድ ከሚሰሩበት ሁኔታ ቀርቶ እንደቀድሞ አትሌቶች የሚተሳሰቡና ሀገርን የሚያስቀድሙበት ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ሃሳብ ይነሳል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቀነሰ መምጣቱ ከስልጠና ጋር የተያያዙ ችግሮች መሆናቸውንም በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚው በኩል ታምኖበታል። በመሆኑም በቀጣይ ይህን ችግር ለመቅረፍ እቅድ በማውጣት ብሄራዊ ስልጠና ለመጀመር እና የስልጠና ሁኔታውን መልክ ለመያዝ ጥረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል። ችግሩን ይቀርፋል ተብሎ የታመነበት የስልጠና ሥርዓት እስከ ዓመቱ መጨረሻ ተዘጋጅቶ በቀጣዩ ዓመት ሥራ ላይ የሚውልበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ኢንስትራክተር አድማሱ ጠቁመዋል።

ኢንስትራክተር አድማሱ እንደሚናገሩት፤ የሚሻሻለው የስልጠና ሁኔታ መለያየት በክለቦች እና ማናጀር ስር የተያዙ አትሌቶች ብቻም ሳይሆን በፕሮጀክቶች፣ የማሰልጠኛ ማዕከላት እንዲሁም አካዳሚዎች ውስጥ ያለውንም የሚያካትት ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ 37 ፕሮጀክቶች በአትሌቲክስ ስፖርት የተያዙ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው 30 የሚሆኑ አትሌቶችን ያቅፋሉ፡፡ ከፕሮጀክቶቹ የተውጣጡ አትሌቶች በቀጣይ ስልጠና የሚያገኙባቸው ደግሞ 10 የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት የላቀ የአትሌቶች መፍለቂያ በሆኑ ስፍራዎች ተገንብተው ተተኪ አትሌቶችን ያፈራሉ፡፡ እነዚህ ማሰልጠኛዎች በፌዴሬሽኑ የሚመሩ ዓላማቸውም በብሄራዊ ደረጃ ተፎካካሪ የሆኑ አትሌቶችን ማፍራት ይሁን እንጂ ስልጠናቸው በሚፈለገው ልክና ሁኔታ ምርጥ አትሌቶችን ለማፍራት የሚያስችል ነው የሚለው ጥያቄ ያስነሳል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ ኢንስትራክተር አድማሱ ከዚህ ቀደም በፌዴሬሽኑ የተዘጋጀ የታዳጊ አሰልጣኞች የስልጠና መመሪያ እንደነበረ ነው የሚያወሱት፡፡ መመሪያው በሁሉም ክልሎችና ማሰልጠኛ ማዕከላት የተሰራጨ ቢሆንም በምን ሁኔታ እየተጠቀሙበት ይገኛል የሚለውን ለመመለስ ግን ምልከታ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም በቀጣይ በየክልሉ ቅኝት በማድረግና በትክክል ተግባራዊ የሚሆንበት አሠራር ይመቻቻል፡፡ በተጨማሪም ከአሰልጣኞች ግብዓት በመውሰድ አስፈላጊ ከሆነ የመመሪያ ክለሳ ሊደረግም ይችላል፡፡ በቅድሚም የባለሙያዎች ቡድን በየማሰልጠኛዎቹ በመገኘት ምልከታውን ያከናውናል፡፡

ከስልጠና ጋር በተያያዘ ከአትሌቶች ባሻገር ባለሙያዎችንም ማብቃት የውጤታማነት ቁልፍ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከዓለም አትሌቲክስ በሚያገኘው የስልጠና ዕድል መሰረት በሀገር ውስጥ ዓለም አቀፍ የዳኞችና የአሰልጣኞች ስልጠናን መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡ ጥሩ ስልጠና ካለ ውድድር ለአትሌቶች ቀላል ጉዳይ መሆኑን፤ በአንጻሩ ስልጠና ላይ ችግር ካለ አትሌቶች ላይ ጫና በመፍጠር ለተሸናፊነት የሚዳርግ መሆኑን ኢንስትራክተር አድማሱ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም በሥራ ላይ ያሉትን አሰልጣኞች ለማነቃቃት እንዲሁም አቅም ለመገንባት የሚያስችል ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ የሀገር ውስጥ ውድድሮችም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማስቻልም የዳኞች ስልጠና ሊሰጥ ችሏል፡፡ በቀጣይም በማዕከላት እና በታዳጊ ፕሮጀክቶች ውስጥ የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ለሆኑ ዓለም አቀፍ ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን፤ ወቅቱን በሚመጥን ደረጃ ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ ማከናወኑም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ነገር ግን ከፌዴሬሽኑ ባለፈ የማሰልጠኛ ማዕከላቱ፣ የአካዳሚዎች፣ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ጭምር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ለውጥ እንዲያመጣ ከውጪ ሆኖ አስተያየት ከመሰንዘር ባለፈ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባቸው ኢንስትራክተር አድማሱ አሳስበዋል። በጋራ በመሥራት ስፖርቱን ወደቀደመ ዝናው እንዲመለስም ባለሙያው ለባለድርሻ አካላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You