
መገናኛ ብዙኃን መረጃዎችን ለአንባቢያን ለአድማጮች፣ እና ለተመልካቾች በተለያዩ ዘዴዎች በማድረስ ግንዛቤ መፍጠር ወይም ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ የተግባቦት መንገዶች ናቸው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ከሰው ልጅ የስሜት ሕዋሳት ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው፡፡ ሰዎች ነገሮችን እንዲመለከቱ፣ እንዲያዳምጡ፣ እንዲናገሩ፣ እንዲዳስሱ፣ እንዲያሸቱና ጉዳዩ እንዲኮረኩራቸው ወይም እንዲነካቸው የማድረግ ኃይል አላቸው፡፡
መገናኛ ብዙኃን ተደራሽነታቸው ለብዙኃኑ እንደመሆኑ ሕዝብን የማስተማር፣ የማስገንዘብ፣ የማሳመን፣ የማነቃቃት፣ አቅጣጫ የማመላከትና የማረም ሥራዎችንም ይሠራሉ፡፡ የመንግሥትን ሀገራዊ አጀንዳዎች፣ የልማትና የእድገት አቅጣጫዎች ለኅብረተሰቡ የሚያስተዋውቁ፣ የሥራ ሂደቶችን የሚከታተሉ፣ ውጤቶችን የሚገልጹ እንደመሆናቸውም በሀገር እድገት ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ አላቸው፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የተቋማትን አፈጻጸሞችን እየገመገሙ ድክመታቸውን የመጠቆም፤ ብልሹ አሠራሮችንና ሙስናን የመዋጋት፤ የኅብረተሰቡ አስተያየቶችና ቅሬታዎችም እንዲደመጡ፣ ተደምጠውም መፍትሔ እንዲያገኙ የማድረግ ሚናም ይኖራቸዋል። መገናኛ ብዙኃን አራተኛ መንግሥት ናቸው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡
እንደ ሀገር የመገናኛ ብዙኃን የቅርብ ዓመታት ሀገራዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ብንመለከት እንኳ በታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ በሀገር ሰላምና ፀጥታ፣ በምርጫ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብሮች ማለትም በግብርና ዘርፍ በከተማ ግብርና፣ በሌማት ትሩፋት፣ በበጋ ስንዴና በሌሎችም አዳዲስ የሥራ ባሕሎች፤ የመንግሥትን የአሠራር አቅጣጫ የማስተዋወቅ፤ ኅብረተሰቡን የማነቃቃትና የማበረታታት ሚናቸውን ሲወጡ ተመልክተናል፡፡
በቱሪዝም፣ በአይ ሲ ቲ ወይም ዲጂታላይዜሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ ወይም ኢንዱስትሪ እና በማዕድን ዘርፎች መንግሥት የሰጠውን ልዩ ትኩረትና እየተከተለ ያለውን የሥራ አቅጣጫ በማመላከትና ግንዛቤ በመፍጠር ህብረተሰቡን የማነቃነቅ ሥራዎችንም ሠርተዋል፤ እየሠሩም ይገኛል። በጤና እና በትምህርት መስኮችም ቋሚ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ጤናው የተጠበቀ እና የተማረ ትውልድን የማፍራት ሚናቸውን መወጣት የተለመደ ተግባራቸው ነው፡፡
የሀገር ገጽታዎችን በመገንባትና የሀገር ገጽታን የሚያጠለሹ አስተሳሰቦችን በመመከትም መገናኛ ብዙኃን ተፅዕኖ ማሳደር የሚችል ሥራ ይሠራሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎች ተግባራቸው እንደ ሀገር ከተመዘገበው ድምር ውጤት ጀርባ መገናኛ ብዙኃን ድርሻቸው ላቅ ያለ መሆኑን ማንም የሚክደው አይደለም፡፡
መንግሥት የሚቀርጻቸው ታላላቅ ሀገራዊ አጀንዳዎችና ፕሮጀክቶች ወደ ኋላ እንዲጎተቱና በታሰበው ልክ እንዳይራመዱ፤ ሕዝብ እንዲማረር፣ አመኔታ እንዲያጣና፣ ተስፋ እንዲቆርጥ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በተለይም በመግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ እነዚህ በተቋማትና በግለሰብ ደረጃ የተንሰራፉ ብልሹ አሠራሮች፤ እድገትን የሚያቀነጭሩ በሽታዎች መሆናቸውም ይታወቃል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ብልሹ አሠራሮችን እና ሙስናን ከመዋጋት አንጻር የሚጠበቅባቸውን ሠርተዋል ባይባልም፤ እጃቸው የደረሰበትን ያህል ፈትሸዋል። ከዚያ በላይ ለመፈተሽም ጥረዋል። የተለያዩ ተቋማትን በር እያንኳኩ ጓዳ ገመናቸውን በመገላለጥ አሠራራቸው ላይ እርምት እንዲወስዱ፣ አጥፊዎችም ሃይ እንዲባሉና እንዲቀጡ ያደረጉባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡
ምንጊዜም እንደ ሀገር የተያዙት የልማትና የእድገት ስትራቴጂዎች ፍሬ እንዳያፈሩ ከሚያደርጉ ሀገራዊ ችግሮች መካከል ሙስና እና ብልሹ አሠራሮች በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ የመሆናቸውን ያህል እነዚህን ከስራቸው ነቅሎ ለመጣል በሚደረገው ትግል መገናኛ ብዙኃን በችግሩ ልክ ተንቀሳቅሰዋል ማለት ግን አያስደፍርም፡፡
ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል። የመጀመሪያው የመገናኛ ብዙኃን በራሳቸው እነዚህን ለሕዝብና ለሀገር እድገት ጸር የሆኑ ጸያፍ ተግባራትን የመዋጋት ቁርጠኝነት ማጣት አንዱ ነው፡፡ በየተቋማቱ የሚስተዋሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? ለሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችሉት እነማን ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስቶ ረጅም ርቀት ለመጓዝ ፍላጎትና ቁርጠኝነት የላቸውም።
ለዚህ ደግሞ በዋነኛነት የሚነሳው ዜጎችም ሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ለመገናኛ ብዙኃን መረጃዎችን በነፃነት የመስጠት ባሕል አለማዳበራቸው ሲሆን፤ ከዚህ ጎን ለጎንም የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ድጋፍ ያለመስጠታቸው ሌላኛው እውነታ ነው። በተለይ ተቋማት በአንድ ጉዳይ ላይ መረጃ እንዲሰጡ በጋዜጠኞች ጥያቄ ሲቀርብላቸው መረጃውን ላለመስጠት የተለያዩ ምክንያቶችን ሲደረድር ማየት የተለመደ ነው።
የሀገሪቱ የመረጃ ነፃነት ሕግ በወረቀት ላይ ብዙ መልካም ዕድሎችን ይዞ ቢመጣም፤ እነዚህን ዕድሎች ወደ ተጨባጭ ተግባርነት ለመለወጥ ግን አሁንም ለሚዲያዎች ፈተና እንደሆነ ነው። ዛሬም በአንዳንድ የተቋም ኃላፊዎች እና መረጃ መስጠት በሚጠበቅባቸው አካላት መረጃ የመስጠት ፍላጎት ሲያጡ ማስተዋል ይቻላል። በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለሚሰጡት አገልግሎት አሊያም ስለ ተቋሙ የአሠራር ሥርዓት ለመገናኛ ብዙኃን ያለማስተዋወቅ አሊያም እራሳቸውን ክፍት ያለማድረግ ችግር አለባቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ‹‹ተቋማት ለምርመራ ጋዜጣ በራቸውን ክፍት በማድረግ የአሠራር ጉድለቶች እንዲታረሙ መተባበር አለባቸው›› በሚል ላስቀመጡት አቅጣጫ ምን ያህሎቹ ተቋማት ተባባሪ ሆነዋል የሚለውን ሆድ ይፍጀው የሚያስብል ነው፡፡
የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ የብዙዎችን ትብብር እና ቀናነት የሚፈልግ ነው። የሀገር እድገትንና የሕዝብ ጥቅምን የሚጎዱ የተንሻፈፉ አካሄዶችን የሚጠግን ፍቱን መድኃኒትም ነው።
ኢትዮጵያ ያሰበችው ግብ ላይ መድረስ የምትችለው እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሪቱን የእድገት መዳረሻ። ተረድቶ በተሰማራበት ሥራ ሁሉ ከእርሱ የሚጠበቀውን መወጣት ሲችል ነው፡፡ ጥቂት ግለሰቦች የብዙኃኑንና የሀገራቸውን ተጠቃሚነት ወደ ጎን ትተው ከመንግሥት አሠራርና ደንብ የወጡ፤ ከማኅበረሰቡ ባሕልና እሴት ያፈነገጡ የስርቆት ተግባራትን ሲፈጽሙ ወይም ተገቢ ያልሆነ አሠራርን ሲከተሉ እየተመለከቱ ጆሮ ዳባ ብሎ መቀመጥ ከየትኛውም ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም፡፡
መገናኛ ብዙኃን ብልሹ አሠራሮችንና ሙስናን እየተዋጉ ኢትዮጵያን ከፍታዋ ላይ ለማድረስ የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ቢታመንም በዚያ ቁመና ልክ አሉ ማለት ግን አያስደፍርም፡፡ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ሚዲያዎች ለሚያቀርቡት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት በአንድም ይሁን በሌላ ልማትና እድገትን መደገፍ መሆኑን ተረድተው ከዚህ አንጻር ለሚዲያዎች ተገቢውን መረጃ በመስጠት ሊተባበሩ ይገባል፡፡
ይህን የማድረግ ፍላጎት ከሌላቸው ግን የበላይ አካላት ጣልቃ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት የምርመራ ጋዜጠኝነት በሀገር ልማትና እድገት ላይ የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ ተረድቶ ተቋማት ጋዜጠኞች ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ ቢያደርግና ጋዜጠኞችን ቢያግዝ ብዙ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም