ለምክክሩ ውጤታማነት ብዝሀ ማንነትን ማክበር

ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት የምትለይበትና የምትታወቅበት አንዱ ነገር ብዝሀነት ነው። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች በሰላም የሚኖሩባት ሀገር በታሪኳ የተለያዩ ልሂቃንን፣ ባሕሎች እና ሃይማኖቶች በአንድነት አሰባጥራ የያዘች ነች። ይህን መሰሉ ብዝሀነት የሀገር ሀብት የልዩ ውበት መገለጫና የመቻቻል ምሳሌ ነው።

ይሁን እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ብዝሀ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ሃይማኖትና ሌሎች ልዩ ልዩ መገለጫ ያላቸው ሀገራት ብዝሀነትን ያማከለ ትርክትና ሀገረ መንግሥት በመገንባት፤ በልዩነት ውስጥ ጠንካራ አንድነት ፈጥረው መሄድ ባለመቻላቸው ምክንያት ፀጋው ወደ እርግማን ተቀይሮባቸዋል፤ ወደማያባራ ግጭት ውስጥም ገብተው ተመልክተናል። የሀገራችን መዳረሻ ይህ ሊሆንም አይገባም።

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በገነቡት ሀገረ መንግሥት ውስጥ የብዝሀ ባሕል፣ ማንነትን አክብረውና ተከባብረው ተቻችለው የዘለቁ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የግጭት መንስኤ ሲሆኑ ተመልክተናል። የፖለቲካ አድማሱ፣ ሀገራዊ ትርክቱ ብዝሀነትን በቅጡ ያማከለ እንዳልሆነ የሚሞግቱ ፖለቲከኞች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደጋጋሚ ትችቶችን ሲያነሱ ይደመጣል። አለፍ ሲልም ነፍጥ የሚያማዝዝ እና ለቀውስ የሚዳርግ ግጭት ሲፈጠር ታዝበናል።

መንግሥት እነዚህንና ሌሎች መሰል የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የማኅበራዊ ቅርቃሮችን በመፍታትና ዘላቂ እልባት ለመስጠት እየሠራ ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ ሀገራዊ ምክክር በማድረግ ዘላቂና ማዕከላዊ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ትርክት መፍጠር ይገኝበታል። በዚህ ሂደት ውስጥ ብዝሀነት ቁልፍ ድርሻ እንደሚወስድ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያምናል። ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን መሠረቱን ብዝሀነትን ማክበር እና በዚያ ውሃ ልክ ውስጥ ሁሉም በሚዛንና በእኩልነት የሚሰፈር መሆኑን ማረጋገጥ ነው።

ብዝሀነት ብሔር ብሔረሰቦችን ብቻ የሚገልፅ አይደለም። ብዝሀነት ሃይማኖትን፣ ፆታን፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልዩነትን፣ ትምህርትን እና ሌሎችም አያሌ ነገሮችን የያዘ ፅንሰ ሃሳብ እንደመሆኑ መጠን በዚያ ልክ አካታች የሆነ ምክክርና አጀንዳ ቀረፃ ማድረግ ያስፈልጋል።

በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከዚህ በሚከተለው ዝርዝር ሃሳብ ላይ በምክክር ኮሚሽኑም ሆነ በቀጣይ በሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ውይይቶች፣ ድርድሮች ላይ ታሳቢ መደረግ ስላለባቸው የብዝሀነት ፅንሰ ሃሳቦችና ምንነቶች ላይ ጥቂት ለማለት ይወድዳል። በተለይ ‹‹በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት በዘላቂነት ለማስፈን ልዩ ትኩረት ሰጥተን ልናከብራቸው ስለሚገቡ የብዝሀነት መገለጫዎች›› የተወሰኑ ሃሳቦችን እንደሚከተለው ያነሳል።

የብዝሀነት መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በቀዳሚነት ሃይማኖት አንዱ ነው። ኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን፣ እስልምና፣ ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክ እና የተለያዩ ተጨማሪ ሃይማኖቶች በሰላም የሚኖሩበት ሀገር እንደሆነች ይታወቃል፤ በዚህ የተነሳ ብዝሀ ሃይማኖት ያለባት ሀገር ነች። በተለይም ኦርቶዶክስ ክርስቲያን እና እስልምና የሀገሪቱን ታሪክ እና ባሕል በሰፊው ተጽዕኖ አሳድረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት ተቋማት በሰላም ለመኖር የሚያስችሉ ሥራዎችን እየተተገበሩ መሆኑን ተመልክተናል።

በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ አንድነት እና ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጠንካራ ስብዕናዎችን ለመገንባት ይህንን ብዝሀነት ማክበር እና ከሁሉም ዓይነት ሃይማኖቶች ነፃ የሆነ የመንግሥት ሥርዓት መዘርጋት ተገቢ ይሆናል። የሀገሪቱን አንድነት ለማፅናት የሚረዱ ምክክሮችና ውይይቶች በሚደረጉበት ወቅት የሃይማኖት ብዝሀነት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው።

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ያሉባት ሀገር ናት። ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ እና ሌሎች ብሔረሰቦች የራሳቸው ቋንቋ፣ ባሕል እና ታሪክ አላቸው። ይህ ብዝሀነት የሀገሪቱን ማንነት የሚያጸና ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግጭቶች ሲነሱና ሉዓላዊት ኢትዮጵያ ላይ ስጋት ሲደቀን እናስተውላለን። የግጭቶቹ መንስኤዎች ከፍትሀዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል፣ ከተዛቡ ትርክቶች እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ሲቆራኙም ተመልክተናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌዴራል ሥርዓቱ በብሔራዊ እና ክልላዊ መንግሥታት መካከል ያለውን ሚዛን ለማስቀደም እየተሠራ መሆኑን ማስተዋል ቢቻልም ዘላቂ፣ አስተማማኝ እና የፀና ሀገረ መንግሥት ለቀጣዩ ትውልድ ገንብቶ ለማስረከብ የብሔር ብሔረሰቦች ብዝሀነት በትክክል መከበሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። ይህንን እሳቤ ለማስረፅ የሚካሄዱ (እንደ ሀገራዊ ምክክር) ዓይነት መድረኮች ቅድሚያ ሊሰጡት ከሚገባ አጀንዳ ውስጥ ግንባር ቀደሙ መሆን ይገባዋል።

ሌላው የብዝሀነት አንዱ መገለጫ ባሕል ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የተለያዩ ባሕሎች የሚገኙባት ሀገር ናት። በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከተራራማ ክፍሎች እስከ ሜዳማ አካባቢዎች፣ ከከተሞች እስከ ገጠሮች ብዝሀ ባሕል በየቦታው ይታያል። ለምሳሌ የትግሬ ምግብ እና የኦሮሞ ሙዚቃ የሀገሪቱን ብዝሀነት ከሚያንፀባርቁ ምሳሌዎች ውስጥ መጥቀስ እንችላለን። የደቡብ ሙዚቃ፣ የአደባባይ ባሕላዊ ሥርዓቱ፣ አለባበሱ እና ሌላውም ሌላውም በሀገራችን በብዛትና በስብጥር ይገኛል።

በመሆኑም ይህንን ኢትዮጵያዊ የሆነ ባሕላዊ ብዝሀነት ያከበረ ጠንካራ አንድነት መገንባቱን ሁሉም ዜጋ ማረጋገጥ ይገባዋል። ዘላቂ ሰላምን ያሰፍናሉ ከሚባሉ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል በሕዝቦች መካከል ያለውን የባሕል ልዩነት የሚያከብርና በመቻቻል የሰፈነበት ሥርዓት መዘርጋት ነው። በመሆኑም ቀጣይ የሀገሪቱን አቅጣጫ በሚወስኑ ማናቸውንም ምክክሮች ላይ የባሕል ብዝሀነት የተመለከቱ አጀንዳዎች በማንሳት ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ማድረግ ያሻል።

ብዝሀነት የኢትዮጵያ ሀብት ነው። ይህ ብዝሀነት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሳውቃት ከማንነት አልፎ በቱሪዝም የኢኮኖሚ ምንጭ መሆን የሚችል ነው። ሆኖም በትክክል ካልያዝነው የራሱ መዘዝ አለው፤ በቀላሉ ግጭቶችን ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ መንግሥት፣ ማኅበራዊ ተቋማት እና ዜጎች በጋራ የብዝሀነት ጠቀሜታ የሚረዳ ምቹ ሥርዓት በምን መልኩ መገንባት እንደሚኖርባቸው ሊመክሩ ይገባል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብዝሀነት በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ሊንፀባረቅ ይገባል። ይህ ማለት ሁሉም ብሔሮች እና ብሔረሰቦች በፖለቲካዊ ሂደቶች ውስጥ እኩል ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ ነው። በምርጫ፣ በፖለቲካ ተሳትፎ እና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ምህዳር መፍጠር አስፈላጊ ነው።

ከላይ ያነሳሁትን መሠረታዊ ጉዳይ መሬት ለማውረድ የትምህርት ሥርዓት ጉልህ ድርሻ አለው። ትምህርት የብዝሀነት ጠቀሜታን ለማስተዋወቅ እና በማኅበረሰብ ውስጥ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል። ለዚህ ደግሞ የትምህርት ሥርዓቱ የሀገሪቱን ብዝሀነት የሚያንፀባርቅ እና የሚያከብር መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለምሳሌ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎችን እና ባሕሎችን ማስተማር የብዝሀነት ግንዛቤን ያሳድጋል። ሰዎች ከራሳቸው ውጭ ያሉ ማንነቶችን ማክበር፣ እና ለልዩነቶቹ ጤናማ የሆነ ምልከታ እንዲኖራቸው ትምህርት ወሳኝ በመሆኑ ትውልዱን በእውቀት ማነፅ ተገቢ ነው።

ብዝሀነትን አከበርን ስንል

ኢትዮጵያውያን ጠንካራ፣ ሉዓላዊት ሀገር ለመገንባት በሚያደርጉት ተከታታይ ውይይት እና ማዕከላዊ ትርክት ግንባታ ላይ የሚከተሉት ነጥቦች መካተታቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል።

‹‹ብዝሀነት ያማከለ ሥርዓት ተገንብቷል›› የምንለው የማኅበራዊ ፍትህ በኢትዮጵያ ውስጥ መስፈኑን እርግጠኞች ስንሆን ነው። ይህ ማለት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መብት እና ዕድል ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው። በተለይም ሁሉም ብሔረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ፆታ፣ ባሕል በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶች ውስጥ እኩል ዕድል ሊኖራቸው ይገባል።

ሌላው ጉዳይ ሚዲያ ነው። ሚዲያ የብዝሀነት ጠቀሜታ፣ አስፈላጊነት እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለውን ጉልህ ሚና ግንዛቤ ለመፍጠር ድርሻው የላቀ መሆኑን ማወቅ ለዚያም ምቹ ምህዳር መፍጠር አስፈላጊ ነው። ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ የተለያዩ ድምፆችን ለማሰማት እና የብዝሀነት ጠቀሜታን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ አቅም ስላለው በቀጣይ በሚደረጉ የፖለቲካ ውይይቶች፣ ድርድሮች እና የሀገራዊ ምክክር መድረኮች ላይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ብዝሀነትን ለማክበርና ያንን የሚሸከም ሥርዓት ለመዘርጋት የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት የማንኛውም ብሔር፣ ሃይማኖት ወይም ባሕል ተከታይ መብቶች ማክበር ማለት ነው። የግለሰቦችን፣ ቡድኖችን እና የተወሰኑ ብሔረሰቦች ሰብዓዊ መብቶች በእኩል መከበሩን የሚያረጋግጥና ለዚያም የሚሠራ ሥርዓት መዘርጋት ይኖርብናል። በመሆኑም በቀጣይ የተሻለች፣ ዘመናዊና ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረጉ ማናቸውም ውይይቶችና ምክክሮች (ሀገራዊ ምክክር ጨምሮ) ብዝሀነትን የሚያከብር የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን የሚያረጋግጥ ተቋማት ምሥረታ አጀንዳ ሊሆን ይገባል።

ለመደምደም

መንግሥት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የሀገር አንድነት የሚሸረሽር አሉታዊ ትርክት እልባት ለመስጠት ተቋማዊ ሥርዓት ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ ነው። በርካታ አስርት ዓመታት በማኅበረሰቡ፣ በልሂቃኑና የተለያየ አመለካከት በያዙ ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠሩ ብዥታዎችን፣ የሃሳብ ልዩነቶችን፣ የአይዲዮሎጂና የመስመር መራራቆችን የሚያጠብቡ አሊያም ጤናማ የሃሳብ መንሸራሸር የሚፈጥር ምህዳር እንዲኖር እየሠራ ነው። ተግባራዊ እንቅስቃሴው ይህንን ዲሞክራሲያዊ ምህዳር ለመዘርጋት እና ሀገር በፀና ሰላምና አንድነት ውስጥ እንድትቆይ ለማድረግ መደላደል ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል።

እሳቤውን ወደ መሬት ለማውረድ ከሚያስችሉ መንገዶች ሀገራዊ ምክክር ማድረግ አንዱ መሆኑ ታምኖበታል። ይህ መንገድ ስኬታማ እንዲሆን ደግሞ ዛሬ በስፋት ያነሳነው የብዝሀነት እሳቤ በምክክሩ ላይ መነፀባረቅ ይኖርበታል።

ብዝሀነትን አክብረናል ስንል የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እኩልነት አረጋግጠናል ማለት ነው። ይህ ማለት ሁሉም ዜጎች በኢኮኖሚያዊ እድሎች እና በማኅበራዊ አገልግሎቶች እኩል መዳረሻ ሲኖራቸው ነው። በዚህ ምክንያት ሀገራዊ ሰላም፣ እድገትና ብልፅግናን ማረጋገጥ እንችላለን። ለዚህ ነው ይህንን መሰል ሥርዓት ለማንበር በተለያዩ ብሔሮች እና ሃይማኖቶች እና ሌሎች ብዝሀ ማንነቶች መካከል የሰላም እና የትብብር መንፈስ መፍጠር የሚያስፈልገው።

ዜጎች በሚኖሩበት ሀገር ላይ ባሕላቸው፣ ሃይማኖታቸው፣ ቋንቋቸው እና ሌሎች ግለሰባዊና የቡድን ማንነቶቻቸው መከበራቸውን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ይህ መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎት በተረጋገጠበት ሀገር ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ የማይደፈር ሉዓላዊነት፣ እድገት፣ ብልፅግና እና ሁለንተናዊ ስኬትን በቀላሉ ማምጣት ይቻላል። ለዚህ ነው እንደ ሀገር ያሉብንን ስብራቶች ለይተንና የመጣንበትን መንገድ በሚገባ ገምግመን ለመጪው ትውልድ የሚበጅ ሀገርና ዲሞክራሲያዊ እሳቤ ትተን ማለፍ የሚጠበቅብን። ይህንን መሬት ለማውረድ እንዲችል ኃላፊነት የተሰጠው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም መዳረሻውም ‹‹ብዝሀነትን ያከበረች ኢትዮጵያ ግንባታ›› ሊሆን የሚገባው ገዢ አመክንዮም ከዚህ እውነታ ይመነጫል። ሰላም!!

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You