
“እኔ የምጠጣው እምባ እንዲሆነኝ ነው” ይላል አባ ጥጉ ጠጁን ወደ ጉሮሮው እያንደቀደቀ። አባ ጥጉ የሚለውን ስም ያወጣንለት እኛ ወዳጆቹ ስንሆን ከበሩ ስር ጥግ ላይ ካልተቀመጠ አምባጓሮ ስለሚያነሳ ነው።
ካምቦ ጠጅ ቤት ከድሮ እስከ ዘንድሮ፣ ከገንፎ እስከ ንፍሮ ያለ ታሪክ ስለሚንሸራሸርባት ታማኝ ታዳሚዎቿ ነን፤ በተለይ አባ ጥጉ ካለ ጥርስ አይከደንም። አንዳንድ ቀን ደርሶ
“አከፋው በጣሙን ከሞቴ አሟሟቴን፣
ማንም ቀልዶበት የዘመን ሽበቴን።”
ይልና ሀዘን ይቀመጣል። ከመሃል ደግሞ “ፈረንጅ የሀበሻን እግር ሲያጥብ እንዲያሳየኝ ጸሎት ልይዝ ሱባኤ እንደገባሁ አይጥ ጋን ተሸክማ ስትንጎራደድ አይቻለሁ” ብሎ በሳቅ ይወድቃል። ከሳቁ መልስ በቀጥታ ጋብዙኝ እንዳይል “ለሽንት አትውጡ ብርሌ ይጠፋል” ይላል ብርሌያችንን በአይኑ እየቃኘ። እኛም አመሉን ስለምናውቅ ለጨዋታ ግልጽ እንሆንለታለን።
“ለሽንት አትውጡ ብርሌ ይጠፋል” የሚለው አነጋገሩ አንዲትን የድማ እብድ ያስታውሰኛል። አንድ ቀን አፋፍ ላይ ቆማ ” ዛሬ ገበያ አትሂዱ ቤት ይቃጠላል” ስትል ለፈፈች፤ የመንደሩ ነዋሪ ግን ከፌዝ ሌላ ቁብ አልሰጣትም። ከገበያ እንደተመለሱ በሳቅ ያለፉት አደጋ እውን ሆኖ ጠበቃቸው።
በመንደሩ የቤት ምልክት የለም እንዳለ ወድሟል። “ምነው?” ቢሏት “ስነግር ነው” አለች፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ “ስነግር ነው አለች የድማ እብድ” ተብሎ ተተረተ። አባ ጥጉም ኪሱ ሲያዛጋ “ለሽንት አትውጡ ብርሌ ይጠፋል” ይላል መጠጥ ሲያሰኘው። እኛም አንጨክንበትም። “በድሮ ጊዜ” እያለ ስለሚያወጋን እጃችን ይፈታለታል።
ከቁመቱ ጋር ውፍረቱ ተዳምሮ ጉርድ በርሜል የሚመስለው ጓደኛችንን አባ ጥጉ “ክምሩ” ብሎ ነው የሚጠራው። እሱም በተራው አባ ጥጉን ለማብሸቅ ነገር ይሰረስራል። “የሰው ጎተራ ስትፈነቅል ነው አደል ቀኝ እጅህን ያጣኸው?” ይለዋል ቀፈቱን እያሸሸ። አባ ጥጉ ሰባት ዘለላ ፀጉሩን እየነጨ “ቀኝ እጄ የናቅፋን አንገት እንዳነቀ ነው የቀረው። ስመትርላት የምትነጭ ሀገር ዋጋዬን አራክሳ መሃሉን ዳር አደረገችብኝ እንጂ እኔስ ሌባን ላጠፋላት ነበር፤ ዳሩ ምን ይሆናል አካሌ ጎሎ መንፈሴ ዝሎ ስመለስ እኔም የኦሪዮን እጣ ፈንታ ገጥሞኝ እንደ ዳዊት ያለ ባለፀጋ ሚስቴን እና ርስቴን ነጥቆኝ ደረስኩ። ይሁን እንጂ አጥንቴን ለከሰከስኩላት ደሜን ላፈሰስኩላት ሀገሬ ፍርዱን ከመስጠት በቀር ትንፍሽ አላልኩም” አለና ከደም የወፈረ እንባውን አንዠቀዠቀው።
“ለክብሯ ስትሞት ውርደት ለደገሰችልህ ምድር ምን የሚሉት ሀገር ፍቅር ነው?” አለ ክምሩ በንዴት አይኑ ቀልቶ። አባ ጥጉ ከያዘው ኮሮጆ ብርቱካን አወጣና ልጦ እንደጨረሰ ይሰጠናል ብለን ስናንቃቃ ሳያካፍለን ለብቻው በላው። በሀፍረት ብርሌያችን ውስጥ ስንደበቅ “ይሄ ብርቱካን ጣዕሙ እንዴት ነው?” ሲል ጠየቀን። ክምሩ የጎሪጥ እያየው “መቼ አቀመስከን?” አለው ሀፍረቱን ለመሸሸግ እየጣረ። “አያችሁ ልጆች…እናንተም የኢትዮጵያን ጣዕም አታውቁትም” አለ በኩራት ተጀንኖ። ቀጠለና “ጉርጉሱም ላይ ቆማችሁ የቀይ ባህርን የሚምነሸነሽ ወጀብ ሽቅብ ተነስቶ ሲወድቅና ከአለቱ ጋር ተፋጭቶ አረፋ ሲደፍቅ ብታዩ የሀገር ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ ይገባችሁ ነበር” እያለ መንፈሳችንን ወስዶ ከምጽዋ ግርጌ ተከለው።
በየፊናችን ሀሳብ ውጠን ስናንቀራጭ “ለሰው ሞት አነሰው አለች ቀበሮ” እውነቷን ነው” አለ አባ ጥጉ አንጀቱ ደብኖ። “ምን ሆንክ ጃል?” አለው ክምሩ ድባቡን ለመለወጥ ሽቶ። “አይ የሰው ነገር አይነገር! “አለ በድጋሚ ክፉኛ አዝኖ። በሰው ተስፋ ልትቆርጥ ባልሆነ? አልኩት በነገሩ ጣልቃ ገብቼ። ”ለነገሩ ለፈጣሪው ያልተመቸ እንዴት ለኔ ሊሆን ይሆናል? ብዬ ገመትኩ ቂሉስ እኔው ነኝ “ አለ በጸጸት ከንፈሩን ነክሶ።
የያዘውን ብርሌ በቁሙ ጨለጠና አስከትሎ “ህይወትን የሚያስተምረው፣ ራስን የሚያስገኘው፣ ወስዶ የሚመልሰው ጎዳና ነውና ምን እንደጻፈልኝ አንብቤው ልዝጋ “ ብሎ እየተንደረደረ ወጣ ። ከዚያን ዕለት በኋላ ረዘም ላሉ ቀናት ድምጹ ርቆብን ምን ሆኖ ይሆን ? እያልን ስንንቆራጠጥ በአንደኛው ቀን ምሽት ላይ ቤቴን አጠያይቆ መጣ። እጁን ከአፉ አስታርቆ ሲያበቃ ያቀረብኩለትን የዕህል ደም ተጎንጭቶ ጉሮሮውን አረጠበና ትንባቴውን አንድ በአንድ አስቃኘኝ ። ”የመጨረሻዋን ጽዋ ስናጋጭ እላፊ ስጫወት አልገመታችሁም እንጂ ለስደት ቆርጬ ነበር። “ አለ የሚተናነቀውን እምባ እየመለሰ። “አንቱ በተባልኩበት ቀዬ ውርደትን በዘከርኩበት ደብር መመጽወትን አምኖ ሞራሌ እንዴት ይቀበል? በተነሳሁ በሶስተኛው ቀን ርሃብ እና ጥሙ አሸንፎኝ ለሞት እጄን ሰጠሁ። በጦር ሜዳ ከሞት ጋር ግብ ግብ ስገጥም ተስፋ ያልቆረጥኩ ሰው በሰው መሃል እየኖርኩ ፍቅር ርቦኝ ሃቄ ሲነጠቅ ካለቦታዬ ስወድቅ በልቤ ያተምኳት ሃገሬ ደበዘዘችብኝ ፤ አለኝ ያልኩት ፈጣሪ የራቀኝ መሰለኝ፤ የተደገፍኩት ሰው እንደከዳኝ ተሰማኝ ፤ ነገር ግን ይህን እሳቤዬን የሚያርቅ ተዐምር ተፈጠረ” ብሎ ዝም አለ። ምን ? አልኩት ተስገብግቤ።
“ጊዜው ቀትር ላይ ነው። ጣረሞት ሲጫወትብኝ የነብሴን ማለፍ እየተጠባበኩ ሳለ የአሞራ መንጋ ሊበላኝ ዞረኝ። ተፈጥሮም መልካምነቷን በግብሯ ገለጠችልኝ። የተነሳው አውሎ ነፋስ አሸዋ አልብሶ ሸሸገኝ። ማታ ደግሞ እንዲሁ ሌላ ፈተና ተጋረጠብኝ፤ አውሬ ሊቀራመተኝ ሲያሰፈስፍ የወርቅ ዘንግ የያዙ አረጋዊ ከአውሬዎች አፍ አስጣሉኝ ። ለካስ ፈጣሪ ያለሃገር ሃገሬም ያለሰው አልተውኝም ።
ከወደኩበት አንስተው እህል ውሃ ሰጡኝና ጎኔ ሲጠገን ህይወት ያሳየችንን ከፍ እና ዝቅ ስንጫወት የሰውን ልጅ የት አገኘዋለሁ እንደማይባል የተማርኩበት አጋጣሚ ተከሰተ። ሚስቴን እና ርስቴን የነጠቀኝ ባለጸጋ ከዓለም ርቆ ኃጢያትን ንቆ መልካም ስራ መንገዴ ንፋስ ዘመዴ ብሎ ጭው ባለው በርሃ መኖር ከጀመረ ዓመታት እንደተቆጠሩ አካላዊ ገጽታው ይናገራል። ገበናችንን ገልጠን ስንጨዋወት እማኝ በሌለበት አውላላ ሜዳ እምባ እየተራጨን ምህረት ተጠያየቅን ። እንዴት የይቅርታ ልብ ሊኖረው እንደቻለ መጠየቄ አልቀረም፤ እሱም ቢሆን ሳይደብቅ የነገረኝ ታሪክ የህይወት ስንቅ ነው።
በአንድ ወቅት ከጎረቤቱ ጋር ይጣላል፤ ይህን ጊዜ በሃብቱ ተመክቶ ያጣ የነጣ መሆኑን ተሳድቦ ይነግረዋል፤ ኋላ ግን ህሊናው ተጸጽቶ ይቅርታ ሲጠይቀው የማዝህን ካደረክ አደርግልሃለሁ ይለውና በማዳበሪያ የዶሮ ላባ ሞልቶ ከሰጠው በኋላ በነፋስ እንዲያዘራውና መልሶ እንደነበረው አድርጎ እንዲያመጣለት አዘዘው። እንደታዘዘው ሲያደርግ ላባዎቹን ንፋሱ የትሜናቸውን በታትኖበት መሰብሰብ አልቻለምና ባዶውን ተመለሰ። ወዳጁም አየህ ባልንጀሬ አንተም የዘራኸው ክፉ ቃሎች ልቤ ውስጥ ተበትነው መልሰህ መሰብሰብ አልቻልክም አለው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የበደላቸውን ክሶ እንባቸውን አብሶ የበረሃን ኑሮ ብቻውን መግፋት ያዘ። ይህ አጋጣሚም እኔን የአውሬ ራት ከመሆን አድኖኛል። በመጨረሻም ልጆቼ እና ባለቤቴ የት እንዳሉ ነግሮኝ ምልክት እንዲሆናት የታሸገ ፖስታ ሰጠኝና እሷ ዘንድ ሳልደርስ መክፈት እንደማልችል አስጠንቅቆ ሙሉ ሃብቱን አውርሶኝ ተመራርቀን ተለያየን። ይሄው አሁን ወደ እሷ እየሄድኩ ሳለ ሁኔታዬን ሳላሳውቃችሁ አላልፍም ብዬ ነው ወደዚህ ማቅናቴ ።
የገጠመኝ እያንዳንዱ ፈተና የህይወት ሽግግር እንጂ ውድቀት እንዳልሆነ እና ለሰው ልብሱ ሰው መሆኑን ተምሬያለሁ፤ ይሁን እንጂ በአብሮነታችን ጊዜ የሰው ልጅ ምን ያደርግልኛል? እያልኩ ሳማርር አዝናችሁብኝ ይሆን? አለና ለይቅርታ ጉልበቴን ያዘ ። ጫንቃ ለጫንቃ ተሳስመን ጓደኞቹ ተሰባስበን የታሸገውን ፖስታ አጅበን ቤተሰቦቹን ፍለጋ ተጣደፍን፤ ይህ ፖስታ ምን ምልክት ይዞ ይሆን ?
ሀብታሙ ባታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም