
ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም የተጀመረው የሠራተኞች የበጋ ወራት ስፖርታዊ ውድድሮች በሳምንቱ የዕረፍት ቀናት በፉክክር ታጅበው በተለያዩ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ቀጥለዋል፡፡ በዚህም መሠረት ባለፈው ጥር 24 እና 25 በበርካታ የስፖርት ዓይነቶች ጨዋታዎች ተከናውነው አሸናፊዎቹ ተለይተዋል፡፡
የወንዶች እግር ኳስ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የዮሐንስ ቢፍ ኢን. ወተር ጨዋታ አራት ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን ፉክክሩም 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ግማሽ ደርዘን ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ተጋጣሚው ኢካፍኮን 5ለ1 በሆነ ውጤት መርታት ችሏል፡፡ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ደግሞ የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶችን በጠባብ ውጤት አንድ ለምንም አሸንፏል፡፡ ረጲ ሳሙናና ዲተርጀንት ፍልውሃ አገልግሎትን 3ለ0 በሆነ የፎርፌ ውጤት አሸናፊ መሆኑን ከውድድሩ አዘጋጅ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሠማኮ) የስፖርት ክፍል የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡
በሠራተኛው የስፖርት መድረኮች ጥሩ ፉክክር ከሚታይባቸው ውድድሮች አንዱ በሆነው ቮሊቦል በሴቶች መካከል በተካሄደው ብቸኛ ጨዋታ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን 2ለ1 አሸንፏል፡፡ በወንዶች ቮሊቦል በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ፋፋ ምግብን 3ለ1 ሲረታ፣ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ፍልውሃ አገልግሎትን 3ለ0 በሆነ የፎርፌ ውጤት አሸንፏል፡፡
በጠረጴዛ ቴኒስ በሁለቱም ፆታዎች የተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ 3ለ0 ውጤት ተፈፅመዋል፡፡ በሴቶች መካከል በተደረገው ብቸኛ ጨዋታ ኢትዮ ቴሌኮም ብርሃንና ሰላም ማተሚያን ሲያሸንፍ፣ በወንዶች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፋፋ ምግብን፣ ኢትዮ ቴሌኮም ብራና ማተሚያን በተመሳሳይ ውጤት መርታት ችለዋል፡፡
በሴቶች ዳርት ስፖርትም ኢትዮ ቴሌኮም ድል የቀናው ሲሆን ተጋጣሚው ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን 2ለ0 አሸንፋል፡፡ በተመሳሳይ በወንዶች መከላከያ ኮንስትራክሽን ብርሃንና ሰላም ማተሚያን 2ለ0 ረቷል፡፡
ለበርካታ ወራት በሠራተኛው መካከል የሚደረገው የበጋ ወራት ውድድር በመጪዎቹ የረፍት ቀናትም በተለያዩ ስፖርቶች ፉክክሮች ቀጥለው ይካሄዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በአንደኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ የፊታችን እሁድ የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በተመሳሳይ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ይገናኛሉ፡፡ ሁለቱም ጨዋታዎች በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይከናወናሉ፡፡ በጎፋ ካምፕ በሚካሄዱ የሁለተኛ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ጨዋታዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ከኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎችን ያፋልማሉ፡፡ በተመሳሳይ ዲቪዚዮን በስብስቴ ነጋሲ ትምህርት ቤት ሜዳ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ቃሊቲ ብረታ ብረትን ከዘመን ባንክ፣ ረጲ ሳሙናና ዲተርጀንትን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ያገናኛሉ፡፡
ከነገ በስቲያ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ሜዳዎች የቮሊቦል፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ዳርትና ዳማ ጨዋታዎች በሁለቱም ፆታ በርካታ ፉክክሮች እንደሚደረጉም ከኢሠማኮ የስፖርት ክፍል የተገኘው የሳምንቱ መርሃ ግብር ያሳያል፡፡
ከሰላሳ በላይ የተቋማት የሠራተኛ ማህበራት የስፖርት ቡድኖች በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቮሊቦል፣ ዳማ፣ ቼስ፣ ገበጣ፣ ገመድ ጉተታና ሌሎችም የስፖርት ዓይነቶች ሠራተኛው ለረጅም ወራት ፉክክር የሚያደርግበት ይህ ውድድር ‹‹የሠራተኛው ስፖርት ለሰላም፣ ለጤናና ለምርታማነት›› በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዘንድሮው ውድድር 1015 ወንድ እና 260 ሴት በአጠቃላይ 1275 ሠራተኞች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ተፎካካሪ ናቸው፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም