
አዲስ አበባ፡- ሚዲያዎች ከዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ በመውጣት ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ የገነባቸውን ዘመናዊ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስቱዲዮዎችን ትናንት ሲያስመርቅ በወቅቱ እንደገለጹት፤ አሁን ባለንበት ዘመን ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችና ሐሰተኛ ትርክቶች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ፡፡ በእንዲህ አይነት ጊዜ እውነትን በእውቀት ላይ ተመሥርቶ ለሕዝብ የሚያደርስ የሚዲያ ተቋም እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ ላለው አብሮነትና አንድነት ትልቁ ፈተና የሆነው ሐሰተኛ ሚዲያና መረጃ መሆኑን ገልጸው፤ የሚዲያ ተቋማት ይህንን በመመከት ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር እና ሕዝብን የሚያስተሳስር ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አሚኮ ላለፉት 30 ዓመታት የክልሉ ሕዝብ መገለጫና ምልክት ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም ሀገራዊ አንድነት እና የሕዝቡን ትስስር የሚያጠናክሩ፣ በእውነታ ላይ የተመሠረቱ እና ጥራት ያላቸው መረጃዎችን ማስተላለፍ ይጠበቅበታል ብለዋል።
አሚኮ የአማራ ሕዝብ ከመላ ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቹ ጋር ተጋምዶ እንዲኖር ቀን ከሌሊት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሚኮ ተደራሽነቱን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ለሕንጻ ግንባታ የሚውል ቦታ አስረክቧል፡፡ አሚኮ በተረከበው ቦታ ላይ ተቋሙን የሚመጥን ሕንጻ ሲገነባ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
አሚኮ የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት ከማገልገል ባሻገር ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር በመቀናጀት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ በበኩላቸው፤ አሚኮ ለሀገራዊ አንድነት አስተሳሳሪ የሆኑ ዘገባዎችን እየሠራ ያለ ተቋም ነው ብለዋል።
አሚኮ ሥራውን በበኩር ጋዜጣ በአማርኛ ቋንቋ ጀምሮ ዛሬ ላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮች የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች መረጃዎችን ለሕዝብ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አሚኮ በሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ በዲጂታል ሚዲያው እና በሌሎች የመገናኛ ብዙኃን አማራጮች በብዝኃነት የማገልገል ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሠራ ያለ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
አሚኮ በአዲስ አበባ ያስመረቃቸው ዘመናዊ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ከቀደመው የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አመልክተው፤ አሚኮ ገዢ ትርክትን የሚያሰርጹ፣ ወንድማማችንትን የሚያጠናክሩና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም