ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙዚቃዊ ቴአትር በየመድረኩ እየተለመደ ነው፡፡ የሚቀርበው ደግሞ ለሙዚቃዊ ቴአትር ተብሎ በተዘጋጀ መድረክ አይደለም፡፡ የተዘጋጀው መድረክ ሌላ ይሆንና ግን እንደ ማጣፈጫ (ወይም እንደ መዝናኛ አይተውት ይሆናል)። ምናልባትም ሙዚቃዊ ቴአትር ራሱን ችሎ ለመድረክ የሚበቃ የማይመስለውም ይኖር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ይሄ ነገር እየተደጋገመና እየተለመደ ሲሄድ ሙዚቃዊ ቴአትር ማለት ራሱ እንደ ሙዚቃ የስብሰባ መዳረሻ እንዳይመስል፡፡
ሙዚቃዊ ቴአትር እና ሙዚቃዊ ድራማ ልዩነታቸው ልብ አይባልም፤ የአንዱን ስም አንዱ እየተካ እንጠቀምባቸዋለን፡፡ መድረክ ላይ የሚቀርብን ሙዚቃዊ ቴአትር ሙዚቃዊ ድራማ ሲባልም ይሰማል፡፡ ቴአትር ዋና መገለጫው ቀጥታ መሆኑ ነው (የመድረክ መሆኑ ማለት ነው)፡፡ ድራማ ግን በቀረጻ መልክ የሚሰራና በሬዲዮ ወይም በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነው፡፡ እንዲያውም ይሄ የጠቀስኩት ከላይ ከላይ ያለው ልዩነቱ እንጂ ጠለቅ ካልን ደግሞ ብዙ ልዩነት አለው፡፡ ለማንኛውም መድረክ ላይ የሚቀርቡ ሙዚቃዊ ቴአትሮችን ‹‹ሙዚቃዊ ቴአትር›› ብለን ነው ምንጠራቸው፡፡
ሙዚቃዊ ቴአትር ምናልባት መዚቃ ስለተጨመረበት መዝናኛም ሊመስል ይችላል፤ ግን ለመዝናኛ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው በደረቁ ከሚቀርበው በተሻለ የማዝናናት ባህሪ ይኖረዋል፡፡ ግን በሙዚቃው ውስጥም ራሱን የቻለ መልዕክትና አስፈላጊነት አለው፡፡ ትዕይንቶችም አጫጭር ስለሚሆኑ በየመሃሉ በሙዚቃ መሸፈን አለበት፡፡
አሁን ወደ ሙዚቃዊ ቴአትሮች እንግባ፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት ሙዚቃዊ ቴአትሮች ራሱን የቻለ መድረክ ተዘጋጅቶላቸው የሚቀርቡበት አጋጣሚ እጅግ በጣም ትንሽ ነው (በአገራችን ማለቴ ነው)፡፡ የሚቀርቡት ለስብሰባ ማስጀመሪያም ይሆናል፡፡
እነዚህ ሙዚቃዊ ቴአትሮች የሚዘጋጁት በታዋቂዎቹ ከያኒያን አይደለም፡፡ በየቀበሌውና በየክፍለ ከተማው የባህል ማዕከላትና የኪነ ቡድን ነው፡፡ በእነርሱ መዘጋጀታቸው አይደለም ችግሩ፤ ይዘታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ እስኪ ለስብሰባ ማስጀመሪያ ወይም እንዲህ እንደ ብሄር ብሄረሰቦችና ግንቦት 20 ዓይነት በዓላት ሰሞን የሚቀርቡ ቴአትሮችን ልብ ብላችሁ እዩዋቸው፡፡ ኢትዮጵያን ወክላ የምትቆም ሴት ትኖራለች፤ የሆነ ጥቁር ነገር ወይም የተቀዳደደ ልብስ ለብሶ የሚረብሽ፣ የሚበጠብጥ ገጸ ባህሪ ይኖራል፡፡ ያንን ሰው ተባብረው ይጥሉታል፤ ያባብሩታል፡፡ መልዕክቱም ተባብረን ድህነትን ወይም ለዕድገትና ለብልጽግና እንቅፋት የሚሆንን ነገር እንጣለው ማለት ነው፡፡
መልዕክቱ ችግር አልነበረውም፤ ዳሩ ግን ኪነ ጥበብ እንዲህ ቀድሞ ጭብጡ የሚታወቅ መሆን የለበትም፡፡ ልክ ገና ሲጀምሩ በምን እንደሚጨርሱት ይታወቃል፡፡ ሁለትና ሦስት ሆነው ስለአንድ ነገር እያወሩ የሆነ ረባሽ ወይም እብድ ነገር ከመጣ የሙዚቃዊ ቴአትሩ መጨረሻ ይታወቃል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ያለው ችግር የኢኮኖሚ ድህነት ብቻ ነው? ሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እኮ መሥራት ይቻል ነበር፡፡ ራሱ የህብረተሰቡንም ችግር ማሳየት ይገባል፤ የመንግስትንም ችግር ማሳየት ይገባል፡፡
ሌላው በሚቀርቡ ሙዚቃዊ ቴአትሮች ላይ የሚስተዋለው ነገር ብሄር ብሄረሰቦችን ለማካተት ሲባል የሚደረገው ተመሳሳይነት ነው፡፡ ይሄ በፌዴራል ደረጃ የተዘጋጀ መድረክ ላይ የሚቀርቡት ላይ ብቻ አይደለም፡፡ የአማራ፣ የኦሮሚያም ይሁን የትግራይ ክልል ውስጥ በክልል ወይም በዞን ደረጃ ሲዘጋጅ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ይካተትበታል፡፡ እንደ ኪነ ጥበብ ካየነው ይሄ የግድ አይሆንም፡፡ የትግራይን ብቻ፣ የአፋርን ብቻ፣ የአማራን ወይም የኦሮሞን ብቻ ማሳየት ይቻላል፡፡ እንዲያውም እንደዚያ ሲሆን ገላጭ የሚሆነው፡፡ ገና ወደ መድረክ ሲወጡ የብዙ ብሄር ብሄረሰብ አልባሳት የለበሱ ተዋናዮችን እናያለን፡፡ ከዚያ ታዳሚው በሙሉ ምን ሊባል እንደተፈለገ ይገባዋል፡፡
አብሮነትን፣ መተባበርን፣ ተከባብሮና ተቻችሎ መኖርን እኮ በአንድ አይነት ሙዚቃዊ ቴአትርም ማቅረብ ይቻላል፡፡ በአፋርኛ ወይም በሶማሊኛ የተዘጋጀ ሙዚቃዊ ቴአትር አማራን ወይም ኦሮሞን ያገለለ ነው ማለት ነው? ይሄ በኪነ ጥበብ አይሰራም፡፡ በዚህ ልማድ ከተሄደ እነዚያ ልጆች ሌላ አይነት የኪነ ጥበብ ሥራ መስራት ይቸገራሉ፡፡ አሁንም እኮ እያስቸገረ ነው፡፡ ለምሳሌ የግንቦት 20 ወይም የህዳር 29 አከባበር ያልሆነ ሌላ መድረክ ላይ እንኳን ሙዚቃዊ ቴአትር ሲቀርብ የብሄር ብሄረሰቦችን ሁሉ ያካተተ ነው የሚሆነው፡፡ እንግዲህ ይሄ ነገር ተለመደና በአንድ አይነት አለባበስ ቢቀርብ ‹‹ብዝሃነትን የጣሰ!›› ሊባል እኮ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከኪነ ጥበብ ጋር አይሄድም!
የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ላይ ራሱ የአንድን ታሪካዊ ቦታ ወይም የአንድን አካባቢ ባህል የሚያሳይ ሙዚቃዊ ቴአትር ማቅረብ ይቻላል፡፡ ይቻላል ብቻ ሳይሆን የተቻለም ስላየሁ ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም 11ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በሐረር ከተማ ሲከበር ሙዚቃዊ ቴአትር ቀርቦ ነበር፡፡ ሙዚቃዊ ቴአትሩ የሐረር ከተማን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል፡፡
ሙዚቃዊ ቴአትሩ ከቀድሞው የሐረር ከተማ ግንባታ አንስቶ የባህልና የቅርስ ባለቤትነቷን ጨምሮ የሚያሳይ ነበር፡፡ በተለያየ ወቅት ያስተዳደሩት አሚሮች ከተማዋን እንዴት በፖለቲካ፣ በባህልና በንግድ ያስተዳድሯት እንደነበር አሳይቷል፡፡
‹‹አዛን›› በማለት የጀመረው ሙዚቃዊ ቴአትር ሐረር በ13ኛው ክፍለ ዘመን ምን እንደምትመስል፣ ከዛም በ16ኛው ክፍለ ዘመን እንዴት የምሥራቅ አፍሪካ የንግድ ማዕከል እንደነበረች ቀረበ፡፡ ነጭ በነጭ የለበሱ በርካታ ወጣቶች የተሳተፉበት ቴአትሩ፣ የሐረርን በሮች ማለትም በድሪ በሪ፣ አስመዲን በሪ፣ ስጉዳጥ በሪ፣ አሱስም በሪና አሮብ በሪ ታይተውበታል፡፡ እነዚህ ነጫጭ የለበሱ ተዋንያን እንደ አጥር በመደርደር፣ የበር ድምፅ በማስመሰል በመካከላቸው ክፍተት እየፈጠሩ በወቅቱ የነበረውን የነጋዴዎች መውጣትና መግባት ለማሳየት ሲሞክሩ ከተመልካቹ ከፍተኛ አድናቆት ተችሯቸዋል፡፡
‹‹ሐረር ተሞሸረች›› የሚለው የቴአትሩ ክፍል ሐረር አሁን ያለችበትን የሚያሳይ ነበር፡፡ በንዋይ ደበበ ሙዚቃ ‹‹ቆንጅት ከሐረር ናት›› ታጅቦ ተመልካቹን በሐሴት ቁጭ ብድግ ያስባለ ነበር፡፡ ታዋቂ ድምፃውያን የሐረር አምስት በሮቿን ሲጠሩ ነጫጭ የለበሱ ወጣቶች ደግሞ በበሮቹ ቅርጽ ተደርድረው ወደ ስታዲየሙ ሲገቡ የክልሉን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ብዙዎች በጭብጨባ አጅበዋል፡፡ በቴአትሩ መጨረሻም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳት የለበሱ ተዋንያን በነዚህ በሮች ሲወጡና ሲገቡ ታይቷል፡፡
‹‹ሐረር ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ይህ ሙዚቃዊ ቴአትር ከጥንታዊቷ ሐረር ተነስቶ የዛሬይቷን ሐረር የሚያስቃኝ ነው፡፡ የሐረርን ታሪክ እንዲሁም ማኅበራዊ መስተጋብሩን ሙዚቃን ከተውኔት ጋር በማዋሐድ አሳይቷል፡፡ በቻላቸው ፈረጅ፣ ነብዩ ባዬና ተስፋዬ እሸቱ የተጻፈው ቴአትሩ፣ የተዘጋጀው በቻላቸውና ተስፋዬ ሲሆን፣ ከ150 በላይ ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡
ለአሥራ አንደኛው የብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል የተዘጋጀው ሙዚቃዊ ቴአትሩ ሐረር የተቆረቆረችበትን ታሪካዊ ዳራ በማስቃኘት ይጀምራል፡፡ ለቴአትሩ መነሻ የተደረጉት በአገር ውስጥና በውጭ ጸሐፍት የተዘጋጁ የታሪክ መጻሕፍትን ሲሆኑ፣ ሐረር አሁን ከምትገኝበት አስተዳደር ሥርዓት በፊት የነበረውን የአሚሮች አስተዳደር የሚያንፀባረቅ ክፍል በቴአትሩ ይገኛል፡፡
ወደ አንድ ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃ ገደማ የሚወስደው ‹‹ሐረር ኢትዮጵያ››፣ ሐረርን ካስተዳደሯት 72 አሚሮች መካከል 42ኛው አስተዳዳሪ የነበሩትን አሚር ኑር እንደ አንድ ገፀ ባሕሪ ወስዷል፡፡
እንግዲህ ይህ በ11ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በላይ ላይ የታየው ሙዚቃዊ ቴአትር ለታዳሚው ሁሉ የሐረርን ምንነት አሳይቷል ማለት ነው፡፡ ኪነ ጥበብ እንዲህ ሲሆን ግልጽ የሆነ ጭብጥ ይኖረዋል፡፡ አለበለዚያ ሁሉንም ነገር ለማካተት ሲል አንዱንም በግልጽ ሳያሳይ ይቀራል፡፡ እንዲህ አይነት ሙዚቃዊ ቴአትሮች እንዲቀርቡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው!
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
ዋለልኝ አየለ