በችግሮች እየተፈተነ ያለው የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የውጪ ንግድ

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ቀዳሚና የተሻለ አቅም ያላት ሀገር ብትሆንም በቆዳና ቆዳ ውጤቶች የምታገኘው የውጭ ገቢ ግን ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ እንደመጣ ይገለጻል። ተግዳሮቶቹም በርከት ያሉ እንደሆኑ ይነገራል። ይህ ለምን ሆነ፤ ተግዳሮቶቹ ምን ምን ናቸው፤ የመፍትሄ አማራጮቹስ? የተለያዩ በዘርፉ የሚሰሩ አካላት ሀሳባቸውን አጋርተውናል ።

አቶ ዙልፊከር አባጅሃድ ይባላሉ። በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ካላቸው ሀገራት ተርታ ብትመደብም ከአላት ሀብት አኳያ ግን ከቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እንዳልሆነች ይናገራሉ። በተለይም ከውጭ ምንዛሬ ግኝት አንጻር ከዓመት ዓመት እየቀነሰች እንደሄደች ያስረዳሉ።

በከብት ደረጃ ብቻ ወደ 165 ሚሊዮን የሚደርስ ሀብት ያላት ኢትዮጵያ ሀብቷን እሴት ጨምራ መጠቀም ባለመቻሏ ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በኤክስፖርት ዘርፉ ከቡና ቀጥሎ ገቢ በማስገኘት የሚጠቀሰውን ዘርፍ አሁን ላይ ወደ 30 ሚሊዮን በማይበልጥ ዶላር ገድባዋለች። የውጭ ገቢዋንም ከአንድ ሦስተኛ እንዳይወጣ አድርጋዋለች ብለዋል። ለዚህም መንስኤው ዘርፈ ብዙ እንደሆነ አስረድተዋል።

እንደ አቶ ዙልፊከር ገለጻ፤ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የውጭ ምንዛሬ ግኝት መቀነስ ምክንያት በማዕከል ደረጃ በተሰራው ጥናት ተለይቷል። ሰባት መሰረታዊ ችግሮች እንደሆኑም ታውቋል። አንደኛው በክላስተርና ግብዓቱ በሚገኝበት አቅራቢያ ላይ የተተከሉ ኢንዱስትሪዎች አለመኖራቸው ወይም የአቀማመጥ ሁኔታቸው የተበታተነ ሲሆን፤ ሁለተኛው የስጋ ተረፈ ምርት የሆነው ቆዳና ሌጦ ክትትልና ድጋፍ ስለማይደረግበት ከጥራት አንጻር ችግር እያጋጠመው መሆኑ ነው። በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚጠቀሰው ደግሞ የቴክኖሎጂ አቅም ውስንነት ነው።

ያለቀለት ቆዳን ማምረትና በተለያየ ዲዛይን ለዓለም አቀፍ ገበያው ለሚቀርብ የተሻለ የቴክኖሎጂ እውቀት ያስፈልጋል። በተጨማሪም ማሽኖች ሊኖሩ ይገባል። ይህንን ከማሟላት አንጻርም ኢንዱስትሪዎቻችን በእጅጉ ውስንነት አጋጥሟቸዋል የሚሉት አቶ ዙልፊከር፤ በአራተኛ ደረጃ የተለየው ተግዳሮት ዓለም አቀፍ ደረጃን አለማሟላት እንደሆነ ጠቅሰዋል። በማህበራዊና አካባቢያዊ ተጽዕኖ ምክንያት ወደ ኋላ መጎተት፤ በዓለም አቀፍ ኦዲቱ የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመቀመጥ እንደ አንድ ችግር ተደርጎ ተወስዷልም ብለዋል።

አንድ የቆዳ ፋብሪካ ሌጦን ያለቀለት ደረጃ ላይ ለማድረስ ቢያንስ ወደ 60 አይነት ኬሚካል ይጠቀማል። ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኬሚካል የሚመጣውም ከውጪ በውጪ ምንዛሬ ነው። በተጨማሪም ፋብሪካዎች ያለቀለት ቆዳና ሌጦን ለማውጣት ቢያንስ 21 ቀን ይፈጅባቸዋል። ለዚህም በቀጣይነት ምርት ለማምረት የሚያስችለውን ጥሬ እቃ ቀድመው ማስገባት ይኖርባቸዋል። ቢያንስ ለስድስት ወር ያህል ሥራቸውን ሊያከናውኑበት የሚችል ግብዓት በስቶክ መያዝ አለባቸውም። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የግድ ፋይናንስ ሊኖራቸው ግድ ይላል። በመሆኑም እነዚህን ተግባራት ለማከናወን የሚያስችላቸው የፋይናንስ አቅም ውስንነት ችግር አንዱና አምስተኛው ተግዳሮት መሆኑንም አንስተዋል።

ስድስተኛው ከገበያ አማራጭና ራስን ማስተዋወቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር ነው የሚሉት ሥራአስኪያጁ፤ በአለማቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተመራጭ ለመሆን መጀመሪያ መደረግ ያለበት ራስን መሸጥ ነው። ማንነትን፣ ምን እንዳለ በሚገባ ማሳወቅ ያስፈልጋል። ኤክዚቢሽኖች ላይ መሳተፍ፤ የራስን ብራንድ መስራት፤ ምርትን እያሳዩ የገበያ ትስስር መፍጠር ዓለም ከመጠቀባቸው ተግባራት መካከል ናቸው። እንደ ሀገር ግን ይህ እየሆነ አይደለም። በዚህም አንዱ ተግዳሮት ተደርጎ የተወሰደው የገበያ አማራጭና ራስን ማስተዋወቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሌላውና ሰባተኛው የተለየው ችግር ተቋማት በትስስር ያለመስራታቸው ሁኔታ ሲሆን፤ የግብይት ስርዓቱን የሚከታተለው አካል፤ የእንስሳት ሀብቱን የሚመለከተው አካል፤ የቴክኒካል ድጋፍ ላይ የሚሰሩ አካላትን ጨምሮ ተናቦ ሲሰራ አይታይም። በዚህም ጥራት ያለው ምርትን አቅርበን ገቢያችንን በሚፈለገው መልኩ እንዳናደርግ ተገድበናል ሲሉ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ጸሀፊ አቶ ዳኛቸው አበበ በበኩላቸው፤ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች የሚገኘው ገቢ የቀነሰበት ምክንያት ብዙ ቢሆንም በዋነኛነት የሚጠቀሰው ችግር የጥራት ችግር እንደሆነ ይናገራሉ። 60እና 70 በመቶ በጥራት የሚገኘው ቆዳ 20 በመቶ ላይ እንዲቀመጥ ያደረገው በቆዳና ሌጦ ኮርፖሬሽን እንዲሁም በግብርና ኤክስቴንሽን ደረጃ የሚደረገው ቁጥጥር በመቋረጡ ይህ ሁኔታ እንደተፈጠረም አስረድተዋል።

35 በመቶ በእርድ ወቅት የሚፈጸም ችግር ሲሆን፤ 65 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በቁም እንስሳት ላይ የሚፈጠር ችግር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዳኛቸው፤ ባለፈው ስምንት ዓመታት በከፊል የለፋ ቆዳ እንዳይወጣ በሕግ መታገዱና ወደ ውጪ ገበያው ከተገባ በ150 በመቶ ታክስ ይደረጋል መባሉ አንዱ ለገቢ ቅነሳው አስተዋጽኦ እንደነበረው ተናግረዋል።

መፍትሄው አንድ ነው። ችግሩን ለይቶ ወደ ሥራው መግባት። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ በጥናት ጭምር የተለየ ሥራ ሰርቷል። በርካታ ለውጦችም እየመጡ ይገኛሉ የሚሉት አቶ ዙልፊከር፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚመራ አንድ የኢንዱስትሪ አምራች ካውንስል እንደተቋቋመና ማን ምን ይሰራል የሚለው ተለይቶ ወደ ስራ እንደትገባ አመላክተዋል። እያንዳንዱ ተቋም የራሱን እቅድ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል። አምራች ካውንስሉ በሁሉም ዘርፍ ላይ ያሉ አመራሮችን ያካተተ በመሆኑ በዘርፉ በተለይም ከፍተኛ አቅም ባላቸው ኩባንያዎች ያሉ ችግሮችን ለይቶ እየሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በአገዋ ምክንያት ሥራ አቁመው የነበሩ ኩባንያዎች ሌሎች አማራጮችን ተጠቅመው እንዲሰሩ መደላደሎች እንደተፈጠሩ አንስተውም፤ አሁን ላይ የገበያ አማራጫቸው አሜሪካ ብቻ የሆኑ አምራቾች አፍሪካ ሀገራት እያጥለቀለቁ እንደሆነና ገቢውን በተቻለ መጠን ከፍ እያደረጉ እንዳሉም አስረድተዋል።

አቶ ዳኛቸው በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አሁን ላይ እየተሰሩ ባሉ ተግባራት መፍትሄዎቹ እየታዩ ናቸው። ለአብነትም በከፊል የለፋ ብቻ ሳይሆን የአለቀለት ቆዳ ጭምር እንዲላክ መፈቀዱ፤ ያለቀለት ጫማና ቦርሳ እንዲሁም ሌሎች ምርቶችን ለውጪ እንዲቀርብ መደረጉ እንደ ሀገር የተሻለ ገቢን እንድናገኝ አስችሎናል። ይሁን እንጂ ያለው ችግር ቀላል የሚባል ስላልሆነ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት በትኩረት መስራት ይርባቸዋል። ዘርፉ ማህበረሰቡን ጭምር ያሳተፈ በመሆኑ ግንዛቤ የመፍጠሩ ጉዳይም ትኩረት ሊቸረው ይገባል።

ዘርፉ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በዓመት እስከ 130 ሚሊዮን ዶላር ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርት ገቢ ያስገኝ ነበር። ከ2010 ዓ.ም በኋላ ግን ይህ ሁኔታ በእጅጉ ቀንሷል። የ2016ዓ.ም ከአጠቃላይ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ገቢም 27 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር። 2017 ዓ.ም የአምስት ወሩ የተገኘው ደግሞ 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ነው።

ሁለቱም ባለድርሻ አካላት የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርት ሀገሪቱ ከአላት ሀብት አንጻር ቢሰራበት የወጪ ገቢው ብቻ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ገቢም በእጅጉ ኢኮኖሚዋን የሚደግፍ እንደሆነ አስረድተዋል። በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ታስገኘው የነበረውን የውጪ ምንዛሬ በእጥፍ ለማሳደግ የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል። ይህ ካልሆነ ደግሞ ችግሩ ከዚህም እንደሚብስ ተናግረዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You