ከተረጂነትና ከጠባቂነት አስተሳሰብ የተላቀቀ፣ ሀገር የሚያለማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሁሉም ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ የግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁን ጠቅሰን በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል። መንግሥት ተረጂ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር ያስችል ዘንድ ‹‹ከተረጂነት ወደ ምርታማነት›› የሚል ንቅናቄ በ11 ክልሎች እየተገበረ ነው። ይህ ንቅናቄ በተጨባጭ መሬት ላይ እንዲወርድና ኢትዮጵያ ላሰበችው የምግብ ሉዓላዊነት የማስከበር ሀገር አቀፍ ጥረት እንዲፋጠን ምን አይነት ሥራዎች ሊከናወኑ ይገባል? ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች አናግረናል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ዳይሬክተርና ተመራማሪ ዶክተር ታደለ ማሞ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ለረጅም ጊዜ የተለያዩ መርሃ-ግብሮች ተነድፈው ተግባራዊ ተደርጓል። ይሁንና እነዚህ መርሃ ግብሮች የጠባቂነትና የተረጂነት ስሜት ፈጥሯል ተብሎ በባለሙያዎች ይተቻል። ያንን ተከትሎ ልማታዊ ሴፍትኔት እንዲተገበር የተደረገ ሲሆን፤ ይህም ተረጂዎች እየሰሩ የሚደገፉበትና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከእርዳታ ሥርዓቱ የሚወጡበት ሁኔታ በመፍጠር የጠባቂነት መንፈስን ለማስወገድ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ይህም ሆኖ ግን ጥቂት የማይባለው ሰው ከመርሃ-ግብሩ ተመርቆ ለመውጣት ያለመፈለግ ዝንባሌ ይታይባቸዋል።
በሌላ በኩልም አስፈፃሚው አካል የግልፀኝነትና ተጠያቂነት ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ለመርሃ-ግብሩ የተመደበው በጀት ለምዝበራ የተጋለጠበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበርም ያስታውሳሉ። መንግሥት ይህንን በመገንዘብ ከልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ-ግብሩ ጎን ለጎን መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ያስችላል ያለውን ‹‹ከተረጂነት ወደ ምርታማነት›› የሚል ንቅናቄ መተግበሩን ይገልጻሉ። ይህም ተረጂው ማህበረሰብ አምራች እንዲሆንና በራሱ ታግሎ ከጠባቂነት አስተሳሰብና ተግባር እንዲወጣ ያለመ መሆኑን ያስረዳሉ። በዚህም በርካታ ተረጂዎች የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ከጠባቂት መውጣት እየቻሉ ቢሆንም የተረጂነትና የጠባቂነት አስተሳሰቡ ስር የሰደደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ ካቀደችው ግብ አንፃር በሚፈለገው ፍጥነትና መጠን ሽግግሩን ማፋጠን ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
ወይዘሮ ሰዒዳ ከድር በግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አማካሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የገጠር ምግብ ዋስትና ፕሮግራም በ1997 ዓ.ም ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ዘንድሮ በመገባደድ ላይ ያለውን ጨምሮ በአምስት ምዕራፎች የመርሃ-ግብሩ ትግበራ ሽፋኑን በማሳደግ የተጠቃሚዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና ለመለወጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። በተለይም በአምስተኛው ምዕራፍ ፕሮግራሙ በአስር ክልሎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ 7ነጥብ9 የሚልቁ ተጠቃሚዎችን በማቀፍ የሚተገበር ነው። በመሆኑም በፕሮግራሙ የመጀመሪያ ዓመት ላይ ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የልየታ ሥራ ተሠርቷል። በዚህም አሰራር የድሃ ድሃ የሆኑ ቤተሰቦች ፍትሐዊ በሆነ የልየታ አሰራር ተለይተው የፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ማሻሻያዎች እና አዳዲስ የአሠራር ሥርዓቶችን በማዘመንና በማስፋፋት ለመተግበር ያለው ጥረትና ቁርጠኝነት እንዳለ ሆኖ በትግበራው ሂደት የተለያዩ ችግሮች እንዳጋጠሙት ይጠቀሳል። አማካሪዋ እንደሚሉትም፤ በፕሮግራሙ ዲዛይን መሠረት ከለጋሾች መቅረብ የሚገባው ሀብት ላይ ከፍተኛ መዘግየትና የገንዘብ መጠን መቀነስ፣ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ፣ ኮቪድና ግጭት ምክንያት ለልማት መዋል ያለበት ሀብት ወደ እለት ደራሽ ምላሽ መዞሩና የተጠቃሚዎችን ጥሪት ማመናመኑ መርሃ-ግብሩ በተሳካ ሁኔታ እንዳይተገበር እንቅፋት ከሆኑ ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው።
በተጨማሪም የዋጋ ንረት፣ በቤተሰብ ደረጃ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎችን ኑሮ እንዲሻሻል ከማድረግ አንፃር ለልማት ሊውሉ የሚችሉ ያገገሙ ተፋሰሶችን ወደ ልማት ለማስገባት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን፤ በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ የሥራ ዘርፍ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ተጨማሪ ገቢና ጥሪት በመፍጠር ከፕሮግራሙ እንዲመረቁ ከማድረግ አንፃር በቂ የብድር አቅርቦት አለመኖሩ በአፈፃፀም የተለዩ ክፍተቶች መሆናቸውን ያስረዳሉ። እንዲሁም ‹‹በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት ተጠያቂነት መንፈስ ሥራቸውን አለማከናወን ክፍተቶች ታይተዋል›› ይላሉ።
በሌላ በኩል የተረጂን ቁጥር እና የተረጂነትን ስሜት ወይም አመለካከትን መቀነስ እና አደጋን የሚቋቋም ማህበረሰብ መፍጠር መቻል የሀገሪቱ እድገት አንዱ መገለጫ ነው። በዚህ ረገድም በዘርፍ ላይ በሁሉም ረገድ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የግብርና ሽግግር በማምጣት ለዜጎቹ በቂ፣ ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብ አቅርቦትን በማሻሻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ወይዘሮ ሰዒዳ ያመለክታሉ። ፕሮግራሙ የኅብረተሰቡን የምግብ ክፍተት በማሟላትና በተለያዩ የዕድገት መርሃ-ግብሮች ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ በማድረግ ሊቆጠርና ሊታይ የሚችል ለውጦች እንዲመጡ አስተዋፅኦ አድርጓልም ባይ ናቸው።
ይሁንና ሀገሪቱ ካስቀመጠችው የተረጂነት ቅነሳ መርሃ-ግብር አንጻር ሲታይ የተረጂነት አመለካከትን በማስተናገድና እርዳታን በመጠበቅ የእድገት ግቦችን ማሳካት ከባድ መሆኑን ያስረዳሉ። እንዲሁም በርከት ያለ ቁጥር ያለው ተረጂ ማህበረሰብንም ይዞም ሀገሪቷ ያስቀመጣቸውን ራዕይ ማሳካት አደጋች እንደሆነ ነው ያስረዱት።
ስለሆነም የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን በአካባቢው ባለው እምቅ ሀብትና ፀጋ ተጠቅሞ በልማት እንዲሳተፉ በማድረግ ኑሯቸውን ማሻሻልና ከፕሮግራሙም በስፋት እየተመረቁ እንዲወጡ፣ የጠባቂነት አመለካከቶች ተወግደው የትርፍ አምራችነት ስሜት በተጠቃሚ የማህበረሰብ ክፍል እንዲሰፍን ማድረግ ተጠባቂ ሥራ እንደሆነ አማካሪዋ ይናገራሉ። በዚህ ረገድ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በቅንጅት የመሥራት ባህልን ማጎልበት እንደሚገባቸው ጠቅሰው፤ ‹‹በኃላፊነት፣ በቁርጠኝነትና በተጠያቂነት መንፈስ መሥራት ያስፈልጋል›› ይላሉ። ይህንንም ለማረጋገጥ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ የሚታቀዱ እና የሚተገበሩ ሥራዎች መኖራቸውና የቁልፍ አመላካቾች አፈጻጸሞችን በየጊዜው አፈጻጸማቸውና ውጤታቸው እየተገመገመ ለውጥ ለማምጣት መሥራት ግድ እንደሚል ነው ያስገነዘቡት።
ዶክተር ታደለ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ከሁሉ በፊት ከተረጂነት አስተሳሰብ እንዲላቀቁ የሰውን ንቃተ ህሊና መገንባት ያስፈልጋል። ‘ማምረትና ራሴን መቻል እችላለሁ፤ ከራሴ አልፎ ለሌሎች እተርፋለሁ’ የሚል አስተሳሰብ መፍጠር ይገባል። ለዚህ ደግሞ የመማሪያ መድረኮች ማዘጋጀት ይጠይቃል። ግንዛቤ ከመፍጠር ጎን ለጎን ተረጂዎችን ወደ ልማት ለማስገባት ወሳኝ የሆኑ እንደ መሬት፣ የብድር አገልግሎት፣ ግብዓትና መሰል ድጋፎች በበቂ ሁኔታ መመቻቸት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪ አጋር የውጭ ድርጅቶች ችግሩ ሲፈጠር ብቻ እሳት ከማጥፋት በዘለለ መሠረታዊ ችግሮቻችንን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ የተቀናጀ የማስተባበር ሥራ መሠራት አለበት።
‹‹ችግሩን የለየ፣ ከአጭር እስከ ረጅም ጊዜ መፍታት የሚያስችል እቅድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል›› የሚሉት ዶክተር ታደለ፤ በአጭር ጊዜ መጀመሪያ የህይወት አድን ሥራዎች ላይ ማተኮር፤ በሁለተኛ ደረጃ ከተረጂነት እንዲላቀቁና ወደ ልማት እንዲገቡ በማድረግ እሴት መገንባት ያስፈልጋል። ጎን ለጎንም ‘እችላለሁ’ የሚለውን አስተሳሰብ እንዲያሳድጉ ንቃተ ህሊናቸውን ማሳደግ ወሳኝ ነው።
በተጨማሪም በየአካባቢው ያለውን እምቅ አቅምና የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ከተረጂነት እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ ይናገራሉ። ለዚህም በዋናነት የክልል መንግሥታት ኃላፊነት ወስደው ያሉትን ሀብቶች በመለየትና ጥቅም ላይ ማዋል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መሥራት ይገባቸዋል ይላሉ። አብነት አድርገውም ‹‹ደቡብ ላይ እንሰትን ለምግብ ዋስትና ይጠቀሙበታል፤ ሆኖም በተመሳሳይ አግሮኢኮሎጂ ያላቸው አካባቢዎች ላይ ሲጠቀሙበት አናይም፤ በመሆኑም አንድ አካባቢ ያለውን ብቻ ሳይሆን ከሌላ አካባቢ ተሞክሮ መውሰድ ያስፈልጋል›› ይላሉ። ይህንን ሥራ ከልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ-ግብሩ ጋር ማገናኘት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ለረጅም ጊዜ የቆዩትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ጊዜ ማላቀቅ እንደፈተና ሊታይ እንደሚችል አንስተው፤ የኅብረተሰቡን ንቃተ ህሊና የማሳደጉ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚገባው ያስገነዝባሉ። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች ርዳታን አሳቦ እጅ በመጠምዘዝ ሀገራዊ ልዕልናን የሚዳፈሩና ፖሊሲን የመሻር ፍላጎት ሊኖራቸው ስለሚችል ተቀራርቦ በድርድር መፍታት እንደሚጠይቅ ይናገራሉ። ‹‹ እነዚህን ስጋቶች በማስወገድ ከተረጂነት የተላቀቀ አልሚ ማህበረሰብ መፍጠር ከተቻለ ኢትዮጵያ የረሃብ ተምሳሌት ተደርጋ በዓለም አደባባይ የምትታወቅበት ገፅታ ይቀየራል›› ይላሉ። ኢትዮጵያ እንደሀገር በየትኛውም መድረክ ላይ ራሷን ማስከበርና የመከላከል አቅሟ ይጎለብታል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም