አዲስ አበባ ፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ሌሎች የሀገሪቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በወደብ አጠቃቀም እንዲሁም በሌሎች የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን አስታወቁ።
በጅቡቲ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከጅቡቲ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፤ የጉብኝቱ ዓላማ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማድረግ ነው። ከጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ከውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር በሁለትዮሽ እና በቀጣናዊ የፖለቲካና የደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በንግድ ጉዳዮች፣ በወደብ አጠቃቀም እና በወቅታዊ ቀጣናዊ ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያም መምከራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ከባለሥልጣናቱ ጋር ገንቢ እና ፍሬያማ ውይይት እንዳደረጉ አመልክተዋል። ኢትዮጵያና ጅቡቲ በባቡር፣ በወደብና መሠረተ ልማት መስኮች ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ጠቁመዋል። ሀገራቱ በጣም ልዩ እና ጠንካራ ትብብር እንዳላቸውም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እ.አ.አ በ1984 እንደተጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም