- ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩም ተጠቆመ
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከነፋስ ኃይል 1 ነጥብ 35 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚያስችል አቅም እንዳላት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ። ዘርፉን ባለሀብቶች እንዲያለሙ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሰሃ ጌታቸው በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከነፋስ ኃይል ብቻ 1 ነጥብ 35 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚያስችል አቅም አላት። በአሁኑ ሰዓት ከዚህ ዘርፍ ማመንጨት የተቻለው ከ400 ሜጋ ዋት የማይበልጥ ነው።
ሀገሪቱ በዘርፉ ካላት ሀብት አንጻር እስከ አሁን የተመረተው ኢምንት እንደሆነ የገለጹት አቶ ፍሰሃ፤ ከንፋስ የሚገኘውን ኃይል ለማሳደግ መንግሥት ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ ቢሰማራ የኃይል አቅርቦት መጠንን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደሚያስችል አመልክተዋል።
የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት መጠን ለማሳደግ በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ተቋሙ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችን ሁለተኛ አማራጩ አድርጎ እየገነባ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ለብሄራዊ የኃይል ቋቱ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማሳደግም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የነፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ከ14 ዓመት ወዲህ መገንባት እንደጀመሩ የተናገሩት አቶ ፍሰሃ፤ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉት ጥቂት የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ናቸው ብለዋል። በተለይም የውሃ መጠን በሚቅንስበት የበጋ ወራት የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን ክፍተት ከመሙላት አንጻር አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ሰዓት ከሀገሪቱ አጠቃላይ የማመንጨት አቅም ውስጥ የንፋስ ኃይል 7 ነጥብ 14 በመቶ ድርሻ እንዳለው ያመለከቱት አቶ ፍሰሃ፤ በ2016 በጀት ዓመት የ3 ነጥብ 32 በመቶ አስተዋጽኦ በማበርከት ለውሃ ኃይል ማመንጫዎች ተጨማሪ አቅም እንደፈጠረ አስታውሰዋል።
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ከአሸጎዳ 120 ሜጋ ዋት፣ ከአዳማ-1 51 ሜጋ ዋት፤ እንዲሁም ከአዳማ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 153 ሜጋ ዋት፤ በድምሩ 324 ሜጋ ዋት በማመንጨት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
120 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአይሻ-2 እና 100 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በግንባታ ላይ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታው ሳይጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት 80 ሜጋ ዋት እያመነጨ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የንፋስ ኃይል ማመንጫ በሶማሌ ክልል አይሻ ወረዳ ለመገንባት አሜአ ፓወር ከተሰኘ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያ ጋር ስምምነት ስለመፈረሙ አስታውሰዋል። ፕሮጀክቱ በመንግሥት እና በግል አጋርነት ማሕቀፍ የሚገነባ ትልቁና የመጀመሪያው የንፋስ የኃይል ማመንጫ ኢንቨስትመንት እንደሆነም አቶ ፍሰሃ አስረድተዋል።
በአሁኑ ጊዜ ለንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶና የሕግ ማሕቀፍ ተዘጋጅቶ ዘርፉ ለግል አልሚዎች ክፍት መደረጉ መደላድል የፈጠረ ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሀብቶች ዘርፉን በማልማት ሥራ ቢሰማሩ የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ ለሀገር ልማትና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት በማዋል እድገትን ማስቀጠል እንደሚቻል አመልክተዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም