ደፍቴ

የማለዳዋ ጮራ መስኮቱን አልፋ የልጅ እግሯን ከወለሉ ስትተክል ጦቢያው ለቁንን ባሏ ገበታ አቀረበችለት:: አፋቸውን ሽረው እንዳበቁ “ጌታነህ መሬቱን የኩል ያዘው ብሎኛልና መሄዴ ነው:: ከብቶችን በጊዜ ሰትሪ ቤቱንም ነቅተሽ ጠብቂ:: ሽማግሌ ተማርጠን ውል ስለምናስር በዚያ ላይ ፍንጥሩን ምኑን ስንል ይመሻል፤ በጨረቃ ልምጣ ብል እንኳን በድንበር የተጣላሁት ያ ማን ነው… አስታጥቄ ገድየው የትም እሰደዳለሁ ብሎ መሳሪያ ገዝቷል አሉ፣ ስለዚህ ማደሬ አይቀርም” አለ አገጩን በእጁ ጭኖ::

ጦቢያው ልቧ በደስታ እየሞቀ “ቢቀርብንም ማስተራረፉ ነው አንዱን በሬ ሽጥና ብረት ግዛ መኖሩ ቤት ይጠብቃል እንጂ መች ይጎዳል?” አለች ገበታውን ከፍ እያደረገች:: “አይ ጦቢያው …” አለና እየሳቀ “የሚጠብቀው አፍ ነው” ብሏት ወጣ:: ጦቢያው ከእይታዋ እስኪርቅ ከበራፍ ቆማ በዓይኗ እየሸኘችው “አፍ ነው የሚጠብቀው ይላል? ወገኛ ወሬስ ታውቃለህ ሱሪው ጅል” አለች በብሽቀት::

ጦቢያው ገበያ ለመሄድ ጓዟን ልታሰናዳ ማጀት ገባች:: የሸመነችውን ጥበብ ቀሚስ ደርግማ ባውንዷን አሠረች:: ጉትቻዋን ሰክታ፣ ዓይኗን በቀጭኑ ተኩላ፣ የአንገት ድሪዋን አጥልቃ፣ ጫንቃዋ ላይ ነጠላ ጣል አድርጋ፣ ድጓን ታጥቃ፣ አልቦዋን አጥልቃ መስታወቱ ፊት ቆመች:: አትኩራ እያየች “አንች ጦቢያው” አለቻት መስታወቱ ውስጥ ያለችውን ራሷን እያየች:: “ይሄ ውበትሽ ስንት ጉድ አፈላ? አንችን ለማግባት ያልተሳለውን ጠይቂኝ:: ይሄ ውበትሽ ጥሬ ከብስሉን ሰነፍ ከብርቱን ቃል አናገረ:: ታውቂያለሽ… ቁንጅናሽ እኮ የወንድነት መለኪያ ነው! አሁን ግን እንጃ … መጥፎ ይሁን ጥሩ እድል የማያላውስ ፍቅር ጥሎብሻል:: ብቻ እሱ የአባቴ አምላክ ይሁንሽ” ብላ ቋጠሮዋን አዝላ ከቤት ወጣች::

ገበያ ስትደርስ አማረች ቀድማት ጤፍ ዘርግታ አገኘቻት:: ሰላምታ ተለዋውጠው ከሥሯ ተቀመጠች:: የገበያውን የዋጋ ውሎ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ አማረች ጦቢያውን የጎሪጥ እየተመለከተች “መአዛሽ እንደ ውሽማ ወጥ ከሩቅ ይጣራል ምንድን ነው እሱ?” በማለት በነገር ጎሸመቻት:: ጦቢያው የወሬዋን ዳና አውቃው ኖሮ “ዓይንሽ እኔ ላይ ይጠባል ቡዳ” አለች የመጣባትን ንዴት ለመሸሸግ እየጣረች::

አማረች የኮረኮሯትን ያህል እየሳቀች “እንኳን ሰውን ሰው የማይበላውን ብበላስ መርጬ እበላለሁ እንጂ እንደ አንች ያለውን እበላለሁ?” አለች የፊቷ ጸዳል እጅጉን እያበራ:: ጦቢያው ከተቀመጠችበት እምር ብላ ተነሳችና “እኔ ልጅት ለመበላት ምን ያንሰኛል?” ብላ አራስ ነብር መስላ ከፊቷ ቆመች:: አማረች የጦቢያውን ቅርጫት አንስታ ወደ እራሷ እያስጠጋች “ባለፈው ተበድረሽ ለዛሬ እሰጥሻለሁ ያልሽኝን እህልም ልውሰድ” አለች በንቀት ዓይን እያየቻት:: ጦቢያው ቁጣዋ ገዝፎ “ንገሪኝ እኔ ለመበላት ምን ያንሰኛል?” አለች በመንጨርጨር:: አማረች ከት ብላ እየሳቀች “እሱንማ ለማወቅ ወንዶችሽን ጠይቂያቸው” በማለት መለስችላት::

ጦቢያው የባሰውን በግና ለጥፊ እጇን ሰነዘረች:: አማረች ከተቀመጠችበት ሳትነሳ በእርግጫ ስትላት የኋሊት እግሯ ከዳት:: ከወደቀችበት ልትነሳ ስትል አማረች በእግሯ ረምዳ ይዛ “አግድም አደግ ባትሆኝ ጥሩ ነው ልክ የለሽ” ብላት መልሳ ተቀመጠች:: ጦቢያው “ልብ አድርጉ” እያለች ስትጮህ አጥናፉ ሽመሉን አገንድሮ ከቦታው ደረሰ:: ይህን ጊዜ አማረች ጓዟን ሸክፋ ሹልክ አለች:: ጦቢያው በበኩሏ ጨርቋን እያረጋገፈች ግርምት ውስጥ ሆና ከእግር እስከ እራሱ በዓይኗ እንደ ሽንኩርት ላጠችው:: ውሽማዋ አጥናፉ ነው:: ተንደርድራ አንገቱ ላይ ተጠመጠመችበት:: “ምነው ጠፋህ?” አለችው እቅፏን እንዳጠበቀች:: “መንገድ እየሄድኩ ነበር ጩኸት ስሰማ ነው ወደዚህ ያገለልኩት ምን ሆናችሁ ነው ጦቢያው?” አለ ቁልቁል እየተመለከታት:: ጦቢያው የናፍቆት ረሃብ አንጀቷን እያመሰው “እሱን ተወውና ጉዞህ የግድ ታልሆነ ባለቤቴ አዳሩን መንገድ ስለሄደ ከብት ሲገባ ድረስና ዓለማችንን እንቅጭ” አለችው በተራዋ በስስት እያየችው:: “አንች ሌባ ጠላሽ ቀጭን ታልሆነ እመጣለሁ” አለ አጥናፉ እየሳቀ:: ጦቢያው “እንግዲያውስ ቶሎ ልሂድና ተሰናድቼ ልጠብቅህ” አለች ለጉዞ ከቆመችበት እግሯን ነቅላ:: አጥናፉም መዳረሻ እንዲሆነው አንድ ሁለት ሊል መሸታ ቤት ገባ::

ጦቢያው ከቤት እንደደረሰች ለእንግዳ የሚሆን ማለፊያ ነገር አልነበራትምና ወዲያ ወዲህ ትራወጥ ጀመር:: ከመሃል “በእንተ ስምአ ለማርያም ስለእመብርሃን ክብር ብለው” የሚል ድምጽ ሰምታ ሞሰቧን ብትከፍተው ባዶ ሆኖ አገኘችው:: አድርሻለሁ ማለት እየከበዳት “የበሰለ እህል የለም ተሜ ምን ይሻላል?” አለች የተሰለበ አኮፋዳው ላይ ዓይኗን ተክላ:: የቆሎ ተማሪው “ጥሬ እህልም ቢሆን ግድየለም” አለ በተማጽኖ:: ጦቢያው ማጀት ገብታ በድርበብ ተልባ ሰፍራ ዘከረችው:: ተማሪው ይሉንታ ከብዶት እየተቅለሰለሰ “እመይቴ” አለ የግዱን:: “አቤት” አለች ጦቢያው ዓይኑን በዓይኗ እየፈለገች:: “እመብርሃን ትቁምልዎና ታላስቸገርኩዎት ቢቆሉልኝ” አለ በሚያሳዝን ድምጽ:: እሽታዋን ሰጠችውና ጥዳለት ከእንግዳዋ መምጫ አስቀድማ ደሽ ደሹን ቀጠለች:: ተሜ ተልባውን ሲቆላ ብረት ምጣዱን አልከደነውም ነበርና ተልባው እየበረረ በየስርቻው ገባ::

የሚዘጋጀውን የዶሮ ወጥ ባየ ጊዜ የአምላክ እናት ያበጀችለት ብልሃት መስሎ ስለተሰማው ገና ለገና መብላትን አስቦ በሃሴት ምራቁን እየዋጠ የፈሰሰውን ተልባ በዝግታ መልቀም ያዘ:: ከኋላው ኮቴ ሰምቶ ካቀረቀረበት ቀና ሲል አንድ ወንድ ወለሉን አልፎ ጓዳ ሲገባ ተመለከተ:: ጦቢያው የቆሎ ተማሪው ነገር እንዳይበላ ሰግታ በስርቆት አየችው:: እንዳቀረቀረ ነው በስሱ ተጽናናች:: ትንሽ ቆይቶ “ደና ዋላችሁ?” የሚል ድምጽ ከወደ ውጭ ተሰማ:: ጦቢያው “እግዚያሄር ይመስገን ማን ነው? ኖሩ” አለች ጉበኑን አልፋ ዓይኗን ወደ በራፍ ወርውራ:: መሬት ተከፍታ ብትውጣት በወደደች… ባለቤቷ ማሩ ነው:: “ምነው በደህና ነው የተመለስከው? ሀገር ሰላም አይደለም?” በማለት ተክተፈተፈች::

ማሩ እግሩን አንፈራቅቆ ሽመሉን በጉያው ከቶ ተደግፎ ቆመና በረጅሙ እየተነፈሰ “ተመንገድ ሰው አግኝቼ ብጠይቅ ጌታነህ ሁነኛ ሰው ሞቶ ለቅሶ ሄዷል አሉኝና ተመለስኩ” አለ በአጭሩ:: “ነፍሱን አይጥ ይብላው እቴ … በዛሬው ቀን ይሞታል?” ብላ አጉተመተመች:: “አናገርሽኝ?” አለ ማሩ:: “አንተስ በዚያው አትደርስም ኖሯል?” አለች ከንፈሯን ነክሳ:: “ቀብሩ የትኛው ደብር እንደሆነ አጣርቼ በሌላ ቀን እደርሳለሁ ብየ ተመለስኩ” ብሎ መለሰላት:: “ኧረ ለመሆኑ ማን ነው የሞተው?” አለች የሚቀጥለው የቤቷ ትርምስምስ እንደ ምርግ እየከበዳት::

“የነጌታነህ እድርተኛ ነው” ብሏት ወደቤት ሲዘልቅ የቆሎ ተማሪውን እንደዶሮ አቀርቅሮ አገኘው:: ከመደቡ እግሩን እያጠፈ “ምነው ደፍቴ ደናም አይደለህ?” ሲል ጠየቀው:: “እመይቴ ተልባ ቆልተውልኝ የፈሰሰውን እየለቀምኩ ነው ጌታዬ” አለ በትህትና እጅ ነስቶ:: ጦቢያው የምትሆነው ጠፍቷት ትንቆራጠጣለች:: “ምን አለ ስትመለስ የሀገሬ አድባር እንዳለ እህል ውሃህን በጨለጠው…” ትላለች ደጋግማ:: “ምን ሆነሻል?” ሲላት እንደ መባተት ብላ “እግርህን ልለቅልቅህ?” አለች:: “መጀመሪያ መዓድ አቅርቢ” አለ ሁኔታዋ ግር ብሎት:: ገበታው እንደተሰየመ የቆሎ ተማሪው አመስግኖ በጓዳ በኩል ዘለቀ:: አባዋራው ማሩ “ምን ሆነሃል ደፍቴ? በሱ ላይ ደጃፍ የለም” አለ በአግራሞት እየሳቀ:: ደፍቴ እንደመደንገጥ ብሎ “ይቅርታ ጌታየ በዚህ በኩል ሰው ሲያልፍ አይቼ በር መስሎኝ ነው” አለ:: ጦቢያው አዛማት:: ማሩ “የምን ሰው ነው?” ብሎ ከጓዳ ቢገባ ወዛም ሰውዬ ኩርምት ብሎ ተቀምጧል:: አጥናፉ ካፈርኩ አይመልሰኝ ግብግብ ያዘው:: ይህን ጊዜ የቆሎ ተማሪው ቀልጠፍ ብሎ የቀረበውን ምግብ ወደ አኮፋዳው ገለበጠና “እርቀ ሰላሙን ያውርድላችሁ” ብሏቸው እየሳቀ ወጣ::

ሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You