አዲስ አበባ፡– በቀጣይ የሚከበሩ በዓላት እና የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በሰላም እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ፤ ከተማ አቀፍ የሰላም ኮንፈረስ ትናንት በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ሲካሄድ እንደገለጹት፤ በቀጣይ በመዲናዋ የሚከበሩ የገና፤ የከተራና የጥምቀት በዓላት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ በሰላም እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በመዲናዋ ማህበረሰቡን የሰላም ባለቤትና ዘብ በማድረግ ያለውን ሰላም የማፅናት፤ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡና ሰላማዊ ህይወት እንዲኖሩ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ሰላም ከቤት ይጀምራል፤ ማህበረሰቡ ሰላሙን ከቤት በመጀመርና የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ በኩል እየተወጣው ያለው ሚና ትልቅ ነው ብለዋል፡፡
ማህበረሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት በመሥራት የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲከበሩና ትላልቅ ስብሰባዎችም በሰላም እንዲካሄዱ ማድረግ እንዳለበት ኃላፊዋ አመልክተው፤ በከተማዋ ሰላም የማስፈን ሥራ በመሠራቱም የተቀናጀ የኮሪደር ልማቶች ተሠርተዋል፤ እየተሠሩም ነው፤ ትልልቅ ፕሮጀክቶችም በጊዜያቸውና በፍጥነት እየተጠናቀቁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሰላም ለሁሉም ነገር ቁልፍ መፍቻ ነው፤ የመዲናዋን ሰላም ለማፅናትና ዘላቂ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተናግረው፤ በቀጣይ በመዲናዋ የሚከበሩ የገና፤ የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ፤ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባም በሰላም እንዲካሄድ ማህበረሰቡ ሰላም በማስከበር በኩል ያለውን ሚና ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው፤ መንግሥት የሰላም እጦት ያለባቸውን አካባቢዎች ሰላም ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ነው፤ ጫካ ለገቡ አካላት የሰላም ጥሪም እያደረገ ነው። የመዲናዋን ሰላም በማፅናትና ዘላቂ በማድረግ፤ የዜጎችን ኑሮ ምቹ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ሰላሟን ለማስከበርም ሌት ተቀን እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
በመዲናዋ የተሠራው ሰላም የማስከበር ሥራ የልማት ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል ያሉት አቶ አብርሃም፤ ሃሳቦችን ወደ መድረክ አምጥቶ በመነጋገር፤ መግባባትና አሉ የተባሉ ችግሮችን መፍታት ይቻላል፤ አፈሙዝ ለችግሮች መፍትሔ አያመጣም፡፡ መፍትሔ የሚያመጣው መመካከር ነው ብለዋል፡፡
መላው ማህበረሰብ ለሰላም የሚገባውን ሁሉ በማድረግ ሰላምን ማፅናትና ዘላቂ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመው፤
በታኅሣሥ መጨረሻና በጥር ወራት የሚከበሩ የገና፣ የከተራ፣የጥምቀትና ሌሎች በዓላት በሰላም እንዲከበሩ፤ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማህበረሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጀት ሊሠራ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም