ከ8 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ባለይዞታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደተሰጠ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- ከስምንት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ የመሬት ባለይዞታዎች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መሰጠቱን በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈፃሚ የጂኦስፓሻል ዴስክ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ያለምዘውድ ደምሴ ገለጹ፡፡

የይዞታ ማረጋገጫው በዋናነት ማሳዎችን መሰረት ያደረገ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ባለይዞታው በህይወት ባይኖር፣ መሬቱ በስጦታ ቢሰጥ ወዘተ በቋሚነት የምናገኘው ማሳውን ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

እንደሀገር 50 ሚሊዮን ማሳዎች አሉ ተብሎ እንደሚገመት ገልጸው፤ ከእነዚህ ውስጥ ለ30 ሚሊዮኑ የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ተሰጥቷል፡፡ አንድ የመሬት ባለይዞታ አንድና ከዚያ በላይ ማሳዎች እንደሚኖረው ታሳቢ በማድረግ እስካሁን ከ8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የመሬት ባለይዞታዎች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

ከነሀሴ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ በገባው አዲሱ የመሬት አዋጅ መሰረት የመሬት ባለይዞታው የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬቱን ከያዘ መሬት የማውረስ፣ የማከራየት፣ አስይዞ የመበደርና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን መጠቀም እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

አዋጁ መሬቱን ከመሸጥና ከመለወጥ ውጪ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ መብቶችን እንደሚፈቅድም ጠቁመዋል፡፡

እንደሀገር በ458 ወረዳዎች ብሔራዊ የመሬት መረጃ ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ኃላፊዋ፤ ይህ ሥርዓት ከወረዳ አንስቶ እስከ ሀገር አቀፍ በሚሰጠው መረጃ መሰረት በየጊዜው መረጃዎች እየተከለሱ የሚሄዱበት አሰራር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ መሰጠቱ እንደሀገር የመሬት ባለይዞታውን ሕጋዊነት የሚያረጋግጥ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ መሬቱን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነትም ስለሚኖር ምርታማነትን ይጨምራል ብለዋል፡፡ የአካባቢ ጥበቃንም ከማጠናከር አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

አዋጁ የሴቶችን የመሬት ይዞታ መብት ከማስጠበቅ አኳያም የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም ከአንድ በላይ ሚስት የሚያገቡ ወንዶች ከመጀመሪያዋ ጋር እኩል ተካፍለው ለሁለተኛዋ ከራሳቸው ቀሪ ላይ እንዲያካፍሉ የተደነገገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም ከአንድ በላይ የሆነ ጋብቻን ካለማበረታታቱ አኳያ ለሴቶች ተጠቃሚነት አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ አብዛኛው ማህበረሰብ የመሬትን ጉዳይ በሚመለከት ከባህላዊው ዳኝነት ይልቅ ወደ መደበኛው ፍርድ ቤትና ወደ መሬት አስተዳደር እየመጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህም የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ከመያዙ ጋር በተያያዘ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የመሬት ቀን በዓል በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በግብርና ሚኒስቴር፣ በላንድ ፎር ላይፍና በደብሊው ኤች ኤች ትብብር በትናንትናው ዕለት ተከብሮ ውሏል፡፡

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You