ዜና ትንታኔ
እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ እድገት ተከትሎ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል፡፡ ይህንኑ ፍላጎቷን እውን ለማድረግም ጥያቄዋን በሰላማዊ መንገድ እያቀረበች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ሰላማዊ የባሕር በር ጥያቄ እንደሀገር የብሔራዊ ጥቅም ዋናው ጉዳይ እንደሆነና ይህንኑ ብሔራዊ ጥቅም እውን ለማድረግ በመንግሥት በኩል ሁለገብ የዲፕሎማሲ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተነግሯል። ለመሆኑ የባሕር በር ጥያቄ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ዋነኛ ጉዳይ አድርጎ በማስቀጠል እንዴት ውጤት ማምጣት ይቻላል? በሚሉት ዙሪያ ባለሙያዎችን አነጋግረናል።
የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪው ቆስጠንጢኖስ በርሄ ተስፋ (ዶ/ር) የባሕር በር ለማንኛውም ሀገር ደህንነትና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማረጋገጥ መሠረት መሆኑን ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የሌሎች ሀገራትን የባሕር በር ማግኘት ለሌሎች ችግሮች ስለሚያጋልጥ ነው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር ሲኖራት የባሕር በሩ እንዲሁ እቃ ለማመላለስ ብቻ ሳይሆን አካባቢው ላይ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ለማቋቋም እንደሚጠቅም ነው የሚያስረዱት፡፡
ለጅቡቲ በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢትዮጵያ እንደምትከፍል የሚናገሩት ቆስጠንጢኖስ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝ ከሆነ ይህ ወጪ እንደማይኖር ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የባሕር በር ሲኖራት የውሃ ቦታዎች ስለሚኖሩ ከፍተኛ የዓሳ ምርት ማምረት የምትችልበት እድል እንዳለ ይገልፃሉ፡፡ ይህም የኅብረተሰቡን የፕሮቲን ፍላጎት በመፍታት ረገድ ጉልህ ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል ይጠቅሳሉ፡፡ በህንድ ውቅያኖስም ሆነ በቀይ ባሕር ውስጥ ማዕድናትም ስላሉ እነዚህን ማዕድናት አውጥቶ በመጠቀም ኢኮኖሚን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚቻል ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባይኖራትም ከአፍሪካ በርካታ መርከቦች ያሏት ሀገር መሆናንም ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ጠቅሰው፤ እነዚህ መርከቦች በጅቡቲ ወደብ ሲቆሙ ለቆሙበት እንደሚከፍሉ ያስረዳሉ፡፡ ይህም በቀጥታ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚነካ ነው የሚገልጹት፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር ቢኖራት ቀላል የማይባል ገንዘብ ማዳን እንደሚቻል ይጠቁማሉ። ከእነዚህ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች አንፃር ነው የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ጥያቄ የህልውና ዋናው የብሔራዊ ጥቅም አካል አድርጎ የሚያነሳው ይላሉ፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሰላሳ ዓመታት ያገለገሉት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በበኩላቸው፤ ሀገር ሙሉ ለመሆን ወሰን፣ መንግሥት፣ ሕዝብ፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ ገንዘብና ሌሎችም እንደሚያስፈልጓት ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች ባልተናነሰ መልኩ አንድ ሀገር የባሕር በር እንደሚያስፈልገውም ይጠቅሳሉ፡፡ የባሕር በር የሌለው ሀገር ከሌሎቹ ጋር እኩል ሊታይ እንደማይችልም ይገልጻሉ፡፡
የባሕር በር ያለው ሀገር ባሕር በር ከሌለው ሀገር ዓመታዊ የተጣራ ምርቱ ከአንድ እስከ ሁለት ከመቶ ብልጫ እንደሚኖረውም ነው የሚጠቁሙት፡፡ ባሕር በር የሌለው ሀገር እያንዳንዱ እቃዎቹ ተፈትሸው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ከመሆናቸው አንፃር ነፃነቱም ሙሉ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር የባሕር በር ጥያቄ ወሳኝ፣ በቀላሉ የማይታይና የብሔራዊ ጥቅም ዋናውና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በሰለጠነው ዓለም የባሕር በር ጉዳይ ብዙም ጎልቶ የሚታይ ችግር ባይሆንም ባሕር በር ማግኘት ሲገባቸው ሳያገኙ ለቀሩ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት እጅግ ወሳኝና የህልውና ጉዳይ ነው። የባሕር በር ያለመኖርን ያክል ለብሔራዊ ደህንነት አስጊ የሆነ ጉዳይ እንደሌለም ነው የሚገልጹት፡፡ ከዚህ አንፃር ይህ የባሕር በር ጥያቄ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ጭምር መሆኑን በመገንዘብ ከሕፃናት እስከ አዋቂ ድረስ እንዲያውቁትና በጉዳዩ ላይ እንዲወያዩበት ማድረግ እንደሚያስልግ ይጠቁማሉ፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የባሕር በር ጥያቄው ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው ሲሉ አንዳንድ ገንዘብ ተከፍሏቸው የሚቀለቡ ኢትዮጵያውያን ባንዳዎች ነገሩን ፖለቲካዊ መልክ በማላበስ በሚያናፍሱት ውዥንብር የኢትዮጵያ ሕዝብ መሸወድ እንደሌለበትም ነው አምባሳደር ጥሩነህ የሚያመለክቱት፡፡ እውነተኛ ኢትዮጵያውያኖች ጉዳዩ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ተገንዝበው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ቆሞ የባሕር በር ጥያቄው በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲያገኝ በሰላማዊ መንገድ የበኩላቸውን ሁሉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው ያመለከቱት፡፡
ቆስጠንጢኖስ(ዶ/ር)፤ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ አሰብና ምፅዋን ጨምሮ ሌሎች ወደቦች የነበሯትና በእነዚህ ወደቦች ከፍተኛ የባሕር ንግድ እንቅስቃሴ የምታደርግ ሀገር እንደነበረች ያስታውሳሉ፡፡ ይህን የንግድ እንቅስቃሴ መልሶ ለማምጣትም ነው መንግሥት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው ይላሉ፡፡ ሰላም እስከሆነ ጥያቄው ተቀባይነት እስካገኘ ድረስ በሶማሊያ፣ ሶማሌ ላንድና ኤርትራም በኩል የባሕር በር ከተገኘ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ሊለውጡ የሚችሉ ሥራዎችን መሥራት የሚቻልበት እድል እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡
አሁን ላይ ነገሮች መስመር የያዙ ይመስሉኛል የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በተለይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለሶማሌላንድ እውቅና እሰጣለሁ እያሉ ነው መባሉ፣ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት እንደመሆኗ አሁንም ድረስ በእንግሊዞች እውቅና ያላት መሆኗ፣ በኢህአዴግ ዘመን በመንግሥት በኩል ኢኮኖሚያዋ እንዲያድግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉና አሁን ላይ ደግሞ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በቱርክ የተደረገው ድርድር ጥሩ ውጤት የሚያስገኝ ከሆነ የኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ብሔራዊ ጥቅሟን የምታስከብርበት እድል ይኖራል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠር የኤሌክትሪክ ኃይል ለጅቡቲ፣ ለሱዳን፣ ኬንያ አሁን ደግሞ ለታንዛኒያ እያቀረበች መሆኑና ይህ ቀጣናዊ ትስስር የሚታሰብ ከሆነ ኢትዮጵያ ራሷ የምትቆጣጠረው የባሕር ወደብ እንደሚያስፈልጋት ቆስጠንጢኖስ(ዶ/ር)፤ ይጠቁማሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት ግርግር የፈጠረውም ኢትዮጵያ የባሕር ኃይልም በቦታው ላይ እንደምታሰፍር ስለተገለጸ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ጅቡቲዎችም ቢሆኑ በዚህ ጉዳይ ደንገጥ ብለው የታጁራን ወደብ ለንግድ ለመስጠት ቢስማሙም የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል በቦታው እንዲሰፍር ሲጠየቁ ግን ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
እነዚህ ጉዳዮች ሰፋ ያለ ውይይት የሚደረግባቸውና በዓለም አቀፍ ግንኙነትና በዲፕሎማሲ የሚፈቱ መሆናቸውንም ነው የሚጠቁሙት፡፡ ልክ እንደ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ሁሉ አምባሳደር ጥሩነህም፤ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የራሷ የባሕር በር እንደነበራት አስታውሰው፤ በጦርነትና በተለያዩ ምክንያቶች የባሕር በሯ የተቋረጠበት ጊዜ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
በታሪክም የኢትዮጵያ መንግሥታት ባሕር በርን መቆጣጠር ያልቻሉበት ዘመን እንደነበርም ያወሳሉ። ነገር ግን ይህ ሁኔታ እንዳልቀጠለና ኢትዮጵያ እንደገና የባሕር በር አግኝታ ስትጠቀም መቆየቷን ያስታውሳሉ፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዓለም መንግሥታት ድርጅት ይህን ተገንዝቦ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት፤ ለዚህም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትዋሃድ መወሰኑንም ያመለክታሉ፡፡
በጊዜው ለኤርትራ ነፃነት የተከራከሩ ጥቂት ወገኖች መኖራቸውን ያነሱት አምባሳደር ጥሩነህ፤ ነገር ግን የዓለም መንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከባሕር በር ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ይህን ውሳኔ እንዳሳለፈም ነው የሚገልጹት። የባሕር በር አለመኖር ኢትዮጵያን ለውጭ ወረራ ክፍት ሊያደርግ እንደሚችል ስለተገነዘበ ነው ድርጅቱ ይህን ውሳኔ የወሰነው ይላሉ፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የምፅዋና አሰብ ወደቦችን ስትጠቀም እንደቆየች ይገልጻሉ፡፡
ሶማሌላንድም ሆኑ ሶማሊያ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ቢሰጡ በብዙ መልኩ ይጠቀማሉ እንጂ አይጎዱም ይላሉ፡፡ የሥራ እድል እንደሚፈጠርላቸውና አዳዲስ ክህሎቶችን እንደሚማሩም ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድገው መሆኑንም ነው የሚጠቁሙት፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ በበኩላቸው፤ አንድ ሀገር ብሔራዊ ጥቅሙን ሊያስጠብቅ የሚችለው ከሌሎች ሀገራት ጋር በሚደረግ ድርድር፣ ትብብርና ስምምነት ነው ይላሉ። የባሕር በር ጥያቄ የዓለም ሀገራት ጭምር የተረዱት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ምላሽ ሊያገኝ የሚችልበት እድል እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡
ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚያፋጥነው ይጠቁማሉ፡፡ የሀገርን ነፃነትና ደህንነትም ያስከብራል ይላሉ፡፡ በጥቅሉ አንድ የባሕር በር ያለው ሀገር የሚያገኘውን ጥቅም ሁሉ ኢትዮጵያ እንደምታገኝም ነው የሚጠቁሙት፡፡ ጠንካራ ሀገርና ሕዝብ የሚገነባውም የባሕር በር ሲኖር መሆኑን ይገልፃሉ። የኢትዮጵያ በቀጣናው ጠንካራ መሆን ደግሞ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለተቀረው የዓለም ኅብረተሰብም ጭምር መልካም መደላድልን እንደሚፈጥርም ነው አምባሳደር ጥሩነህ የሚናገሩት፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም