የዓለም የፀረ ኤችአይቪ/ ኤድስ ቀን ባሳለፍነው ህዳር 22/2011 በሀገራችን ለ31ኛ ጊዜ በዱከም ከተማ ተከብሮ ነበር። ዱከም ከተማ ውስጥ ከ500 በላይ ፋብሪካዎች ይገኛሉ። በዓሉን በዚህ ስፍራ ማክበር ያስፈለገበት ዋና ምክንያትም አካባቢው የኢንዱስትሪ አካባቢ እንደመሆኑ ይበልጥ ተጋላጭነት ሊኖር ስለሚችል ለማንቃት ጭምር ነው።
በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ማህበራት ጥምረት አባልና በኔትዎርክ ኦፍ ኔትዎርክስ ኦፍ ኤች አይቪ ፖዘቲቭ ኢን ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ መኮንን ዓለሙ በዚሁ የማንቂያ በዓል መርሐ ግብር ላይ ካገኘናቸውና ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኙ ወገኖች አንዱ ናቸው። ኃላፊውን ስለኤችአይቪ መተላለፊያ መንገድ እንዲሁም በአጋላጭ ሁኔታዎችና በመከላከሉ ዙሪያ ወጣት ማዕከላትን ጨምሮ በአመራሩና ባለድርሻ አካላት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አስመልክተን አቶ መኮንን አነጋግረን እንዲህ ብለውናል ‹‹ቫይረሱ በደሜ ውስጥ መኖሩን ካወኩኝ 26 ዓመታት በላይ ቆይቻለሁ፤ በመሰረቱ ማንም ሰው ከመገመት እና ከመጠራጠር ውጪ በዚህን ጊዜ ነው፣ በዚህ ሁኔታ ነው ለኤችአይቪ የተጋለጥኩት ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም፤ ነገር ግን አሁን እኔ በአርባዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ ነው የምገኘው። 27 ዓመት ከዚህ ዕድሜ ላይ ስትቀንስ ሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ በወጣትነት ዕድሜ ላይ ባለሁበት ጊዜ ነው የተጋለጥኩት፤ በአብዛኛው የአምራችነት ጊዜዬን ቫይረሱ በደሜ ውስጥ ኖሮ ነው የጨረስኩት። ስለዚህ በወጣትነት ዕድሜ ደግሞ በማወቅም ባለማወቅም በተለይ ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት ስለቫይረሱ ትክክለኛ ግንዛቤ ባለመኖሩ ለኤችአይቪ የሚያጋለጡ ባህሪያቶች ውስጥ በመግባታችን ምክንያት ለኤችአይቪ እንደተጋለጥኩ በትክክል መገመት ይቻላል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ወገኖች በተደራጀ መንገድ እና በጋራ ኤችአይቪን የመከላከል እና ቁጥጥር ሥራውን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ በመሰረቱት በዚህ ጥምረት ከሥራዎቻችን አንዱ በዋናነት ኤችአይቪን የመከላከል ሥራ ነው። ሥርጭቱን በመከላከል ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን እንተገብራለን፤ በተጨማሪም ደግሞ ተጽዕኖውን ከመቀነስ አንፃር ሰዎች ተመርምረው ውጤታቸውን እንዲያውቁ ቅስቀሳዎችን በማድረግ ምርመራ የሚያደርጉባቸውን ሁኔታዎች እና ምቹ አጋጣሚዎችን መፍጠር፤ ተመርምረው ውጤታቸውን ካወቁ በኋላ ደግሞ በተለይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች በቀጥታ ወደ ፀረ-ኤችአይቪ ህክምና ውስጥ ገብተው ህክምናቸውን በአግባቡ እና በትክክል ወስደው በህክምናው የሚገኘውን ውጤት እንዲያስገኙ እና ለመከላከሉም አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ነው። ተመርምረው ከቫይረሱ ነፃ የሆኑት የማህበረሰብ ክፍሎች ደግሞ ለአንዴ እና ለመጨረሻ በቀጣይ ህይወታቸው ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ የማስተማርና የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ ጥረቶች የማድረግ ሥራነው ብለውና።
ለኤችአይቪ ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን አስመልክተው በሰጡን ሀሳብ በርካታ ናቸው ብለውናል፤ ነገር ግን አንዱና ዋነኛው መተላለፊያው መንገድ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ነው። በአንድም በሌላም መንገድ በህይወት አኗኗር ዘይቤያቸው፣ በሥራ ባህሪያቸው ሁኔታ ለቫይረሱ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለኤችአይቪ ቫይረስ የሚጋለጡበት ሁኔታ አለ። በተለይም ደግሞ ወጣቶች፣ በአንድም በኩል በቅርብ ጊዜ ስለኤችአይቪ የሚሰጡ መረጃዎች፣ ቅስቀሳዎች፣ ትምህርቶች በመቀነሳቸው ተፅዕኖውን ባለማወቃቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአጓጉል ባህሪያቶች እና በውጭ የባህል ተፅዕኖ ውስጥ በመውደቃቸው የተነሳ ላልተፈለጉ ባህሪያት የሚጋለጡበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ከባህሪያቱ ጥቂቱን ለማሳያ ያህል በማለት እንዲህ ጠቅሰውልናል ከባህሪያቶች መካከል፣ ጥንቃቄ የጎደለው ወሲባዊ ግንኙነት ማድረግ አንዱ ነው፤ በዚህም የተነሳ በአብዛኛው ወጣቱ ትውልድ ለበሽታው ይበልጥ ይጋለጣል። በሌላ በኩል ደግሞ የሥራ ባህሪያቸው ለዚህ ተጋላጭ የሚያደርጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ፤ ሴተኛ አዳሪዎችን ወስደን ብናይ ከፍተኛ የስርጭት ሁኔታ ከሚስተዋልባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ይጠቀሳሉ። ረጅም ርቀት አሽከርካሪ ሾፌሮች እና የትራንስፖርት ሠራተኞች፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቃሽ ሆኖ በተለያዩ ኢንዱስትሪ ውስጥ እና አንዳንድ ሜጋ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚሠሩ ነጋዴዎችና ታራሚዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተጋላጭ ናቸው። ላልተፈለገ እርግዝና እና ለኤችአይቪ/ኤድስ የሚያጋልጣ ቸው የሥራ ባህሪያቸው፣ የአኗኗር ሁኔታዎች ስለሚገፏቸው ይበልጥ ተጋላጮች ይሆናሉ ብለዉናል።
ይሄን ዓይነቱን ተጋላጭነት ለመቀነስ መፍትሄው ምንድነው? ብለን ለጠየቅናቸው
አቶ መኮንን ሲመልሱ ኤችአይቪ/ቫይረስ ሀገራዊ የሥነልቦና፣ የጤና እና የፖለቲካ ችግር ነው። ተጋላጭነትን ለመቀነስ አንዱና ዋናው መፍትሄ፣ በሁሉም ደረጃ ላይ ያለው አመራር ኤችአይቪ አሁን ላይ የሀገራችን ብሎም የዓለማችን ፈተና መሆኑን በተገቢው መንገድ ተገንዝቦ አፀፋዊ እርምጃ እንዲወስድ ማድረግ ነው። መንግሥት የመጀመሪያ አጀንዳው አድርጎ በሚሰጠው የአመራር ሂደቶች በአጠቃላይ ኤችአይቪ ኤድስንም የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራን በአንደኛ ደረጃ ማየት አለበት፤ ሚዲያው፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት ተቋማትም ቀጣይነትና ወጥነት ባለው መንገድ ህብረተሰቡን የመቀስቀስ፣ የማስተማር፣ የባህሪ ለውጥ እና ስርፀት ሥራዎችን አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል።
በተለይ ወጣቶች ላይ አሁን የምናየው ከሞራል እና ሥነምግባር ልህቀት ጋራ ተያይዞ የሚፈጠሩ በርካታ ችግሮች አሉ። ከቤተሰብ ጀምሮ የሃይማኖት እና የትምህርት ተቋማትና በየደረጃው ያሉ አመራሮች በሥነምግባር እና ሞራል ትምህርት ላይ ያተኮረ ትምህርት መስጠት ይገባቸዋል። ኤችአይቪ በትክክል ተፅዕኖ ሊያደርስ እንደሚችል ሊማሩ ሊያውቁ በሚችሉበት ሁኔታ የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ይላሉ።
የቫይረሱን ተፅዕኖ ከመቀነስ አንፃር ያሉትን ተግዳሮቶች አስመልክተውም እንግዲህ ተፅዕኖውን ከመቀነስ አንፃር በሚዲያ እየተነገረ እንዳለው አንዱ እንቅፋት ተመርምሮ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ወደ ህክምናው አለመምጣታቸው ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ህክምናውን የጀመሩ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ከህክምናው በመውጣታቸው እና ህክምናውን በተገቢው መንገድ ባለመውሰዳቸው የተነሳ መድኃኒቱን ውጤት እንዳያመጣ አድርጓል። በአንድ በኩል ቫይረሱን እየተለማመደ መድኃኒት እንዲሰጠው፣ በሌላ በኩል ደግሞ መድኃኒቱን እየወሰዱ በተለያዩ የጤና፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ ነው። ይህም ሁኔታ በ2020 አንዱ ከተያዘው ከሦስቱ ዘጠናዎች ውስጥ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች መድኃኒታቸውን ወስደው ማክሲመም ቫይራል ሰፕሬሽን ወይም ቫይረሱ በሰውነታቸው ውስጥ ችግር በማይፈጥርበት ደረጃ ላይ ማድረስ ነው። ስለዚህ ሕክምናውን በትክክል እና በአግባቡ ባለመውሰዳቸው የተነሳ አብዛኞቹ ሰዎች በመድኃኒቱ የሚገኘውን ጥቅም ማምጣት ካልተቻለ በእኛ ድርጅት በይበልጥ አጠናክሮ የሚሠራው በተለይ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ የጤና ተቋማት ጋራ ሰዎች ህክምናቸው ላይ እንዲቆዩ እና ህክምናቸውን አቋርጠው በተለያየ ምክንያት የጠፉ መድኃኒት ተጠቃሚዎች ደግሞ ተመልሰው ወደ ህክምናው ገብተው በአግባቡ እንዲከታተሉ የማድረግ ሥራዎችን እንሠራለን።
የቫይረሱን ተጋላጭነት ለመቀነስ ዋንኛ መፍትሄው ምንድነው? በማለት ላነሳንላቸው ጥያቄም አቶ መኮንን ሲመልሱ አሁን ይበልጥ ተጋላጭ እየሆነ ያለው ወጣቱ ነው፤ የነገ የሀገሪቱ ተረካቢም ወጣቱ ነው፤ የሀገሪቱን ሕዝብ 1/3 በላይ የሚወክለው ወጣቱ ነው። ስለዚህ ወጣቱ ቅድሚያ የሚሰጡትን ነገር ቅድሚያ በመስጠት፣ ከውጭ የባህል ተጽዕኖዎች ነጻ በመሆን፣ በሞራል እና በሥነ ምግባር በታገዘ እና ዓላማቸውን በሚያሳኩበት ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ እራሳቸውን ከኤችአይቪ እና ከሌሎች ለጤና እና ለማህበራዊ ችግሮች ከሚዳርጉ ሁኔታዎች እራሳቸውን መቆጠብ ይኖርባቸዋል። እንዲሁም፣ ራስን መቆጠብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ማስተማር እና ማዳን ይኖርባቸዋል ማለት ነው ብለዋል።
የቫይረሱን ስርጭት ከመግታትና ከመቆጣ ጠር አንፃር የወጣት ማዕከላት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ሲገልጹም እኔ ባለኝ መረጃ ወጣት ማዕከላት ሲቋቋሙ ዓላማቸው ወጣቱ በሥነ ምግባር የተሟላ፣ ሞራሉን የጠበቀ፣ ባህሉን የጠበቀ፣ ለራሱ እና ለሌላው ማህበረሰብ ሊተርፍ የሚችል ወጣት ማፍሪያ ማዕከል ተብለው ነው የተቋቋሙት እና ያንን በትክክል ተጠቅመንበታል ወይ? ማዕከላቶችን ወጣቶች ለራሳቸው እና ለማህበረሰቡ አርአያ በሚሆኑበት ደረጃ እየተጠቀምንበት ነው ወይ በሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ ይላሉ። ስለዚህ ወጣት ማዕከሎቻችንን ለዚያ አገልግሎት ማዋል አለብን። እንዳውም አንዳንድ የወጣት ማዕከላት ከሥነምግባር መጠበቂያነት ባሻገር፣ ከሞራል መጠበቂያነት እና ለጤና መጠበቂያነት ባሻገር ለአጓጉል ባህሪያቶች መስፋፊያ እየሆኑ የመጡበት ሁኔታዎች አሉ። አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ የወጣት ማዕከሎቹ ከተደራጁ በኋላ ህንጻው ብቻ ቆሞ ሲሆን፣ የምናይበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ በትክክል እና በአግባቡ ከተጠቀምንበት ትምህርት ቤት ያለውን ወጣት በትምህርት ቤት እናገኘዋለን፣ ትምህርት ቤት ያለውን እና ከትምህርት ቤት ውጪ ያለውን ወጣት ደግሞ ብቸኛ ልናገኝ የምንችልበት ቦታ ወጣት ማዕከል ነው ብለዋል።
እኛም እንደ ማህበረሰብ ወጣት ማዕከላት ለሞራል እና ለሥነምግባር መገንቢያ፣ እራሱን እና ቤተሰቡን አገሩን ከኤችአይቪ እና ከሌሎች የጤና ችግሮች የሚጠብቅበትን ትጥቅ የሚታጠቅበት ማድረግ ከቻልን ወጣቱ ከዚህ በላይ ማድረግ ስለሚችል ኤችአይቪን በትክክል ለመከላከል እና ለመግታት የሚያስችል ሥራዎችን መሥራት እንችላለንና ለተግባራ ዊነቱ እንትጋ እንላለን።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
በኃይሉ አበራ