አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ስምምነቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመተግበር የምታደርጋቸውን ዘርፈ ብዙ ጥረቶችና ውጤቶች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአግባቡ እንዲያውቅ በጋራ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንም የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳን ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከኢንዱስትሪ ከግብርና፣ ከውሃና ኢነርጂ፣ ከማእድን፣ ከከተማና መሠረተ ልማትና ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ደን ልማት ጋር ትናንት ተፈራርሟል፡፡
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ በወቅቱ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ አካባቢን ከብክለትና ከብክነት ለመከላከል በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመሩ የአካባቢ ጥበቃ ስምምነቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመተግበርና የገባቸውን ቃል ለማክበር ዘርፍ ብዙ ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች፡፡
ይሁንና ሀገሪቱ አካባቢን ከብክለትና ከብክነት ለመከላከል የምትደርጋቸውን ጥረቶችና ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ዓለም በአግባቡ እንዲያውቅ ከማድረግ አንፃር ክፍተቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ብዙ እንሠራለን ብዙ እንተጋለን፣ ይሁንና ትጋትና ልፋታችን መሆን ባለበት ልክ ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ያስፈልጋል›› ያሉት ኢንጂነር ለሊሴ፤ ይህን ለማድረግም ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ ተቋማትና እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ተቋሙ በብሄራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመሩ የአካባቢ ጥበቃ ስምምነቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመተግበርና ውጤታማነታቸውን ተደራሽ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ያስገነዘቡት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጎልበትም ባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ስምምነትን በመፈራረም ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡
በሰባት ተቋማት መካከል የተፈረመው ስምምነትም በተለይ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ እና ማረጋገጫ ሥራዎች ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ እኤአ በ2030 የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን 68 ነጥብ 8 በመቶ ለመቀነስ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቃል ገብታለች›› ያሉት ኢንጂነር ለሊሴ፣ ስምምነቱም ይህን ቃል ለመፈፀም ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ስምምነት በየጊዜው ክትትል የሚደረግበት መሆኑን ያስገነዘቡት ኢንጂነር ለሊሴ፣ ተቋማቱም በልዩ ትኩረት ኢትዮጵያን ቃል ከገባችው በላይ ማሳካት እንደምትችል ማሳየትና ለዓለም ምሳሌ እንድትሆን ሌት ተቀን እንዲተጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሰባቱም ተቋማት ኃላፊዎችም፣ ቅንጅታዊ ሥራዎችን በማጎልበት ኢትዮጵያ አካባቢን ከብክለትና ከብክነት ለመከላከል የምታደርጋቸውን ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ለማስቀጠልና ውጤቶችንም በሚፈለገው መልኩ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚተጉ ቃል ገብተዋል
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 545/2016 ለአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከተሰጡት የተለያዩ ሥልጣንና ተግባር መካከል አንዱ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልኬት ሥራዎችን በማካሄድ የማረጋገጥ፣ በሌሎች የተደረጉ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልኬቶችን የማረጋገጥ የመቆጣጠር እንዲሁም ለሚመለከተው አካል ሪፖርት የማቅረብ ኃላፊነት አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም