የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት በሁሉም የፌዴራል ተቋማት እየተተገበረ ነው

አዲስ አበባ፡- በተያዘው በጀት ዓመት የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓቱ (ሲስተም) ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በሁሉም የፌዴራል ተቋማት እና ቅርንጫፎቻቸው እየተተገበረ መሆኑን የፌዴራል መንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡

የፌዴራል መንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሠረት መስቀሌ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት በ270 የፌዴራል ተቋማት እና 65 ቅርንጫፎቻቸው ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

ሲስተሙ በአዲስ አበባ ከተማ ሆነ በየክልሎች ያሉ ነጋዴዎች በፌዴራል የግዥ ሥርዓት ላይ እኩል እንዲሳተፉ እድል የሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ላይ ከ22 ሺህ በላይ አቅራቢዎች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት በ2014 ዓ.ም በዘጠኝ ተቋማት የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው፤ በዘንድሮ ዓመት በሁሉም የፌዴራል ተቋማትና ቅርንጫፎቻቸው ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ከፌዴራል ተቋማት ቅርንጫፎችም ከአዲስ አበባ ከተማ በ100 ኪሎ ሜትር ቅርበት ላይ ያሉት በሙሉ በግዥ ሥርዓቱ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ወደ ሲስተሙ ያልገቡ የፌዴራል ተቋማት ቅርንጫፎች አሉ የሚሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ራቅ ብለው በየክልሎቹ ቅርንጫፍ ያላቸው ያልገቡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እነዚህ ደግሞ በቀጣይ ጊዜያት በማሠልጠን ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

ክልሎችም የራሳቸው ሥርዓት እንደሚኖራቸው ጠቅሰው፤ ከፌዴራል መንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ጋር የተናበበ ሥርዓት እንዲኖራቸው በባለሥልጣኑ በኩል ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል፡፡ ክልሎቹም በፈጠነ ሁኔታ ወደ ሥርዓቱ የመግባት ፍላጎቱ ስላላቸው የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ በዘንድሮ ዓመት ሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች እና 65ቱ ቅርንጫፎቻቸው የግዥ እቅዳቸው በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱ መሠረት አቅደዋል፡፡ የሁሉም ተቋማት እቅድ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ ላይ ይታያል፡፡ በዚህ ዓመት ምንምን ዕቃዎች እንደሚገዙ፣ ግዥዎች ለመፈጸም ምን ያህል በጀት እንደያዙ፣ በምን አይነት የግዥ ሥርዓቶች እንደሚገዙ፣ በዓመቱ ውስጥ የትኛውን ግዥ በየትኛው ጊዜ እንደሚያከናውኑ ሁሉ የሚያሳይ ዝርዝር የግዥ እቅድ በመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት (ኢጂፒ) ውስጥ ይታያል፡፡ ይህንንም ተቋማቱ መቶ በመቶ ፈጽመዋል፡፡

እስካሁን ባለው ክትትል የግዥ ሂደታቸውን አብዛኛዎቹ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ሥርዓት በኩል እየፈጸሙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ የተለየ ችግር የሚገጥማቸው ተቋማት መኖራቸውን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በሥርዓቱ ችግር፤ ባላቸው የኔትወርክ ችግር አልያም በግዥው ልዩ ባህሪ ሁኔታ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ በመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት ግዥን ለመፈጸም የተቸገሩ ካሉ ልዩ ፍቃድ እየጠየቁና እየተፈቀደላቸው በማንዋል የሚገዙ መኖራቸው አመላክተዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ተቋማቱ ካለልዩ ፍቃድ በራሳቸው ፍቃድ ግዥ የሚፈጸሙ ካሉ ግን በኦዲት ይረጋገጣል፡፡ በማንዋል የተፈጸመ ግዥ ግልጽ ስላልሆነ ሥርዓቱ ላይ ሊታይ አይችልም፡፡ በማየት የሚቻለው በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱ የተከናወነው ብቻ ነው፡፡ በማንዋል የሚሠራ ነገር ካለ ሰነድ በመፈተሽ ይረጋገጣል፡፡ በፕሮግራማችን መሠረት ወደ ተቋማቱ ሄደን ኦዲት በምናደርግበት ጊዜ በማንዋል የተፈጸመ ግዥ ካለ ይረጋገጣል፤ ሕጋዊ ተጠያቂነትም ያስከትላል ብለዋል፡፡

የባለፈው ዓመት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ 65 በመቶ ያህል ግዥ የተፈጸመው በመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ነው፡፡ የተቀረው 35 በመቶ ያህሉ ደግሞ በማንዋል የተፈጸመ ነው፡፡ በማንዋል የተፈጸመው ግዥ አንዳንዶቹ አስፈቅደው የገዙ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ደግሞ የፌዴራል ተቋማት ሆነው ተደራሽ ያልተሆነባቸው ቅርንጫፎቻቸው ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You