ብልፅግና ለሕዝብ የገባውን ቃል በውጤታማነት እየፈጸመ መሆኑን አስታወቀ

– የፓርቲው 2ኛ ጉባዔ በመጪው ጥር ወር እንደሚካሄድ ገለጸ

አዲስ አበባ፡- የብልፅግና ፓርቲ ለሕዝብ ቃል የተገቡ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የማጠናከር፣ የዴሞክራሲ ግንባታን የማጎልበት፤ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት የማስመዝገብና ሌሎች ሥራዎችን በውጤታማነት እየፈጸመ መሆኑን የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አስታወቁ ። የፓርቲው 2ኛ ጉባዔ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ትናንት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ በመጀመሪያው የብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች ለሕዝብ ቃል የተገቡ ሥራዎች በውጤታማነት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር የመጀመሪያው ጉባዔ አጀንዳ እንደነበር አንስተው፣ በዚህ ረገድ በተለይም በአሰባሳቢ ትርክት ዙሪያ በስፋት በመሠራቱ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልፀዋል። ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ማጠናከር የሚያስችሉ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ፣ ተግባራቱ ለሀገራዊ አንድነት አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራትም በስፋት ተከናውነው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ጤናማ ትብብርን መሠረት ያደረገ ግንኙነት መፍጠር መቻሉን አመልክተዋል። ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትም ችግራቸውን በንግግርና በውይይት እንዲፈቱ ምቹ ምህዳር መፈጠሩን ጠቅሰው ፣ ለአብነትም የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተከናወኑ ሥራዎችን ዘርዝረዋል።

በቀጣይነትም ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ፣ አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ሀገር መገንባት፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት ቀዳሚ ሀገራት አንዷ እድትሆን ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ ኢኮኖሚው በአማካይ በ7 ነጥብ 2 በመቶ እያደገ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት ሀገራት መካከል አንዷ እድትሆን የተያዘውን ግብ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ በመቻሉ ከውጭ ይገባ የነበረን የስንዴ ምርት በማስቀረት ወደ ውጭ መላክ የተቻለበትን ታሪካዊ አጋጣሚም ጠቅሰዋል። የተጀመረው ጥረትም የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥና ከተረጂነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት ጥሩ መሠረት ያኖረ መሆኑን ተናግረዋል። በዲፕሎማሲ ረገድም ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም በተግባር የሚያስጠብቁ የተለያዩ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

በመጀመሪያው የብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ የተወሰኑ ውሳኔዎች፣ የተቀመጡ አቅጣጫዎችና ለሕዝብ ቃል የተገቡ ሥራዎች ውጤታማ በማድረግ ረገድ ሕዝብን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ለፓርቲው ቀጣይ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ ተዋቅሮ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። የፓርቲው 2ኛ ጉባዔም ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ፤ ብልፅግና ፓርቲ ለሕዝብ ቃል በገባው መሠረት በዘላቂ ሰላም ግንባታና አካታች ልማት ስኬቶችን አስመዝግቧል ብለዋል። ኢትዮጵያን ከግጭት አዙሪት ለማላቀቅ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥትና አወንታዊ ሰላም ግንባታ ላይ ብዙ ርቀት መጓዙን አንስተዋል። ለውጡ ያልተዋጠላቸው አካላት የፈጠሯቸውን ግጭቶች በድርድርና በውይይት ማርገቡንም ገልጸዋል።

ፓርቲው ለአወንታዊ ሰላም ግንባታ መሳካትም ችግሮችን በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት፣ የሽግግር ፍትህና የተሃድሶ ተግባራትን ለማከናወን ተግባራዊ ቁርጠኝነቱን በማሳየት ላይ መሆኑን አመልክተዋል። ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ባደረገው ጥሪ መሠረት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ወደ ሰላም በመምጣት የሀገር ጸጥታና ልማትን ለማረጋገጥ ዋነኛ ተዋናይ በመሆን ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

ብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ባለፉት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት በማጠናከር ከአንድም ሀገር ጋር ግጭት አለመግባቱንም በስኬት አንስተዋል። የሀገርን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት የሚያስጠብቁ ጠንካራ የፀጥታ ተቋማት መገንባታቸውን ጠቁመዋል።

ፓርቲው በአንደኛ ጉባዔው ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማቶችን እንደሚተገብር ቃል መግባቱን አውስተው፤ በዚሁ መሠረት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ የሚገባ ስንዴን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት የገባውን ቃል መፈጸሙን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ወደ ውጭ መላክ ተጀምሯል ብለዋል።

በቱሪዝም ዘርፉም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ገፅታ የቀየሩ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች በጥራትና በፍጥነት መተግበራቸውን አንስተዋል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ሥራ መጀመራቸው፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት፣ እና የማዕድን ዘርፉ ላይ መሠረታዊ ለውጦች መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል።

እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ፤ፓርቲው የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በገባው ቃል መሠረት የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ዲጅታል በማስገባት ሲቪል ሰርቪሱን ሪፎርም ማድረግ ጀምሯል። እንደ ሀገር ያልተሻገርናቸውን ችግሮች በመፍታት አካታች የኢኮኖሚ እድገት፣ ዘላቂ ልማትና ሰላም ላይ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እምቅ ጸጋዋን በመጠቀም ወደ ከፍታዋ ለመውሰድ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እና በተባበረ ክንድ ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ የብልፅግና ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You