ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማረጋገጥ ከሚያስችሏት እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገሪቱ ውስጥ ማበራከት እንደሆነ ይገለጻል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያም የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡ ይህ መሆኑ እንደ ሀገር ምን ፋይዳ ይኖረዋል? በዘርፉ የሚሠሩ ምሁራን የተለያዩ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡
አቶ በርኦ ሀሰን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ናቸው፡፡ አረንጓዴ ትራንስፖርትን እንደ ሀገር መፍጠር በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይናገራሉ። በተለይም በከተሞች አካባቢ ፋይዳው ቀላል እንዳልሆነ ይጠቁማሉ፡፡ የአየር ብክለት በስፋት የሚፈጠርባቸው አካባቢዎች ከተሞች በመሆናቸው ይህንን በመቀነስ በኩል የማይተካ ሚና እንዳለውም ያስረዳሉ፡፡
ቤንዚልን መጠቀም ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን ሞኖክሳይድ እና ናይትሮጅን ኦክሳይዶችን መፍጠር እንደሆነ የሚጠቁሙት አቶ በርኦ፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት በትራንስፖርት ሲስተም ውስጥ ማስገባት ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ እንደማበጀት ይቆጠራል፡፡ ለከተሞች ንጹህ አየር እና የተሻሻለ የሕዝብ ጤናንም ለማምጣት ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መበራከት እንደ ሀገር ያለው ሌላኛው ጠቀሜታ ትልቁን ግብዓት ማለትም የነዳጅ ወጪን መቀነሱ ነው የሚሉት አቶ በርኦ፤ ኢትዮጵያ በዓመት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለነዳጅ ወጪ እንደምታደርግ ያነሳሉ፡፡ ከፍተኛ ወጪ የተደረገበት ነዳጅም ጥራቱ አጠያያቂ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡ በዚህም ከትራንስፖርት ዘርፉ 14 በመቶ በላይ ጀምሮ የአካባቢ በካይ ጋዝ ሀገሪቱ እንድታመነጭ እያደረጋት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ ነዳጅን እንደ ዋና የትራንስፖርት ግብዓትነት መጠቀሟ ከፍተኛ ወጪ ከማውጣቷ ባሻገር ለጤና እና ለአካባቢ ብክለት እንድትጋለጥ ሆናለች፡፡ በጥገናና መሰል ችግሮች ምክንያት ከፍተኛ ተጨማሪ ወጪም እያወጣች ትገኛለች፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ታደለችው ሀብት እንዳትሸጋገር አግዷታል፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማበራከት ያስፈለገበት ምክንያት ይህ ነውም ይላሉ፡፡
በኤሌክትሪክ መኪና ላይ በስፋት ትኩረታቸውን አድርገው የሚሠሩና ‹‹ጀማ ኢንጅነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት›› ሥራ አስኪያጅ አቶ ትንሳኤ አማከለው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የካርቦን ልቀት 0 ነጥብ 3 ድርሻ እንዳላት ጠቅሰው ፤ ወደ 40 በመቶ የሚሆነው የአየር ብክለት በነዳጅ ከሚሠሩ በ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎቿ የሚመጣ መሆኑን ይናገራሉ። ለነዳጅ ፤ ለጥገና የሚወጣውም ወጪ ቀላል እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀሟ ብዙ ነገር እንደምታተርፍበትም ያብራራሉ፡፡
የአካባቢ ብክለትን ለመከላለክል እና ከታዳሽ ኃይል የሚገኝን ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለመጠቀም አማራጩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ ማዋል እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ትንሳኤ፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከነዳጅ ወጪ ቅነሳ ባሻገር ሌላም ጠቀሜታ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ ይህም የድምፅ ብክለትን መቀነስ እንደሆነ ጠቁመው፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጸጥ ያለ የኤሌክትሪክ ሞተሮችን ስለሚጠቀሙ ፀጥታ የሰፈነበት እና ሰላማዊ ከተማን ይፈጥራሉ ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እንዲበራከቱ የ 10 ዓመት እቅድ ይዛ እየሠራች ትገኛለች የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እንደ ሀገር 342 ሺህ እስከ 500 ሺህ የሚሆኑ ከሁለት እግር ጀምሮ ያሉ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በ10 ዓመት ውስጥ ይኖሩናል ተብሎም እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም መንግሥት ጥሩ መደላደሎችን እየፈጠረ እንዳለ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም አንዱ ከቀረጥ ነጻ የሚሆኑበትን አሠራር መፍጠሩ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
ሌላኛው የግዢ ሂደቶችን ማስተካከል መጀመሩ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ግዢዎች ሲፈጸሙ 50 በመቶ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪእንዲሆን መወሰኑም ሌላው መደላደል እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
አሁን ላይ ከ100 ሺህ ያላነሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በሀገር ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህ ቁጥር ሀገሪቱ አረንጓዴ ትራንስፖርትን በምን መልኩ እየገነባች እንዳለ የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም በኋላ ከአላት ጥቅምና የወደፊት አቅጣጫ አንጻር አያየች ስታንዳርድ አዘጋጅታለችና በስፋት የምትሠራበትም እንደሆሚሆን ይገልጻሉ፡፡ በተለይም የነዳጅና የናፍጣ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ለመቀየር የተሰጠው ትኩረት ብዙ ነገሮችን እንደሚቀይሩም ይናገራሉ፡፡
አቶ ትንሳኤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንደ ሀገር ያላቸው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል፤ ማሽኖችንና ልዩ የሆኑ የኃይል መሙያ ቦታዎችን (ስቴሽኖችን) እንደሚፈልግ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም መንግሥት ልክ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማበራከት እንደሠራው ሁሉ አገልግሎቱን በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅበታል ይላሉ፡፡ አሁን የተጀማመሩ ነገሮች እንዳሉ ጠቅሰውም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያመላክታሉ፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በሀገሪቱ ውስጥ መበራከቱን ተከትሎ ጊዜያዊ ችግር እንደሚገጥሙ አቶ በርኦን ያምናሉ፡፡ ለዚህም መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የኃይል መሙያ ማሽኖች ችግርና ኃይሉን ለመሙላት የሚያስችሉ ስቴሽኖችን በተቻለ መጠን ለማሟላትም እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
በመንግሥት በኩል እየተሠሩ ካሉ ተግባራት መካከል አንዱ አስመጪና ላኪዎች የአስመጭነት ፈቃድ ሲወስዱ በትንሹ ሁለት የቻርጅ ማሽን እንዲተክሉ በሕግ እንዲገደዱ መደረጉ ነው፡፡ በዚህም ከ360 በላይ ማሽኖች መተከል ችለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በተለያዩ ቦታዎች ከ70 በላይ ፈጣን ቻርጀሮች እንዲተከሉ ተደርገዋል፡፡ የቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎችን (ስቴሽኖችን) በተመለከተም ከሪል እስቴት ጀምሮ እስከ መኪና ማቆሚያዎች ድረስ ፈጣን ቻርጅ ማድረጊያ ማሽኖች እንዲተክሉ እየሆነ ነው፡፡ ሥራው በተጠናከረ መልኩ እንዲከናወንም እንደ ሀገር በኮሪደር ልማቶች ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁለተኛው የኮሪደር ልማት ብቻ 54 ስቴሽኖች ተፈጥረዋል፡፡ በቀጣይም 54 ስቴሽኖችን ለመፍጠር እየሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
እንደ ዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በጎርጎሪያኑ 2023 ከአጠቃላይ የመኪና ሽያጭ (ገበያ) ውስጥ አንድ አምስተኛውን ይይዛል። በጎርጎሪያኑ 2022 በዓለም ላይ ከ10 ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች የተሸጡ ሲሆን፤ ይህ አሃዝ በ2023 መገባደጃ 14 በመቶ አድጓል። በተያዘው የጎርጎሪያኑ 2024 ደግሞ ሽያጩ 17 ሚሊዮን እንደሚጠጋ መረጃው ያሳያል። ከዚህ አንጻርም ምክንያታቸው የተለያየ ቢሆንም ሀገራት ምርጫቸውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዳደረጉ መገንዘብ ይቻላል፡፡
እንደ ሁለቱም ምሁራን ሃሳብ ኢትዮጵያ በቀጣይ በዚህ መልኩ ከተጓዘች ወጪዋን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን መደላድልን ትፈጥራለች፡፡ የአየር ንብረቷን በመጠበቅም ለዜጎቿ ከድምጽም ከአየርም ብክለት የጸዳ አካባቢን ታስረክባለች። ጤናማ ዜጋንም ትፈጥራለች፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም