የተረሳው የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር

ዜና ሐተታ

ትምህርት ሚኒስቴር ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር እንዲደረግ በትኩረት እየሠራ ነው። ሚኒስቴሩ የውድድር ደንብ አዘጋጅቶ ሰሞኑን ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል ።

ትምህርት ሚኒስቴር ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ቤቶች በዞን ደረጃ እና በ2018 ዓ.ም ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ መልክ የትምህርት ቤቶችን ስፖርት ውድድር ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ መሆኑን ሰነዱ ያሳያል።

በትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ቦጋለ፤ እንደተናገሩት፤ ብዙ ሰው ስፖርት የአካል ብቃትና የአካል ጥንካሬ ብቻ ይመስለዋል። ስፖርት የአዕምሮ ብቃትና የአዕምሮ ጥንካሬ ነው። ትምህርት ቤቶች ላይ መሥራት ትውልድ ላይ መሥራት ነው። በአዕምሮ የዳበረ እና የነቃ ትውልድ የሚፈጠረው በአካላዊ ጤና የነቃ ሲሆን ነው። የትምህርት አቀባበላቸውም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ሠብዓዊነታቸው የሚገነባው በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ነው።

እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለጻ፤ ትምህርት ሚኒስቴር ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ትውልድ የሚፈጠርበት ትምህርት ቤት ላይ ይህን እንቅስቃሴ መጀመሩ ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል። በትምህርት በኩል ጤናማ እና ሥነ ምግባር ያለው ትውልድ ከመፈጠሩ ባሻገር ሀገራቸውን ወክለው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ ወጣቶች የሚፈጠሩት ከትምህርት ቤት ነውና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ወገን ድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን፣ ወረዳዎችን፣ ክልሎችን እና ቀጣናዎችን ወክለው የመጡ ተወያዮች ባቀረቧቸው ሪፖርቶች የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩ በትምህርት ቤቶች ውስጥ መነቃቃትን ፈጥሯል። የትምህርት ቤቱን ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ወጣቶችና የሥራ ኃላፊዎች ጭምር አነቃቅቷል። በተማሪዎች መካከል የመተዋወቅና የማህበራዊ መስተጋብር ልምምድ እንዲያደርጉ ዕድል ፈጥሯል። ሆኖም በአንዳንድ ክልሎች ችግሮች እንዳሉም የገለጹ ነበሩ።

ከጋምቤላ ክልል ተወክሎ የመጣው እና የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያ የሆነው መሐሪ ገብረእግዚአብሔር ባቀረበው ሪፖርት፤ በዚህ ረገድ በክልሉ ምንም እንዳልተሠራ ተናግሯል። በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት፤ የአደረጃጀት ችግር እንዳለ አስረድቷል። ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የማይንቀሳቀስ ቋሚ የሆነ ባለሙያ ያስፈልገዋል። ሪፖርት ከማቅረብ ይልቅ ተግባራዊ ክትትል ይፈልጋል። ስፖርት የትውልድን ሥነ ልቦና በማጠንከር ከፍተኛ ሚና ስላለው በቋሚነት የሚሠራ መሆን እንዳለበትም ያሳስባል።

‹‹ጋምቤላ ውስጥ በየሜዳው ኳስ የሚጫወት ነው የምታየው፣ ትምህርት ቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየወረዳው ብትገባ ኳስ የሚጫወት ታገኛለህ፤ ክልሉ ሜዳ ስለሆነ ለኳስ ምቹ ነው›› የሚለው መሐሪ፤ አሠራሩ ግን ችግር እንዳለበት ይናገራል። አሁንም እየተሠራ ያለው በልማዳዊ መንገድ ነው። ትኩረት የሚሰጠው ከዚህ በፊት በስፖርት የታወቁና የተለመዱ አካባቢዎች ላይ ብቻ ስለሆነ ይህ ልማድ መቀረፍ እንዳለበትም ያሳስባል።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መሠረተ ልማትና አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ አቶ ታዬ ግርማ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የትምህርት ቤቶች የስፖርት ሊግ ውድድር ሕገ ደንብ ወጥቶለት ትኩረት የተሰጠው የስፖርት ትምህርት በመማሪያ ክፍል ውስጥ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ መሰጠቱ ውጤታማ ስለማያደርገው ነው። ትምህርት ቤት በሁሉም ዘርፍ ተተኪ የሚፈጠርበት ስለሆነ በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ዜጋ ለመፍጠርና በስፖርቱም ዘርፍ ተተኪ ለመፍጠር ነው።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር አሠራር ደንብ ትምህርት ቤቶች ከክፍል ክፍል፣ ከትምህርት ቤት ትምህርት ቤት፣ ከቀጣና ቀጣና እና ከዚያም በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲወዳደሩ የሚያደርግ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚያደርጉት ዝግጅትም በዘጠኝ ቀጣና ተደራጅተዋል።

‹‹በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሜዳ ብቻ ሳይሆን እንደ አጠቃላይ የደረጃ (የስታንዳርድ) ችግርም እንዳለ የሚታወቅ ነው›› ያሉት አቶ ታዬ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው ‹‹ትምህርት ለትውልድ›› መሠረት ባለሀብቶችና ታዋቂ ሰዎች ለትምህርት ቤቶች እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡንም ያሳስባሉ። ትምህርት ቤቶች ሲጠናከሩ ስፖርት በቀዳሚነት እየታሰበ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ይህ የትምህርት ቤቶች ስፖርት ሊግ ውድድር መጀመር ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን የሥራ ኃላፊዎችንም አነቃቅቷል፤ ብዙዎች ጤናቸውንም እንዲጠብቁ አድርጓል ነው ያሉት።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You