አዳማ፡- ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር በቅርቡ የሰላም ስምምነት ያደረገው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተወካዮች በኦሮሚያ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ መሳተፋቸው ትልቅ ስኬት መሆኑን ኮሚሽኑ ገለጸ።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ(ፕሮፌሰር) የኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መጠናቀቁን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ ፤ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች በምክክሩ እንዲሳተፉ ለማድረግ በተደጋጋሚ ዝግጁነቱን ሲገልጽ ቆይቷል። በቅርቡ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር ስምምነት ያደረገው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ተወካዮች በምክክሩ መሳተፋቸውም ትልቅ ስኬት እንደሆነ አስታውቀዋል።
ምክክር አንዱ ተሸናፊ አንዱ አሸናፊ የሚሆንበት ሂደት ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መድረክ መሆኑን የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ምክክሩ በመደማመጥ፣ ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊነትን በመላበስና መተዛዘንን በማስቀደም ወደ መግባባት የምንደርስበት መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዋና ኮሚሽነሩ ገለጻ ፤ ከታህሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የኦሮሚያ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ከሰባት ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን በማወያየት ታሪካዊ መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።
ምክክሩ በአራት ትልልቅ ክላስተሮች ተከፋፍሎ መካሄዱን ተናግረው 5 ቀናት በወሰደ ሂደት 640 የምክክር ቡድኖች ተዋቅረው ነጻና ግልጽ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተው፤ አጀንዳዎችን የመለየት ሥራዎች በየቡድኑ በአግባቡ መከናወኑን ተናግረዋል። በየቡድኑ የተደራጁ እና የተጠናቀሩ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።
እንደ ዋና ኮሚሽነሩ ገለጻ ፤በቀጣይ ለሚከናወነው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔም 320 የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች፣12 የሃሳብ መሪዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች ተወካዮች፣ 31 የመንግሥት ተወካዮች እና ሌሎችም ተመርጠዋል።
ምርጫው ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ግልጽ እና አሳታፊ እንደነበር ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ተወካዮቻቸውን ያላሳወቁ እንደ ሃይማኖት እና ፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉ ተቋማት በኮሚሽኑ አሠራር መሠረት በቀጣይ በተቋማቸው በኩል ተወካዮቻቸውን እንደሚያሳውቁ ጠቁመዋል።
የሴቶች ተሳትፎ 30 በመቶ እንዲሆን ኮሚሽኑ ካስቀመጠው ግብ አኳያ የተሳካ እንደነበረ ጠቁመው ፤ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎም በጥንካሬ የታየ መሆኑን አመላክተዋል። የሚዲያ አካላት የኦሮሚያ አጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክን ለሕዝብ በማድረስ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዋና ኮሚሽነሩ፤ የምክክሩ ሂደት የተሳካ እንዲሆን ተገቢውን ትብብር እና ድጋፍ ያደረጉ ሌሎች አካላትንም አመስግነዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሳተፉ የተመረጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ወኪሎች የተሰጣቸውን አደራ መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም