ዜና ትንታኔ
የናይል ወንዝ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ወደተፈጻሚነት ከገባ ሁለት ወር ሞልቶታል። ማሕቀፉ ሕግ ሆኖ መጽደቁ ኢትዮጵያን ጨምሮ በወንዙ ውሃ ፍትሃዊ አጠቃቀም ዙሪያ ጥያቄ ላላቸው የተፋሰሱ ሀገራት ታሪካዊ ድል እንደሆነ ይታመናል።
ኮሚሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋቁሞ ወደሥራ እንዲገባ ኢትዮጵያ የትብብር ማሕቀፉን በመመሥረት የነበራትን የመሪነት ሚና ዳግም መጫወት እንዳለባት የዘርፉ ምሁራን በስፋት ይናገራሉ። ግብጽ የኮሚሽኑን መመሥረት ለማደናቀፍ የተጀመረውን ሴራ መከላከል የሚቻለው ይህን በማድረግ እንደሆነ ይመክራሉ።
አቶ ፈቂአሕመድ ነጋሽ የውሃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ግብጽና ሱዳን መጀመሪያ ላይ ድርድሩ ውስጥ የገቡት በቅኝ ግዛት የደለደሉትን ውሃ እውቅና እናሰጣለን በሚል ነበር። እንደተጀመረም አካባቢ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት እነርሱን የመደገፍ አዝማሚያ ያሳዩ ስለነበር የተሳካላቸው መስሏቸው ነበር። በኋላ ላይ ግን የእነዚያ ሀገራት መሠረታዊ ፍላጎታቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ ያሰቡት ሳይሳካ ቀርቷል።
ሰባቱም የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በኢትዮጵያ እየተመሩ ግብጽና ሱዳን ደግሞ አንድ ላይ ሆነው ድርድሩ ወደመቋጨቱ ሲቃረብ፤ ግብጽና ሱዳን ያቀዱት ስላልተሳካላቸው ስምምነቱን ጥለው እንደወጡ የሚናገሩት አቶ ፈቅአሕመድ፣ በስምምነቱ ውስጥ ከተካተቱ ከዘጠኙ ተደራዳሪ ሀገራት ሁለት ሶስተኛ ሀገሮች ከፈረሙ ወደመጽደቅ እንደሚሔድ ይታወቃልና ድርድሩ ለፊርማ ክፍት መደረጉን ያስታውሳሉ፤ በዚህም የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ፊርማዋን ያኖረችው ኢትዮጵያ ስትሆን ቀጥሎ ዑጋንዳ፣ ታንዛንያና ሩዋንዳ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ በሶስተኛው ቀን ኬንያ ስትፈርም ከዚያ ከአስር ወር በኋላ ብሩንዲ መፈረሟን ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የማጽደቅ ሒደቱ ሲጀመርም በመጀመሪያ ያጸደቀችው ኢትዮጵያ ነች። ቀጥሎም በተከታታይ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ዑጋንዳና ብሩንዲ ሲሆን፣ በዚያን በድርድሩ ወቅት ደቡብ ሱዳን ነጻ ሀገር ባለመሆኗና በሱዳን ውስጥ በመሆኗ ያልተደራደረች ሀገር ብትሆንም ነጻ ከወጣች በኋላ ግን ስድስተኛ አጽዳቂ ሀገር በመሆኗ ሕግ ለመሆን በመብቃቱ ፤ የአፍሪካ ኅብረትም ተፈጻሚ መሆኑን አሳውቋል።
ይሁንና ይላሉ የውሃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው፣ ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ግብጾች እንቅልፍ አልወሰዳቸውም። ያልፈረሙ ሀገራት እንዳይፈርሙ፣ የፈረሙ ሀገራት ከፊርማው እንዲወጡ፣ የፈረሙ ሀገራት ደግሞ እንዳያጸድቁ በማድረግና በዓመት እስከ አስር ሚሊዮን ዶላር ድረስ ወጪ በማውጣት ስምምነቱን ለማጣጣል ሲተጉ እንደነበር ያብራራሉ።
ግብጾች፣ በአብዛኛው የሚያደርጉት ነገር አንደኛ፤ ስምምነቱ የሁሉንም ሀገር ይሁንታ እስካላገኘ ድረስ ስድስት ሀገራት ብቻ የፈረሙት ስምምነት ሕገ ወጥ ነው የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የናይል ተፋሰስ ውሃን አያስተዳድርም የሚል ሲሆን፣ ሶስተኛ ደግሞ እኛን አይመለከተንም የሚሉ ነው ይላሉ። ይህን ሃሳባቸውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተጋባት እየተንቀሳቀሱ እንደሆኑም ያስረዳሉ።
ለእኛ ትልቁ ስኬት የሚባለው ግን የማሕቀፉ ሕጋዊ መሆን ቀድሞ የነበሩ ሕጎችን መሻሩ ላይ ነው የሚሉት ደግሞ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ናቸው። ለአብነትም የ1959ኙን ሁለት ሀገሮች ብቻ ወስነው እንዳሻቸው የሚያደርጉትን አካሔድ መለወጡ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ያስረዳሉ። በቀጣይ ደግሞ ኮሚሽኑ እንደሚመጣ አስታውቀው ይህን ኮሚሽን ኢትዮጵያ የምትደግፈው እንደሆነ ይናገራሉ። ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ሰላም የሚሰጥና ለሁሉም የሚጠቅም መሆኑንም ይገልጻሉ።
የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን በሕግ ተቋቁሟል። አሁን የሚቀረው መዋቅሩን አዘጋጅቶ ተግባርና ኃላፊነቱን ወስኖ በሰው ኃይል፣ በማቴሪያልና በፋይናንስ አጠናክሮ ሥራ የማስጀመር ሥራ ነው ያሉን ደግሞ አቶ ፈቅአሕመድ ሲሆኑ፣ ይህ እንዳይሳካ ግን ግብጾች ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።
ይህን ለመቋቋም ኢትዮጵያ የሚጠበቅባት ከላይኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ጋር በመሆን ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ተቀቋቁሞ ወደሥራ እንዲገባ ማድረግ ነው። ኮሚሽኑን ወደሥራ ማስገባት ሲባል በሁለንተናው ጠንካራ እንዲሆን ማድረግንም ያካትታል። ደከም ያለ፣ ውሳኔ የማይሰጥ፣ በቂ ፋይናንስና አቅም የሌለው ከሆነ አንደኛ ለውጥ አያመጣም፤ ሁለተኛ ተመልሶ የሚወድቅበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስለዚህ በጣም ጠንካራና ትልልቅ ውሳኔዎችን መወሰን የሚችል ኮሚሽን መሆን አለበት፤ ሀገራቱም በቂ የገንዘብ መጠን ሊያቀርቡለት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚህ ምክንያታቸውን ሲዘረዝሩ አእንዳሉት፤ ሀገራቱ ገንዘብ ካላቀረቡ ኮሚሽኑ የልማት አጋሮችን ገንዘብ መጠየቅ ይጀምራል፤ ገንዘብ መጠየቅ የጀመረ ዕለት ደግሞ የልማት አጋሮችን አጀንዳ እንጂ የተፋሰሱ ሀገራትን አጀንዳ ማስፈጸም አይችልም። ስለሆነም በቂ የፖለቲካ ድጋፍ የተሰጠውና ከፍተኛ የዲፕሎማሲ አቅም እንዲኖረው የተደረገ ኮሚሽን ማቋቋምና ከኮሚሽኑ ጋር ደግሞ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል።
የተፋሰሱ ሀገራት፣ ኮሚሽኑ የሚያወጣቸውን እቅዶች ከተገበሩና ወገባቸውን አስረው ወደልማት ከገቡ የግብጽን ጫና መቋቋም ብቻ ሳይሆን ግብጽ ራሷ ተመልሳ ወደ ስምምነቱ እንድትመጣ ሊያደርጋት የሚችል ነው። የኮሚሽኑ ጠንካራ መሆን ጥቅሙ ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ የተፋሰሱ ሀገሮች ጭምር ነው ይላሉ።
የውሃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው እንደሚያብራሩት፤ ኢትዮጵያ የሚጠበቅባት ነገር ቢኖር መምራት ነው። ቀደም ሲልም ወደ ድርድሩ ሲገባም ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ተጫውታለች፤ አሁንም ኮሚሽኑን በማቋቋሙ ላይ የመሪነቱን ሚና መጫወት አለባት። ሀገራቱ ግን ሲፈርሙና ሲያጸድቁ በራሳቸው ላይ የዓለም አቀፉን ግዴታ ጥለው ነውና ወደኋላ የሚሉበት ምንም ምክንያት የለም፤ ይህ የጋራ ኃላፊነት ነው።
ሚኒስትሩ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ብዙ ሀገሮች ስለማሕቀፉም ሆነ ስለኮሚሽኑ ግንዛቤውን ስላገኙ ተፈጻሚነቱ እንዲፋጠን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ። ኢትዮጵያ የምትፈልገው ይህንኑ እንደሆነ አስረድተው፤ ቀደም ሲል ግን ስለፍትሃዊነት ስንጮህ የነበረው ብቻችንን ነበር ሲሉ አስታውሰዋል። ስለሆነም ኢትዮጵያ በአሁኑ ውቅት አጋዥ ማግኘቷንም አስረድተዋል።
በዚያው ልክ ደግሞ ፈተናዎች አሉብን። የታችኞቹ ሀገሮች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ፤ ሚዲያዎችንም በመጠቀም ጭምር ኮሚሽኑ ስኬታማ እንዳይሆን ይጥራሉ። በተለይ ግብጾች የትብብር ማሕቀፉን ማጣጣልን ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ምንም አይነት ገንዘብም ሆነ ድጋፍ እንዳይገኝ በተለያየ ቦታ በመንቀሳቀስ የማከላከል ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን ጉዳዩን በአግባቡ መግለጽና ማስገንዘብ ይጠበቅብና ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ ዋና ሥራ የሚባሉት አንደኛው ስምምነቱን ማስፈጸም ሲሆን፣ ስምምነቱ ደግሞ የውሃ አጠቃቀምን፣ የውሃ ጥበቃን፣ የውሃ እንክብካቤን እንዲሁም የውሃ አስተዳደሩንም የሚመለከት ነው የሚሉት የውሃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው ናቸው። ስለዚህ ተፋሰሱ ጠንካራ ከሆነ ውሃውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ይህ ደግሞ የሁሉም ሀገራት ፍላጎት ነው። እንዲያውም ኮሚሽኑ ለሀገራቱ እስከ ውሃ መደልደል ድረስ የመሄድ ሥልጣን ይኖረዋል ብለዋል።
እንደ አቶ ፈቅአሕመድ ገለጻ፤ ሌላኛው ጉዳይ በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር ነው። እንደሚታወቀው የናይል ተፋሰስ ሀገራት በአብዛኛው ለብዙ ዘመናት ለእርስ በእርስ ግጭት፣ ድርቅ፣ ረሃብ ሲጋለጡ የቆዩና እንዳያድጉም ከፍተኛ ደባ ሲደረግባቸው የነበረ ስለሆነ አቅማቸው የዚያን ያህል የጎለበተ አይደለም። ለብቻቸው ግዙፍ የሆኑ ልማቶችን ማካሔድ አይችሉም። ስለዚህ ኮሚሽኑ ሀገራቱ የገንዘብ፣ የእውቀት እና የፖለቲካ ጉልበታቸውን አቀናጅተው በተለይ የጋራ ልማታቸውን እንዲያካሂዱ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ይሆናል።
እንዲሁም ኮሚሽኑ፣ በየተፋሰሱ ደግሞ እንደየ አግባቡ ሌሎች የልማት ተቋማት እንዲቋቋሙ የማድረግ ሥራ ይኖረዋል። ስለዚህ ያንንም ሥራ በመሥራት ሀገራቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ከሌሎች ሀገሮች ደግሞ ጫና ሲመጣ ሀገራቱን የመከላከል ሥራ የመሥራት ሁኔታዎችም ይኖራሉ። ስለዚህ ኮሚሽኑ በጣም በርካታ ድጋፍ የሚሰጥ ነው ሲሉ ያመለክታሉ።
መረጃዎች እንደሚያመክቱት፤ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ድርድሩ የተጀመረው በዘጠኝ ሀገራት መካከል እኤአ በ1997 ነው። ለ13 ዓመታት ድርድር ላይ ከቆየ በኋላ የተፈረመው እኤአ በ2010 ነው።
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ግብጾች የቱንም ያህል ቢሯሯጡ አይሳካላቸውም። ይሁንና ሁሌም ከመሞከር አይቦዝኑም። እኛ ግን የሚጠበቅብን መሥራትና እውነትን ይዘን አሸናፊ መሆን ችለናል። እኛ ዓባይ ላይ ባለማነው ኢነርጂ፣ በቀጣይም በምናለማው ኢነርጂ ኬንያ ተጠቃሚ ናት። ዛሬ ኢትዮጵያ ለኬንያ ኢነርጂ ትልካለች። በተመሳሳይ ጅቡቲም ሱዳንም ከኢትዮጵያ ተጠቃሚ ናት። ለየሀገራቱ ኢነርጂ እየሸጥንላቸው ነው።
አቶ ፈቅአሕመድ በበኩላቸው፤ ግብጽ ሴራዋን ማራመድ ትችላለች፤ ዋናው ነገር ሀገራቱ ያንን የግብጽ ጫና የመቋቋም አቅምን ማሳደግ መቻል አለባቸው ይላሉ። ሀገራቱ የግብጽን ጫና የመቋቋም አቅም የገነቡ ጊዜ የግብጽ ሩጫ ትርጉም አይኖረውም ብለዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም