የምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ምርት የሚሸጋገሩበትን አሠራር መፍጠር እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፦ የምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ምርትና አገልግሎት የሚሸጋገሩበት ጠንካራ አሠራር መፍጠር እንደሚገባ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩ ገለጸ።

በኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዴሲሳ ያደታ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የዓለምን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሳቤ የቀየረ ዘርፍ ነው።የሀገራትን ኢኮኖሚ በማይናጋ መሠረት ላይ የጣለ ዘርፍ መሆን የቻለው በምርምርና ጥናት በመታገዙ እንደሆነ አንስተዋል ።

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን አስተዋጽኦ ሊያሳካ የሚችለው በጠንካራ የጥናትና ምርምር ሥራዎች መደገፍ ሲችል መሆኑን ጠቁመው፤ የምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ምርትና አገልግሎት የሚሸጋገሩበት ጠንካራ አሠራር መፍጠር እንደሚኖርበት ተናግረዋል

እንደ እርሳቸው ገለጻ ፣ የየትኛው የዓለም ሀገር የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የልህቀት ደረጃ ላይ የደረሰው የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን ሀገራት የቴክኖሎጂ ሥራ በቀጥታ በመኮረጅና በራስ አቅም ወደ ማምረት በመግባት ነው ። የጥናትና ምርምር ተቋማት ለሀገራችን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት እውን ለማድረግ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን መቅሰም ይኖርባቸዋል ።

ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታና የኢኮኖሚ ደረጃ እንዲቃኝ አድርጎ መተግበር ያስፈልጋል ያሉት ዴሲሳ (ዶ/ር) ፣ የምርምር ሥራው ውጤታማ እንዲሆን መንግስት የተሻለ በጀት በመመደብ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል ።

በተጨማሪም የግል ባለሃብቱ ኢንዱስትሪውን የሚመሩት ባለሙያዎች ስለዘርፉ የተሻለ ዕውቀት ያላቸው እንዲሆኑ ማድርግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ባለሙያዎቹም ለጥናትና ምርምር ሥራ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ።

የጥናትና ምርምር ተቋማቱ የቴክኖሎጅ የምርምር ሥራ በቅንጅት መስራት የሚገባቸው መሆኑን ያነሱት ሥራ አስፈጻሚው ፤ በዚህም የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከምርምር ተቋማት እና ከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጋር በቅርበትና በአጋርነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ።

ኢንስቲትዩቱ የአምራች ኢንዱስትሪው በሀገር ውስጥ የሚለሙ ምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲጠቀሙ ድጋፍና ማበረታቻዎችን እያደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል ።”በዚህም አበረታች ለውጦች ቢታዩም አሁንም ለጥናትና ምርምር ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶ መስራት ይጠበቃል “ሲሉ ተናግረዋል ።

በሀገራችን የአምራች ኢንዱስትሪን ያማከለ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መፈልፈያና ማበልፀጊያ ማዕከላት እንዲፈጠሩና እንዲጠናከሩ መደረግ እንዳለበት አመልክተው ፤ኢንዱስትሪዎቹ ከምርምር፣ ከከፍተኛ ትምህርት እና ስልጠና ተቋማት ጋር የምርምርና ልማት ሥራዎችን በአጋርነት የሚያካሂዱበት አሰራርን መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

ዴሲሳ (ዶ/ር)፣ የምርምርና ልማት ተቋማት ውጤታማነትና ቅንጅታዊ አሰራር ከመዘርጋቱ ባሻገር የምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ምርትና አገልግሎት የሚሸጋገሩበት ጠንካራ አሰራር መፍጠር ላይ በትኩረት ሊሰራ የሚገባ መሆኑንም አስገንዝበዋል ።

የጥናትና ምርምር ተቋማት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን አስተዋጽኦ እንዲሳካ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸው፤የጥናትና ምርምር ተቋማት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲሳካ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል ።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You