በተለምዷዊ አካሄድ ግብርናን በማልማት የሚፈለገውን የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት እንደማይቻል ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡- በተለምዷዊ አካሄድ ግብርናን በማልማት የሚፈለገውን የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት እንዳማይቻል ተገለጸ። ከዘመኑ ጋር የሚራመዱ ምቹ የግብርና ፖሊሲዎችን በመቅረጽ የአርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ ተመልክቷል።

የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ፋጂ ጫላ የጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ተግባራዊ በሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶች ዙሪያ ውይይት ሲካሄድ እንደገለጹት፣ በተለምዷዊ መንገድ ግብርናን በማልማት በሚፈለገው ልክ የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት አይቻልም። አዳዲስ አሠራሮችንና ፖሊሲዎችን በመዘርጋትና በመቅረጽ ግብርናውን ማዘመንና የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ሕይወት መለወጥ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድም ከለውጡ ወዲህ ባለፉት ስድስት ዓመታት የሚፈለገውን ሁሉን አቀፍና ሰው ተኮር ልማትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው።

በክልሉ ግብርናን ለማሳደግ ያለውን ሀብትና እድል በመረዳት ዘርፉን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በመተግበር ውጤት ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል። ለአብነትም የበጋ መስኖንና የሌማት ቱርፋት መርሃ ግብሮችን ጠቅሰዋል። እነዚህና መሰል መርሃ ግብሮችም ውጤታማ እንዲሆኑ የባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ሚና ትልቅ እንደነበር ተናግረዋል።

ምቹ የግብርና ፖሊሲዎችን በመቅረጽ የዜጎችን ሕይወት ማሻሻልና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ አመልክተው፤ የአንድን ሀገር እድገት ለማረጋገጥና ለማሸጋገር የፖሊሲዎች ሚና ትልቅ ነው ብለዋል።

የጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን የክልሉ መንግሥት ግብርናን ለማሸጋገር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የጉዲና ቱምሳ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሌንሳ ጉዲና በመድረኩ እንደገለጹት፣ የፕሮጀክቱ ዓላማ የግብርናው ዘርፍ የሴቶች፣ ወጣቶች አካታችነት በማጥናት ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት ማቅረብ ነው።

ምቹ የግብርና ፖሊሲ እንዲዘጋጅ የሚያስችል ፕሮጀክት በሁለት ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ፕሮጀክቱ በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች የግብርና፣ ጤና፣ የአመጋገብ ሥርዓትን ጨምሮ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃትና የፋይናንስ አካታችነት ጉዳዮች ላይ ይሠራል ብለዋል።

ለፕሮጀክቱ መነሻ በኦሮሚያ ምርትና ምርታማነት ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ ግብዓቶች ተሰብስበው ጥናት መቅረቡን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ የተለያዩ ፖሊሲ አውጪዎች በሚያወጡት ፖሊሲ ለግብርና የሚያመች በማድረግ እንዲቀርጹ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ አርሶ አደሮች፣ አርብቶአደሮችና ከፊል አርብቶአደሮች፣ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲ እንዲዘጋጅ የሚያስችል መሆኑን በመግለጽ፣ ለፖሊሲው ትግበራም ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ለሁለት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልገው ከሆነ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ በሁለቱ ክልሎች ውጤታማ ከሆነ በሌሎች ክልሎችም ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You